Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዕውን የዘር ፖለቲካ በዘመን ኢሕአዴግ ነበር?

ክፍል ፪

በታዲዮስ ጥበቡ

ሰዎች በተለያዩ ጉዳዮች የተለያዩ ቡድኖችን የሚፈጥሩት ከምንም በላይ በውስጣቸው ከጠነሰሱት ሥነ ልቦናዊ ውቅርና ከምንመርጠው ቡድን ፍልስፍና መነሻነት ነው፡፡ በቀለም ከሄድን ጥቁር እንደዘር ይቆጠራል፤ ነጩም እንዲሁ፡፡ ጥቁሩ ከሌላው ጥቁር አንድ የሚያደርገኝ የቆዳ ቀለሜ ነው ብሎ የተቀበለው በመሆኑ የሥነ ልቦናዊ ውቅሩ ለጥቁር አብሮ በማበር ወይም ነጭ ከነጩ ጋር አብሮ በማበር መቧደን ይታያል፡፡ በሌላ መልኩ የሚያቀራርቡኝ ናቸው ብሎ በሚገምታቸው ነገሮች የሚገኝበት ቦታ የሚከተለው ሃይማኖት፣ የሚቀበለው የፖለቲካ ፍልስፍና ወዘተ፣ ራስን በማቧደን የክፍፍል ስያሜ ቢሰጥም በምንም መልኩ በዚህ ጋር የሚያገናኘውም የለም፡፡ ግን በጭፍለቃ አነጋገር ከዚህ ጋር ተያይዞ ይጠራል፡፡ ከዚህ ጋር አገናኝቶ ቡድንን ከመጥራት እንደሚራምደው የማኅበራዊም ይሁን የፖለቲካ ፍልስፍና ዘረኛ ከማለት ይልቅ ጠባብኛ፣ አናፋሽ፣ ንፋቃውያን፣ ተንጦልጧዮች ብንላቸው ከዚህ ጋር ሳናገናኝ ልንገልጻቸው እንችላለን፡፡

ቋንቋንና ዘርን ከመቀላቀል ባለፈ ደግሞ ቋንቋንና ማንነትን እንዲሁ ሲያደበላልቁት ይስተዋላል፡፡ የማንነትን ትርጓሜ ለመስጠት በተለመደው መልኩ ሌሎች ያሉትን አላጣቅስም፡፡ ማንነት ሰዋዊነት ነው፡፡ ሰዋዊነት ለሰው የሚያስፈለገውን መፈለግ ነው፡፡ ለሰው የሚያስፈልገው ደግሞ በሕይወት መኖርን ጨምሮ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ፍላጎቱ እንዲሟላለት ነው፣ ማንነቱ ባህሉ ሲከበርለት ነው፣ ማንነቱ ቋንቋው ሲከበርለት ነው፣ ማንነቱ የፈቀደው ቦታ መኖር መቻሉ ነው፣ ማንነቱ ያመነበትን መግለጽ ሲችል ነው፣ ማንነቱ በፈለገው ቦታ ገብቶ ማፍራት ሲችል ነው፣ ማንነቱ ያመነበትን እምነት መከተል ሲችል ነው፣ ማንነቱ የመጻፍና የመናገር መብቱ ሲከበር ነው፣ ማንነቱ የግለሰብ መብቱ ሲከበር ነው፡፡ ማንነቱ ፍትሕ ማግኘቱ ነው፣ ማንነቱ አድሎአዊነት የማይደርግበት ሲሆን ነው፣ ማንነቱ ወዘተ፣ ማንነቱ ሰውነቱ ነው፡፡፡ ከእነዚህ ከተጠቀሱት ወይም ካልተጠቀሱት ውስጥ አንዱን መዞ የማንነት መገለጫ አድርጎ መደምደም አይደለም፡፡ ማንነትም ለብቻ የሚሰጥ ለብቻ የሚነጠቅ አይደለም፤ ማንነት ከምንኖርበት ኅብረተሰብ ጋር የተቆራኘ ነው፣ ማንነት ከቋንቋ ጋር ብቻ የተቆራኘ አድርገው ይደመድሙታል፡፡ እጅግ ግዙፍ ስህተት፤ ትግርኛ የሚናገረው ሰው በሕይወት አጋጣሚው ጃፓን አገር ቀሪ ሕይወቱን ቢኖርና ጃፓንኛ ብቻ ቢናገር፣ እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ የተከበረለት ቢሆን ማንነቱን አጣ ልንል እንችላለን? አንድ ኦሮሞ ጀርመን አገር በመኖሩ እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮለት በጀርመን የመግባቢያ ቋንቋ እየተነገረ የሕይወት ዘመኑን ቢያሳልፍ ማንነቱን አጣ እንላለን? አንድ አማራ ሳዑዲ ዓረቢያ ቢኖርና ዓረብኛ ቋንቋን እየተናገረ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮለት የሚኖር ከሆነ ማንነቱን አጣ ማለት ይቻላል? የፈለግንበት ቦታ ለመኖር የራሳችን ምርጫ አድርገነው ሳንገደድበት የምንኖርበትን ማኅበረሰብ ቋንቋ በመናገራችን ማንነታችንን አጣን ወይም ማንነታችንን በፈቃዳችን አዋረድን ማለት ነው? ለመሆኑ በፈቃድ ማንነቱን አሳልፎ በመስጠት መዋረድ የሚፈልግ አለ? ኢኮኖሚያዊ ችግር ኖሮብን እንኳን ቢሆን ተገደን ካልሆነ በስተቀር ወደን ማንነታችንን እናዋርዳለን? ኢኮኖሚያዊ ችግር ሳይሆን ከፍተኛ ልዕልና ላይ የደረሰ ምሁር አፍ የፈታበትን ቋንቋ ትቶ እንግሊዝኛ እየተናገረ አሜሪካ የናሳ ሠራተኛ ቢሆን ማንነቱን አጣ ልንለው ነው? ነው ወይስ በውዴታ ማንነቱን አዋረደ? ይህን ሁላ ያልኩት ቋንቋና ማንነት የማይገናኙ መሆናቸውን በምሳሌነት ለማቅረብ ነው፡፡ እንግሊዝኛ እየተናገረ ናሳ ውስጥ የሚሠራ ምሁር አፍን የፈታበት ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ወዘተ ቢሆን እነዚህን ቋንቋዎች በመናገሩ ዝቅ ተደርጎ ሊታይ ወይም ክብሩ ሊዋረድ አይገባም እንጂ፣ እንግሊዝኛ በመናገሩ ማንነቱን አጣ ማለት አይደለም፡፡ ሕወሓት ወራሹ መንግሥትና ሌሎች ጋሻ ጃግሬዎቹ ቋንቋን ከፍታ ያለው የማንነት መገለጫ አድርጎ ከማየትም በዘለለ ጠቅለል አድርገው ማንነትን ከቋንቋ ጋር ብቻ አጣምረውታል፡፡ ከቋንቋ ውጭ የሰው ሌሎች የማንነት መገለጫዎች አይታዩዋቸውም ወይም ሊያዩቸውም አይፈልጉም፡፡

በአማራው ማኅበረሰብ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ፖለቲካን በግሪኮች አነጋገር ሳይሆን በራሱ የአነጋገር ዘይቤ ‹ቦተሊካ› ይለዋል ትርጓሜውም ‹‹ውሸት›› ማለት ነው፡፡ የግሪክና ኢትዮጵያ ትውውቅ ጥንተ ጥንት እንጂ እንደሌሎች የዘመኑ አዳጊ አገሮች የቅርብ ዘመን አይደለም፡፡ የቃለ መወራረሱም እንዲሁ ጥንተ ጥንት ነው፡፡ ምንም እንኳን በእውነታው ሲታይ ፖለቲካ ውሸት የማያጣው ቢሆንም ቅጥ ያጣ ውሸት ሲሆን ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን ያሳጣል፡፡ ፖለቲከኞች አዋቂዎች ናቸው፣ ሕዝብ ያለአዋቂ ነው፣ ፖለቲከኞች አዋቂዎች ናቸው፣ ሕዝብ ለራሱም አይቆረቆርም ወዘተ ያሰኛል፡፡ ሕወሓት መራሹ መንግሥት ወይንም በዚህ ጊዜም ቢሆን የእነሱን የፖለቲካ መስመር ለመከተል የሞት ሽረት ነው ብለው የሚያምኑ በግዙፍ ውሸት ሕዝብን ማታለል አይቻልም፡፡ ቋንቋ ማንነት ብቻ አይደለም፣ የቋንቋ ፖለቲካም የማንነት ፖለቲካ አይደለም፣ ቋንቋ የዘር መገለጫም አይደለም፣ ዘርና ቋንቋም አይገናኙም፣ ወሰን በቋንቋ ተናጋሪነት ካልተለየ አሐዳዊ ፖለቲካ ማለትም አይደለም፣ የአሜሪካ ግዛቶች ወሰን የተከለለው በቋንቋ ተናጋሪነት አይደለም፡፡ ታዲያ አሜሪካ አሐዳዊ ፖለቲካን ነው የምታራምደው? አሜሪካ እኮ ፌዴራላዊ የፖለቲካ ሥርዓት የምትከተል ቁጥር አንድ ዴሞክራሲያዊት አገር ናት፡፡ የሕወሓት ፖለቲከኞችና አቀንቃኞቻቸው ሕዝብ አያውቀውም ብለው ደምድመውታል? ልብ ሌላ ምላስ ሌላ ካልሆነ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማምጣትና በአገራችን ማስፈን ይኖርብናል እያልን እንጮሀለን፡፡ ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ካልሆነ በስተቀር እውነትም ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋታል፤ ታዲያ አሐዳዊ ሥርዓትን የፖለቲካ ፕሮግራሙ አድርጎ የሚደራጅ የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ቢመዘገብ ወንጀለኛ ነው? እስካሁን አንድም የፖለቲካ ፓርቲ አሐዳዊ ፖለቲካን አራምዳለሁ ብሎ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ለሕዝብ ያሳወቀ የለም፡፡ ቢኖርስ መብቱ አይደለም? ዴሞክራሲ ማበቢያ አሐዳዊ ማስፈራሪያ ነው? የቁርጥ ጊዜ የልማት አጋር የሆነችን ቻይና የፖለቲካ ሥርዓቷ አሐዳዊ ነው ታዲያ አሐዳዊን እንደ ሰይጣን ካየነው ለምን ከቻይና ተጠጋን? ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ በማንኛውም ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ መድረክ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን አጋርነቷን ለረዥም ዘመናት ያስመሰከረችው፣ በጣሊያን ወረራም በሶማሊያ ወረራም እንዲሁም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም የኢትዮጵያ አጋር የሆነችው ሩሲያ አሐዳዊ መንግሥት ናት የተሳሳተ ፖለቲካዊ ሥርዓት ነው? የፖለቲካ ሥርዓትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መምረጥ ያለበት ሕዝብ እንጂ ፖለቲከኞች መሆን አለበት? ፌዴራላዊም ይሁን አሐዳዊ መንግሥትን በኢትዮጵያ ለመትከል መወሰን ያለበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሳተፈበት አብላጫ ድምፅ እንጂ፣ ፖለቲከኞች ያቀረቡልንን ተጋቱት በግድም በውድም በማለት ነው? ፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ ሥርዓትን በእነሱ ችሮታ ለሕዝብ የሚሰጡትና የሚነሱትስ መሆን አለበት? የሕዝብ ይሁንታና የሕዝብ የበላይነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሰማይ የራቀ መሆን አለበት? አምባገነን መሪዎችስ የሚፈለፈሉት የፖለቲካ ሥርዓቱን በእኛ ችሮታ ለሕዝብ ሰጥተናል በሚል የትቢታዊ አስተሳሰብ አይደለም ትላላችሁ?

ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ የሕወሓትን የፖለቲካ መርህ ስንገልጸው በአብዛኛው ዘረኝነት የሚለውን ቃል ስንጠቀም ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳን ቃል አጠቃቀም እንደ አግባቡ ቢሆንም የሕወሓት የፖለቲካ ሥርዓት ዘረኝነት ሳይሆን ቋንቋ መር ንፋቃውያን ነው፡፡ ቋንቋን እንደዘር በመቁጠር የኑፋቄ ፖለቲካን ከልክ በላይ በማራገብ ሕዝብ ለሕዝብ እንዲለያይ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ ሥራ ሲሠሩ በመቆየታቸው በዘር ግንድ አንድ የሆነውን ሳይቀር በኑፋቄ ቋንቋ እንዲለያይ አድርገውታል፡፡ ሕወሓት ብቻም ሳይሆን ሌሎች ፀረ ኢትጵያውያን የቋንቋ ብዝኃነትን እንደ መግቢያ ቀዳዳ በመቁጠር በቋንቋ መለያየታችን በዳይ ተበዳይ አድርጎ በሐሰት የማወናበድ ንፋቃን ቋንቋ ሲሰበክ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉት ከ80 በላይ ብሔረሰቦች በመቼም ዘመን በመቼም ጊዜ አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔረሰብ የጨቆነበት አጋጣሚ የለም፡፡ ኖሮም አያውቅም፡፡ ሕወሓት መር በሆነው አንድ የኢሕአዴግ ስብሰባ ላይ አንደኛው ተሰብሳቢ ተነስቶ የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ልጅ መሆኑን ገለጸና መደምደሚያው ግን የሚያሳዝን ነበር፡፡ አባቴ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ እናቴ ደግሞ ከአባቴ የተለየውን የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆኗ ሁሌ ይጣሉ ስለነበር አባቴን ጠልቼዋለሁ፡፡ እሱ የሚናገረውንም ቋንቋ ጠልቼዋለሁ ብሎ ተናገረ፡፡ በትዳር ውስጥ ቋንቋ መሠረታዊ ችግር ሆኖ አያጣላም፣ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ቢያጣላ ኖሮ ሲጀመርም አይጋቡም ነበር፣ ተመሳሳይ ቋንቋም ኖሯቸው የሚጣሉ ባለትዳሮች አሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ የሚፋቱም አሉ፣ ልጅ በወላጆቹ መሀል የጥል ምክንያቶች የሆነውን ላያውቅ ይችላል፡፡ በቋንቋ ልዩነት ነው ብሎ መደምደሙ ግን ስህተት ነው ፣ይህ ሰው ይህን ምስክርነቱን ሲሰጥ ሕወሓት በተለያየ ቋንቋ የምንናገርን ኢትዮጵያውያን ስንናቆር እርስ በርሳችን ስንሻኮትና ስንጣላ እርሱ የአገዛዝ ዕድሜውን እንደሚጨምር ስላሰበ ይህ ዓይነቱን የዋህ ምስክር ሰጪ ልቦናን እውነት አስመስሎ ተቆጣጥሮታል፡፡ የዚህ ሰው ወላጆች እናቱም አባቱም ዘሩ መሆናቸውን ግን ከቶ ሊሽረው ባልተገባ ነበር፡፡ እናቴን የበደለ አባቴ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆኑ የአባቱን ቋንቋ የሚናገርን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅ በምን አግባብ ተገቢ ይሆናል? ሁለት ወንድምና እህት ቢጣሉ ከጥሉ ውጭ ያሉ ወንድ ወይም ሴት እህትና ወንድም ያለ ምክንያታዊነት በምን መልኩ በጭፍንነት ለአንድ ይወግኑ? እርሱ የእኔ መንትያ ስለሆነ ወይም እርሷ ይወግኑ? እርሱ የእኔ መንትያ ስለሆነ ወይም እሷ የእኔ ተከታይ ስለሆነች ወይም እሱ የእኔ ቀጥተኛ ታላቅ ስለሆነ ወዘተ በሚል ተልካሻ ምክንያት ይወገን ወይንስ ላለመግባባት ምክንያቶች ካሉ መርምሮ እንደየባህላችን በአስታራቂ ሽማግሌነት መልካም የእህት ወንድምነት ትስስራችንን እናምጣ፡፡ ጥቅም እንኳን ቢያጣላ ወይም ቢያወዛግብ ጥቅሙ መቅረት ይችላል፡፡ ዝምድናው ግን ሊቀር ይችላል? ዝምድናውን ፈልገን ወይም በዘልማድ ያገኘነው አይደለም፣ ተፈጥሮ የሰጠን እንጂ ጥቅምን ግን ስንፈልግ የምናገኘው ካልፈለግን የምንተወው ወይም ፈልገንም አልፈለግንም ሊገኝ ወይም ሊታጣ የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሰዎች ትጋት ጋር ተዛምዶ የሚገኝ የሚታጣ ቢሆንም ተፈጥሮአዊ ግን አይደለም፡፡ ዘር ግን ብንፈልገውም ባንፈልገውም ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡

ቋንቋን እንደ ዘር በመቁጠር የለከፈን በሽታ የከሌ መንግሥት የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ ነበር፣ በመሆኑም የዚህን ቋንቋ ተናጋሪ ሴት ጡት ቆርጧልና የእሱን ቋንቋ የሚናገር በሙሉ የተወገዘ ይሁን፣ የእሱን ቋንቋ የተናገረ ሁሉ ጨቋኝ ነበር፣ ወዘተ ብሎ ፍረጃ እንደምን ይመዘናል? እከሌ መሪ በመሆኑ ጡት ስለመቁረጡ እርግጠኛ ሳይኮን የእሱን ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩት ሁሉ በምን መልኩ ጨቋኝ ተሰኝተው ይፈረጃሉ? አንድ መንግሥት የራሱን የግዛት ጠንካራነት ለማምጣት ወይም የሚገብርለትን ለማብዛት ወይም እምቢተኛን ለማበርከክ ወይም ለሌሎች ምክንያቶች ከሚገዳደሯቸው ጋር የይዋጣልን ጉልበት መፈተኛ ጦርነት ይካሄዳሉ፡፡ በጦርነት ደግሞ መሞሸር ሳይሆን መሞት ነው ያለው፣ መቁሰል ነው ያለው፣ ሽንፈትን መቀበል ነው ያለው፣ ታዲያ አሸናፊ የሆነው አሸናፊነቱን ያገኘው ወይ ሊያሸንፍ፣ አልያም ሊሸነፍ መሆኑን እያወቀ በመሆኑ ሲያሸንፍ ተሸናፊው ጉዳት ደርሶበት እንደሚሆን ይታወቃልና ተሸናፊ ለምን ጉዳት ደረሰበት ብሎ መደምደም ተገቢ ይሆናል? ያለ ጉዳት ከሆነማ ሲጀመርም ጦርነት አልነበረም፡፡ በጦርነት የተማረከን ወይም ሕይወቱ የተሰዋን ሰዋዊ በሆነ አግባብ መደረግ ያለበትን አለማድረግ፣ መደረግ የሌለበትን ማድረግ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና አይደለም፡፡ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ሰብዕናን ከፍ ከፍ በማድረግ ሰብዓዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ ይህ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና የዘቀጠበት ድርጊት ወርዶ የዘቀጠ ተግባር አይፈጽምም፤ ለምን ቢባል አሸናፊነቱን አረጋግጧል፡፡ የተሸነፈው ሁሉ ትዕዛዙን የሚፈጽም ነውና ሌላ ኢሰብዓዊነት ድርጊት አያስፈልገውም፤ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ቡድን የሚገዳደሩ የሉም ባይባልም እንደየአቅማቸው የሚመጥን ቅጣት ሊሰጥ ይችል ይሆናል እንጂ ኢሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ መፈጸም ይኖራል ማለት ያስቸግራል፡፡ በጦርነትም ይሁን በሌላ መልኩ የበላይነትን የያዘ ወገን የሚያስተላልፈው ትዕዛዝ ተግባራዊ ባይሆን ከእስራት እስከ ሞት ብይን ማድረግ ይቻላል፡፡ የቅርብ ምሳሌ ለመስጠት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥቱ ነዋይንና በላይ ዘለቀን በስቅላት እንዲቀጡ አድርገዋል፡፡ ድርጊቱ ትክክል ነው አይደለም ብዙ ሊባል ቢችልም እንደ መንግሥት ውሳኔያቸውን የመወሰን መብትና ሥልጣን ነበራቸው፡፡ ዕውን በቋንቋ ላይ በደል ነበር? ቋንቋ ምን መሠረታዊ የመደብ ልዩነት ስላለው ነው በዳይ ተበዳዩን የሚያስነሳ? በአፍ መፍቻ ቋንቋው በመናገሩ እንደ ወንጀለኛ የተቆጠረ ነበር? ከሕወሓት መንግሥትነት አንድን ቋንቋ ናቂ ሌላውን ተናቂ በማስመሰል በሥነ ልቦና ለመለያየት፣ ይህ ስም ይህን ቋንቋ ለማንቋሸሽ ነው ይህ ስያሜ ሌላውን ቋንቋ ለማጥላላት ነው፤ በሚል ለተወሰኑ ቋንቋዎች የተለጠፉ ቃሎች ነበሩ፡፡ እንድንለያይ ስለተፈለገ ዳሩ ግን አንዱ ቋንቋ የበላይ ሆኖ ሌላው ቋንቋ በታች ሆኖ አላገለገለም ወይም አልተንቋሸሸም፡፡ ሰዎች ቋንቋ በዳይ ነው ስላሉን ብቻ ቆም ብለን ስናስተውል አሜን ብለን በድያለሁ ወይም ተበድያለሁ እንበል? ሕወሓት በረጨው የቋንቋ ፖለቲካ አራጋቢነት በየፊናው ተበዳይ ብሎ በመዝራቱ በቋንቋ የተበደሉ የመሰላቸው ሰዎች ወይም ቋንቋ በዳይንና ተበዳይን ይፈጥራል ብለው እንዲያራግቡ ተልዕኮ የተሰጣቸው ሰዎች የበዳይ ተበዳይነትን ትርከት ሲያናፍሱ በተሰጣቸው የቋንቋ ፖለቲካ አራጋቢነት ውለታ ሲሾሙ የአካባቢ መጠሪያን መቀየር ጀመሩ፡፡ የአካባቢ ስም በመቀየርም የባለቤትነት ማረጋገጫ የሚሆን መሰላቸው፤ አዲስ አበባን ፊንፊኔ፣ ደብረ ዘይትን ቢሾፍቱ፣ ናዝሬትን አዳማ፣ ዝዋይን ጭላሎ፣ ወዘተ. በሚል ተኳቸው፡፡ ስም የባለቤትነት ዋስትናን የሚሰጥ ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ድረስ ደብረ ዘይትንና ናዝሬትን እስራኤል የይገባኛል ጥያቄ ባቀረበች ነበር፡፡ በደቡብ ወሎ የሚገኙትን ሊባኖስና ደማስቆንም እንዲሁ የሊባኖስና የሶሪያ በሆኑ ነበር፡፡ በአማራው ክልል የኦሮምኛ ስያሜ ያላቸው እነ ይልማና ዴንሳ፣ ወሎ፣ ቦረና፣ ወረኢሉ፣ ወዘተ. የይገባኛል ጥያቄ እንዳይነሳ አማራው ስማቸውን በቀየረ ነበር፡፡ የስም አሰያየሞች የራሳቸው የታሪክ ዳራ ይኖራቸዋል፡፡ እኛ በጥናትና ምርምር ወይም ከዚህ ውጪ በአፈታሪክ ያልተላለፈልን ሆኖ ወይም የተጻፈ ታሪክ ቢኖርም ገና ያገኘነው ሆኖ ወይም ቢጻፍም ታሪኩ ጠፍቶ ይሆናል እንጂ ይበልጥ የሚያኮራን ታሪካዊ መስህብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለማጥፋት ከመሮጥ ለማወቅ ብንጓጓ ይሻል ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያራመድነው ያለው የዘር ፖለቲካ ሳይሆን የቋንቋ ፖለቲካ ለግለሰብም፣ ለቡድንም፣ ለኅብረተሰብም፣ እንዲሁም ለአገርም የማይጠቅም መሆኑን በጥልቀት በመመርመር ተረድተን ወደሚያዋጣው የፖለቲካ ፍልስፍና እዝነ ልቦናችንን ብናሰባስብ ይሻላል፡፡ በዘር ወይም በቋንቋ፣ ወይም በሃይማኖት ፖለቲካን መቃኘት እጅጉን የከፋ ነው፡፡ አገራችን በታሪኳ ሁሉንም አልፋበታለች፤ በዘር ፖለቲካ በንጉሣዊ ሥርወ መንግሥትና ኢምሮች ተዳድራለች፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን የክርስትናው እንዳለ ሆኖ ግራኝ አህመድ እስከ ጎንደር ድረስ ደርሰው ገዝተዋል፡፡ የቋንቋ ፖለቲካም እንዲሁ ባለፉት 27 ዓመታት የሕወሓት መራሹ መንግሥት አሳይቶናል፡፡ አሁንም ቢሆን ሞተሩን የሚዘውረው ተቀያየሩ እንጂ የቋንቋ ፖለቲካው ነው፡፡ ሞተን እንገኝ እንጂ የቋንቋ ፖለቲካውን የሙጥኝ እንላለን የሚሉት ቀላል አይደለም፡፡ ያገኘነውን ድል አሳልፈን አንሰጥም ይላሉ፡፡ በመሆኑም የፖለቲካው ወጀብ ወደየት እንደሚወስደን አላወቅነውም፡፡ የቋንቋ ፖለቲካን የሚቃወሙትም የዘግ (የዘውግ) ፖለቲካ እያሉን ነው፡፡ ለፖለቲካው መጠሪያነት ከምንጨነቅ ፍልስፍናው ላይና ራዕዩ ላይ ትኩረት ብናደርግ ይሻል ነበር፡፡ ለነገሩ አይፈረድም እየነጎድን ያለነው በሚሉን እንጂ በማስተዋል መርምረን ባለመሆኑ ነው፡፡ ከ27 ዓመት በፊት ፖለቲካው መሠረቱ የነበረው በብዙ ቁጥር የሚጠቀስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የትምህርት ተደራሽነት አናሳ በሆነበት ሁኔታ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ደግሞ የአንዳንድ ትናንሽ አገሮች የሚኖራቸውን የሕዝብ ብዛት ያህል በትምህርት ላይ ያለን ወጣት ይዘን ነው፡፡ የተማረውም ይሁን በመማር ላይ ያለውም ወጣት አንብቦና መርምሮ ከመቀበል ይልቅ በስማ በለው የሚረጭለትን ተቀብሎ በመርጨት ሆኗል፡፡ ሳይቀበልም ይሁን ተቀብሎ ሲረጭ ቆም ብሎ አስቦና አሰላስሎ አይደለም፡፡ የተማረው ቁጥር እንደመጨመሩ የዚያኑ ያህል የተማረ ሥራ አጡም በርክቷል፡፡ ወጣቱ በወጣትነት ዕድሜውና ጉልበቱ አገሩን ቢያገለግል መልካም ነበር፡፡ አገርን ለማገልገል ደግሞ የግድ ተቀጣሪ መሆንም አያስፈልግም ነበር፡፡ ተሰጥቶ በሚያልፍ መልሰን በማናገኘው ጊዜ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በብዙ አቅጣጫ በተማርነው ሙያም ይሁን በሌላ በማንበብና ያነበብነውን በማስተዋል ብዙ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር በተቻለን ነበር፡፡ ፖለቲካውንም ቢሆን ከሚነገረን ይልቅ አንብበን በመመርመር የሚጠቅምና የሚጎዳውን በለየን ነበር፡፡ የሚያፋጀንንና የሚያባላንን ትተን አገርን ከፍ ከፍ ወደሚያደርግ ድርጊት በተሰማራን ነበር፡፡ ጥበብም ይሁን ዕድገት በግለኞች አልተገኘም፡፡ እኛ ግን የግለኝነት አባዜ ተጠናውቶን የኔ የኔ እንጂ የእኛ የእኛ ማለትን እርግፍ አድርገን የተውነው እስኪመስል ይስተዋላል፡፡

በቋንቋችን ራሳችንን ሸጉጠን የከሌ ቋንቋ ተናጋሪና የከሌ ቋንቋ ተናጋሪ ተጋጩ ቢባል የግጭቱን መንስዔ አውቆ ለማስታወቅ ሳይሆን፣ ምክንያቱንም ለማወቅ ትንሽ እንኳን ጥረት ሳናደርግ የቋንቋ ወገንተኛ ሆነን መካረሩን እናባብሳለን፡፡ ግጭቱንም አስፍተን አስፍተን ፖለቲካዊ እናደርገዋለን፡፡ ይህ የዚህ የ27 ዓመት ንፋቃዊ የቋንቋ ፖለቲካ የዘራውና የተገኘው ፍሬ ነው፡፡ እኔም ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በምንመረቅበት ዓመት ያውም በሁለተኛው ተርም እኔ ከምናገረው ቋንቋ ሌላ የራሱ አፍ መፍቻ ቋንቋ ተናጋሪ ለብዙ ዓመታት አብረን በአንድ ክፍል የተማርን ተጋጨን፣ ወጣትነት እልኸኝነት ያጠቃዋልና ግጭቱን አከረርነው፡፡ ከውጭ የተደባደብነው አልበቃ ብሎን የመኖሪያ ቤታችን በተለምዶ ዶርም የምንለው ፊት ለፊት ነበርና እዚያም ደግሞ ነው ይህ ሁኔታ አግባብ እንዳልሆነ የተረዱ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ የክፍል ጓደኞቻችን ሽምግልና ገብተው ይቅር ለፈጣሪ ተባባሉ ብለው  አስታርቀውናል፡፡ ይህ ድርጊት በዚህ በሕወሓት መራሹ የቋንቋ ፖለቲካ ቢሆን ኖሮ ሽማግሌ ሆነው ያስታረቁን ጭምር የቋንቋ ወገንተኛ በመሆን ወደ ከፋ ብጥብጥ ውስጥ በተገባ ነበር፡፡ አሁን ላይ የቋንቋ ወገንተኝነት ለምን ነገሠ? ቋንቋ ለቋንቋ በዳይና ተበዳይነት የመጣው እኔኑ ምሳሌ ያደረግኩት ከ1980ዎቹ በፊት ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ቋንቋ እንደ መደብ መለያ ሆነ፡፡ ነገር ግን ቋንቋዎች ከ1983 በፊት ነበሩ በኋላም አሉ፡፡ የጥልና የቁርሾ መነሻ ግን ሊሆኑ የቻሉት ከዘመነ ሕወሓት የአገዛዝ ጅማሮ ጋር ስለምን ተጣመረ? በእውነት በዳይ የሆነ ቋንቋ ተበዳይ የሆነውን ቋንቋ ጨቁኖና አፍኖ ስለያዘው ነበር? በሕወሓት የቋንቋ ፖለቲካ ጊዜ እኔ የግጭት ገጠመኜን የጠቀስኩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለብዙ ጊዜ ቋንቋን መሠረት ባደረገ መልኩ ስሙ የሚነሳ ነው፡፡ ቅድመ 1980ዎቹ የሌለበትን መገለጫ ድህረ 1980ዎቹ ለምን የቋንቋ ግጭት እንደ ታርጋ መገለጫው ሆነ?

እናትና አባት ለልጆቻቸው የበጎ ሥነ ምግባር አርአያ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በእውቀት የሚወልዷቸውን ምሩቃን፣ በተማሩት ሙያ ሥነ ምግባርን ጠብቀው ሕዝብን እንዲያገለግሉ አርአያ መሆን ሲገባቸው፣ ሙሰኛውና አባካኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሆኖ እያለ እንደምን ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጠበቁ ይሆናሉ? የፌዴራል መንግሥት ኦዲት ጽሕፈት ቤት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኦዲት ግኝቱን ለተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመንግሥትን ሕግና መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር አባክኗል ሲል ለመድረክ ፍጆታ ሲባል በፓርላማ አባላቱ እምቧ ከረዩ ይባላል፡፡ እንዴት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  እንዲህ ዓይነት ድርጊት ይደረጋል? የሚለውን አስተያየት በቴሌቪዥን መስኮት ለሕዝብ ይታይና የማስተካከያ ዕርምጃ ይደረግ ተብሎ አስተያየት ከመስጠት ባለፈ ማስተካከያ መደረግ አለመደረጉ በድጋሚ ሳይገለጽ ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም›› እንደሚባለው ይሆናል፡፡ የበላይ ኃላፊዎችም ከወንበራቸው አይነቃነቁም፡፡ የደሃው ሕዝብ የግብር ገንዘብም ውኃ በልቶት ይቀራል፡፡ ግፋ ቢል ዘወር ይደረጉ ከተባለ በተሻለ ሹመት ወደ ሌላ ይወሰዱና ሌላ ወንበር ይሰጣቸዋል፡፡ የሌባ ልጅ ሌባ ቢሆን እንደማይደንቅ ሁሉ ከእንደነዚህ ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ባለሙያዎች ሙሰኛ ቢሆኑ ይፈረድባቸው ይሆን? ልብ በሉልኝ ሁሉም ሙሰኛ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ ሙሰኝነት ኃጢአት መሆኑ በየትኛውም እምነት ይወገዛል፤ ግን እነሱን ያመረተው የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሕዝብን ሀብት አባክኗል ተብሎ ለሕዝብ ሲገለጽ የሰማ ባለሙያተኛ ምን ዓይነት ሥነ ልቦና ይዞ ወደ ሥራ ይሰማራል?

የቋንቋ መር ፖለቲካ አራማጁ ሕወሓት ከወጣበት ከአገዛዝ ከፍታ አውርጀዋለሁ የሚለው የለውጥ አራማጅ ፖለቲከኛ፣ ቋንቋ መር የሆነውን የታችኛው መዋቅር እንኳን ሊያፈርሰው ሊነካውም ያሰበ አይመስልም፡፡ በዚህ የአንድ ዓመት ቆይታው መግፋትን አናራምድም ሲባል ይደምጣል፡፡ በአሸዋ ላይ የቆመ መሠረት ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፖለቲካም እንዲሁ ሊታሰብ ይችላል፡፡ አንዱን ፈላጭ ቆራጭ ቋንቋ መር ፖለቲካ ዝቅ በማድረግ፣ ሌላውን ቋንቋ መር ፖለቲካ ከፍ ማድረግ ከሆነ አበው እንደሚሉት ‹‹አልሸሹም ዘወር አሉ›› እንደሚባለው ነው፤ ወይም የ1966 የተማሪ ንቅናቄ እንደሚሉት ‹‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም ዓይነት ይሆናል፡፡ በመግባቢያዬ እንዳልኩትም አሻግረው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ወዴት እንደሚወስዷት ገና ብዥታ ላይ ነን፡፡ በሚምሉትና በሚገዘቱት እንመናቸው? ስንል አንዳንድ ምልክቶች እንዳናምን ያደርጉናል፡፡ ፖለቲከኛስ በሚናገረው፣ በሚምለውና በሚገዘተው ፀንቶ ይቀጥላል? ስንልም ፖለቲካ እንደየወቅቱ ተለዋዋጭ ነው እያሉ ባሉን  ሳይገኙ፣ በማሉልን ሳይፀኑ ስናገኛቸው እምነታችን ይሸረሽራል፡፡ ፖለቲከኝነት ይሁንታ እንጂ ይሉኝታ ሲያጣብን ውኃ እንደመዝገን ይሆንብናል፡፡

የሽግግር መሥመር ቀያሹ መንግሥት በምሁራን የሐሳብ ልዕልና እንመራ፤ በጉልበት ሳይሆን በሐሳብ  አሸናፊነት፣ በጡንቻ ሳይሆን በጭንቅላት፣ በጥይት ሳይሆን በብዕር፣ በአፈሙዝ ሳይሆን በአፍ እንድንሸናነፍ ይተርኩልናል፡፡ ዕውነታው ይህ ከሆነ ሳንቆስል፣ ሳንደማ፣ ሳንገዳደል፣ በአሸናፊ ሐሳብ በሕዝብ ይሁንታ እንመራ፡፡ በጠባብነት ሳይሆን በአቃፊነት፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር እንኑር፣ ፖለቲካውም አግላይ ሳይሆን አካታች፣ ነቃፊ ሳይሆን አቃፊ፣ በዳይ ሳይሆን ለተበዳይ የቆመ ይሁን፡፡ አገራችንን ሰላም ያድርግልን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles