ከጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጋር አያይዘው ክልላዊና አገር አቀፍ ፈተናዎችን አንፈትንም የሚሉ መምህራን ተጠያቂ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ በወቅታዊ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ፣ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚጀመረው ክልላዊና አገር አቀፍ ፈተናዎችና በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ፤ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፈተና ሒደት ከጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጋር እንደማይያያዝና ተማሪን ይዞ መብት መጠየቅ ተገቢ እንዳልሆነ፤ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ በዚህ ዙሪያ እንደማይደራደር፣ በየክልሉ ያሉ መምህራን ማኅበራት አቋማቸው ይኸው እንደሆነ በመግለጽም፤ መምህራን ምንም ዓይነት ጉዳት በማያስከትል መልኩ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ማሰማት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም አልተከበረም በሚል ሠልፍ የወጡ መምህራን፤ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ማንሳታቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህንን አስመልክተው አስተያየት የሰጡት ዶ/ር ዮሐንስ፣ በማኅበሩ ዕውቅናና ያለዕውቅና መምህራን ሠልፍ ወጥተዋል ብለዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ዮሐንስ፣ ማኅበሩ ደንብና ሥርዓት ያለውና በአስተዳደራዊ መዋቅር የሚመራ እንደመሆኑ፤ መምህራን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሥርዓቱን ተከትለው መሆን ይገባቸዋል፡፡ ያለማኅበሩ ዕውቅና የወጡት መምህራን ጥያቄያቸው ትክክል ቢሆንም፣ ማኅበሩ ለእነዚህ ዕውቅና አይሰጥም፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ተወካዮች በተገኙበት፣ በአማራ ክልል ምክር ቤት ተጠርቶ፣ ጉባዔ ተካሄዶና ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ውይይትና ክርክር ከተደረገ በኋላ ሰላማዊ ሠልፍ የወጡ መምህራን በማኅበሩ ዕውቅና አላቸው፡፡
የክልሉ መምህራን በሰላማዊ መንገድ ሐሳባቸውን መግለጻቸውንና ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን በማስታወስም፣ 11106 መምህራን ያህል 230 ሚሊዮን ብር የሦስተኛ ወገን ክፍያ እንዲከፈላቸው ክልሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ በአገሪቱ ከሚስተዋለው ለውጥና የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተያይዞ የሌሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ያከሉት ዶ/ር ዮሐንስ፣ ይህ ከማኅበሩ ደንብ እንደሚመነጭ፣ ማኅበሩ በ1985 ዓ.ም. በነበረ ውይይት ከፖለቲካ፣ ከጎሳ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ ልዩነቶች ነፃ ሆኖ በአንድ ማኅበር ጥላ ስር አሰባስቦ በትምህርት፣ በመምህራን መብት፣ በአገራዊ ልማት አንድ ሆኖ መምህራን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ስለመሆኑ ዕውቅና አግኝተዋል ብለዋል፡፡
አገሪቷ ከምታራምደው መድብለ ፓርቲ ሥርዓት የተነሳ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ መምህራን ደግሞ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡ የተለያየ አመለካከት መኖር መብት ቢሆንም፤ በፖለቲካ ክፍፍል ውስጥ መግባት ለሙያው አደገኛ ነው፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ እንደ ተቋም ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ሙያውን፣ ትምህርትን፣ ጥቅማ ጥቅም ላይ ይሠራል ተብሏል፡፡ ማኅበሩ፣ ከመንግሥት ልማት ውጭ መሆን ስለማይችል፣ በልማት ጉዳዮች ሥርዓት ዘርግቶ ከመንግሥት ጋር ይሠራል፡፡
ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ማኅበሩ፣ የመምህራንን መብትና ጥቅም፣ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅና ተሳትፎ እንዲጨምርና ከሙያ ማኅበሩ የሚጠበቁ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡