“ሆቴሌ ውስጥ ሆነው ነፍሳቸው የተረፈላቸው 1268 ሰዎች ከሞት ሊተርፉ የቻሉት በቃላት ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የነዚህን ሰዎች ሕይወት ያተረፈው ገንዘብ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታትም አይደለም፡፡ ወደ አረመኔዎቹ ሰዎች ይወረወሩ የነበሩ ቃላት ናቸው መድኅን የሆኑት፡፡ ቃላት በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡” እነዚህን ሐረገ ሐሳባት የያዘው አንቀጽ የተገኘው በቅርቡ የኅጽመት ብርሃን ያየው “የመንጋ ፍትህ መዘዝ” የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡
`An Ordinary Man` በሚል በፖል ሩሴሳባቢጊና የተጻፈውን “እውነተኛ ግለ ታሪክ” ወደ አማርኛ የመለሱት አቶ ጌታቸው አሻግሬ ናቸው፡፡ ይህ በአንድ ተራ ሩዋንዳዊ የሆቴል ሥራ አስኪያጅ የተጻፈው መጽሐፍ በሩዋንዳ ስለተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ የሚያወሳ ነው፡፡
ተርጓሚው ታሪኩን ለመተርጐም ከፍተኛ መነሳሳት የፈጠረባቸውን ሁኔታ በመቅድማቸው የገለጹት፡ “ኢትዮጵያዊ ወገኔ በተለይም ተተኪው ወጣት ትውልድ ይህን መጽሐፍ ቢያነብ የመንጋ ፍትህ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ይበልጥ ይረዳል ብዬ በማሰብ ነው፤” በማለት ነው፡፡