ሰላም! ሰላም! ከዚያም ከዚያም ተበዳድረው ልጃቸውን ዓረብ አገር የላኩ ጎረቤቴ ሰሞኑን ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሲሉ ሰነበቱ። የወለደ መቼስ ምን መቻያ አንጀት አለው? ምን በሁለት እግሩ ቆሞ ቢሄድ ልጅ ለአባት ለእናቱ ያው ምን ጊዜም ልጅ ነው። ‹‹ተው እርስዎ አይጨነቁ የወሰዳት መንገድ መልሶ በሰላም ያመጣታል፤›› ‹‹ስላቸው እሱ ለተረት ነው የሚሰምረው፡፡ የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ የሚባልለት መንገድ በነገሥታት አገር ፍቺው ሌላ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉኝ፣ በምርጫ ያልነገሡ ነገሥታት የሚመሩዋት አገር ውስጥ በመኖሬ ፈጣሪዬን ‹‹አመሠገንኩ››። ምሥጋና ማንን ገደለ? እኔ በኋላ የለሁበትም። እነ እከሌ የወደቁበትን፣ እነ እከሌ በእነ እንትና በኩል እንኳ ሄደው ያላስጨረሱትን፣ ይኼን ያህል ጉቦ እኔ ራሴ ከፍዬ ‘ኒል’ የወጣሁበትን መንገድ አሁን አንተ ማን ሆነህ ነው የምሥጋና ምንጣፍ የምታስነጥፍበት? ለሚሉኝ ተችዎች መልሴ ራዕይ ስላለኝ የሚል ነው። ቢያንስ ቢያንስ ራዕይ አልባ አለመሆኔ ይታወቅ ለማለት ያህል ነው፡፡
በረባ ባረባው አመዳችን ቡን እንዳለ በየአቅጣጫው እንደ ስደተኛ ሕዝብ መበተን አያሳዝንም ወይ? አንድ ወዳጄ በቀደም፣ ‹‹ቆይ ግን እኛ መቼ ነው ወጉ ደርሶን ስደተኛ ጠርዘን የምናባርርበት ቀን የሚመጣው?›› ሲለኝ ነበር። እሱ ‹ብድር በምድር› በሚለው ሥሌት ስለሚኖር ነው እንዲህ የሚለው። እኔ ግን ሐሳቡ የተመቸኝ የዛሬ ማየት ትተን የነገን እያሰብን በአገራችን ኑሮ፣ የሰው አገር ሰው ልብ የምናሸፍትበት ቀን እንዲመጣ ነበር። ዳሩ ባለ ራዕዩ መሆን የሚገባው መስጠም እየፈራ ሥራው ሁሉ ወሬና ስደት ሆኗል። ስንቱን ትልቅ ሐሳብና ራዕይ ይዘው መስጠም እየፈሩ፣ ባህሩንና ወጀቡን በጉንጭ አልፋ ዲስኩር ሰግተው ለትውልድ የሚጠቅም ታላላቅ ውጥንና አጀንዳ ገና ሳይጀምሩት ትተውት፣ ባህር የበላቸውን ቆጥራችሁ ታውቃላችሁ ግን? ምኑን ይቆጠራል አትሉኝም? አሁንም ስደት ያምረናል እንዴ?
መቼም ሰውና ምድሩ ሲነሳ ጨዋታ ብዙ ነው። ሰውን ሰው አላነሳው አለ እንጂ፣ ጨዋታውስ ወሬ የሚባለው ቤንዚን እያለለት አልቀዘቀዘብንም። ታዲያ በዚህ በዓረብ አገር የሚኖሩ የአገራችን ልጆች ጉዳይ ጨዋታ አንስተን እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የስደት ዋነኛው ምክንያት ምንድነው?›› ብዬ ጠየቅኩት፡፡ “መጨካከን ነዋ። አለመረዳዳታችን ሁሉንም በየፊናው መፍትሔ ፈላጊ አደረገው፤” አለኝ። እንዲያው ግን እንዲህ የሰው መጨካከን አይገርማችሁም? የባሻዬ ልጅ፣ “ምን ታደርገዋለህ? የወረት ዘመን ስለሆነ እኮ ነው፤” ብሎ ጨመረልኝ። ወረት ቢል በቀደም ዕለት የሆንኩትን ላጫውታችሁ። ከመቼው ተጋብተው ከመቼው እንደተፋቱ አላውቅም፣ ሁለት ባልና ሚስት ንብረት እኩል ለመካፈል ቤት ይሸጣሉ። እንግዲህ አሻሻጩ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት መሆኑ ነው። ዘንድሮ ምን የማይሸጥ ምን የማይገዛ ነገር አለ አትበሉኝ ብቻ፡፡
ይቅርታ አድርጉልኝ ስላቋረጥኩ፡፡ የዘንድሮ ፍቅርና የቴሌ ኔትወርክ ግን መንታ እህትማማቾች አይመስሉም? ደርሰው ምጥት ደርሰው ሂድት ሲሉ? አቤት ደግሞ ቤቱን ብታዩት? እዚያ ነበር ተወልዶ አድጎ አርጅቶ መሞት ያስብላል እኮ! የአብዛኞቻችን ኑሮ አንድ ቤት ውስጥ ተወልዶ እስከ ማርጀት ስለሆነ ብዬ ነው፡፡ እናማ በምታውቁት ፍጥነት ታ! ታ! ታ! አድርጌ ቱጃር ነጋዴ ቤት ፈላጊ አገኘሁ። መቼም ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነው፡፡ ምንም እንኳ የእኛ አገር ‘ኔትወርክ’ ‘ፎርሜሽን’ እስካሁን ባይታወቅም፡፡ እናማ ቤቱን ከመግዛቱ በፊትና ሰዎቹን ከማነጋገሩ አስቀድሞ፣ “ለመሆኑ በሰላም ነው ይህን የመሰለ ቤት ሰዎቹ የሚሸጡት? መቼም በዚህ ዘመን ከዚህ የተሻለ ቤት ልሥራ ማለት የሚታሰብ አይሆንም…” አለኝ። እኔም፣ “የለም በሰላም እንኳ አይደለም፡፡ ፍቺ ላይ ስለሆኑ ነው፤” ብዬ ዓይን ዓይኑን አየሁት። በቃ የማንፈራው የለም እኮ እኛ ደላሎች፡፡ ‘ደግሞ የፍቺ ቤት ገዝቼ ነገ እኔስ ብፋታ?’ እንዳይለኝ ሠግቼ እኮ ነው ዓይን ዓይኑን የማየው፡፡ ምን ይታወቃል? እሱም ከሚስቱ ጋር አልጋ ለይቶ ወረቀት ሳይቀድ የሚኖር አጭልግ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይ ጉድ አጉል ልማድና አስተሳሰብ እንኳን በገንዘብ መቼ በበረኪና ለቀቀ ብላችሁ ነው፡፡ ኧረ ተውኝማ!
ስለምን ነበር የምንጫወተው? አዎ! ስለወረት! የሳምንት ፍቅር፣ የሳምንት ኩርፊያ፣ የሳምንት ጓደኝነት፣ ወር የማይቆይ ሹመት፣ ዓመት የማይቆይ ሽረት፣ አንድም ቀን የማይተገበር መርህ፣ በተግባር የማይታይ ስብከት። ኧረ ምኑ ቅጡ? ወረት! ወረት! ወረት! በአንድ ወገን የጓዳችን ወረት አልብቃቃ ሲለን በአንድ ቀን ወረት እያሳሳመ ሲያናክሰን ኑሮን እንደ ቀልድ፣ ዕድሜን እንደ ቀላል ይኼው እንገፋዋለን። ‘መኖር ደጉ ብዙ ያሳያል’ ተብሎም አይደል? እናማ እንዲህ እያሰብኩ ሳላውቀው ይኼን ሁለት ቀን ‘ወረተኛ ነሽ አታዋጭኝም’ የሚለው ዜማ ከአፌ አልጠፋ ብሎ ነበር፡፡ እህሳ? ማንጠግቦሽ ጆሮ ደርሶ እርፍ፡፡ ያው እንደምታውቋት፣ “ምነው ሐሳብን ፊት ለፊት የመግለጽ መብት በተከበረበት ዘመን ጥግ ጥጉን ያዞርሃል?” ብላኝ ቁጭ፡፡ እንዲህ የአንጎራጎርነውና የተነፈስነው ሁሉ ፖለቲካ ነው እየተባለ እንዴት መኖር እንደምችል ስታስቡት አያማችሁም ታዲያ? አቤት ዘንድሮ አባብለን ተናግረን እንዲህ ከተባልን፣ ዴሞክራሲ አለ ብለን የልባችንን ብዘረግፍ ጉድ ነበር የሚታየው፡፡ ጉድ ነው ዘንድሮ!
ያልኳችሁን ቪላ አዋክቤ ካሻሸጥኩ በኋላ ‘ኮሚሽኔን’ ስቀበል ሆዴ ሲጮህ ሰማሁ፡፡ ነገር ስበላ ምግብ አለመብላቴን ረስቻለሁ፡፡ ከረሱ ይረሳል ሆድም ሆነ አገርም ቢሆን፡፡ ወደ ቤቴ ልሄድ ስል የባሻዬ ልጅ ደወለ፡፡ “እህ?” ስለው፣ “ምሳ እየበላን የማዋይህ ነገር አለ ቶሎ ድረስ፤” አለኝ፡፡ ወደ ፒያሳ ገሰገስኩ፡፡ እንዳየኝ ጠኔ እንደጠናብኝ ከፊቴ አንብቦ (አቤት የሰው ኪስና ሆድ እንደምናነበው ልብም ማንበብ ብንችል መቼም ተላልቀናል እስካሁን) “በል ቶሎ ወደ ሸራተን” አለኝ፡፡ ልቤ ተንሸራተተ! “ምን ልንሠራ?” ስለው፣ “ምሳ ልንበላ፤” አለኝ ከአፌ ነጥቆ፡፡ ‘ይኼ ሰውዬ ዛሬ ምሳዬን ሸራተን አብልቶ እስከ ሚቀጥለው ገቢ ያሉትን ሌሊቶች በሻማ እንዳከብርለት ይፈልጋል? ምነው ፈጣሪ አንድ ያለኝን ወዳጅ ሳዝንበት ዝም ባትል?’ እያልኩ ተከተልኩት፡፡ ጥቂት ሄደን የሆነ ምግብ ቤት ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ አስተናጋጁ፣ “እንኳን ወደ ሸራተን በሰላም መጡ፤” ሲለኝ ነፍሴ ገባች፡፡ ለስሙ ብቻ ክፈሉ ካልተባልን የእኔም የእሱም ምሳ እንደወረደ ከምንጠጣው የእግዜር ውኃ ጋር ከ80 ብር እንደማይበልጥ አወቅኩ፡፡ የደሃ አምላክ የት ሄዶ ያለግጦሽ መሬታችን እንሰማራና? አስተናጋጁ በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም አንድ ነን በሚል መንፈስ በቀልጠፋ መስተንግዶው ሲያረካኝ ሳየው ወደ ባሻዬ ልጅ ዘወር ብዬ፣ “ምናለበት የዴሞክራሲ ጠበቆች ነን የሚሉንም እንዲህ ለመርሐ ግብራቸው ዕውን መሆን ሲተጉ ብናይ?” ማለት። መቼም አፌ አያርፍ! “ከምርጫ በኋላ የመፈተኛቸው ጊዜ ሲደርስ እንደ ጴጥሮስ ባይከዱን ለማለት ፈልገህ ነው?” አለኝ፡፡ እሱም አፉ አያርፍ!
በሉ እስኪ እንሰነባበት! እኔና ምሁሩ የበሻዬ ልጅ ጊዜው አሁን ከሆነ እኛ ሳያልፍልን አልፎለት አምስት ብር የገባ በቆሎ እሸት እየበላን የእግር መንገድ እንጓዛለን (ይቅርታ ‘ዎክ’ እናደርጋለን ለማለት ነው፡፡ እስካሁን በደረቅ አማርኛ-እንግሊዝኛ ያስራብኳችሁ አይበቃም?) ዶፉ ዝናብ አልፎ ወደየቤቱ የሚቻኮለውን ሕዝብ እያየን ወሬ ጀመርን፡፡ “አንበርብር? እውነት ግን እንደዚህ ሕዝቧ ተጠቃሚ ያልሆነባት አገር ዓለም ላይ የቷ ናት?” ብሎኝ ዕርምጃውን ገታ አድርጎ ቆመ፡፡ “ማለት?” አልኩት ጠጠር ያለው ጥያቄው እንዳሰኘኝ መልስ ለመስጠት አላመች ብሎኝ፡፡ “በቃ! የወጠነችውን እንዳይሳካ በውስጥም በውጭም ሴራ ሲጎነጎንላት፣ ትንሽ ትልቁ ከፍ ስትል ሊያወርዳት አበሳውን ሲያይ፣ ጠቀምኩሽ ብሎ ያልጎዳት፣ እኔ ነኝ የማውቅልሽ ብሎ ያልገደላት ማን ነው? አቤት! ስንቱን ያለፈ ብርቱ ሕዝብ መሰለህ ይህ ሕዝብ?” ብሎኝ በሐሳብ የትና የት ተሰደደ፡፡ ወዲያው ደግሞ ምልስ ብሎ በንዴት እየተንቀጠቀጠ፣ “የእስካሁኑ ይበቃል፡፡ ከዚህ በኋላ ማንም በሕዝብ ስም እንዲቀልድ፣ በሕዝብና በአገር ሀብት እንዲደላደል አንፈቅድም፡፡ ማንም!” ብሎኝ እንዳፈጠጠ ቀረብኝ፡፡
እኔም ምንም እንኳ ስሜታዊ ቢሆንም የተናገረው እውነት ስለነበር፣ “አዎ የእስካሁኑ ይብቃ!” ብዬ መለስኩለት፡፡ ፉከራዬ የወረት እንዳይሆን እየተጠራጠርኩ፡፡ ካልንስ ‘የወረት ዘመን ይብቃ!’ ነበር፡፡ ከባሻዬ ልጅ ጋር ተለያይተን ወደ ቤቴ ስጓዝ ራሴን ታዝቤ በራሴም አፍሬ እግሬ መራመድ አቃተው፡፡ ቆይ ግን ከማዋየው ሰው ሁሉ ጋር ነው በመፈክር የምለያየው ብዬ ራሴን ጠየቅኩት፡፡ ስንቱን ርዕሰ ጉዳይ በእኛ ይብቃ፣ እስከ መቼ፣ መጥኔና የመሳሰለውን እያልኩ የዘጋሁት ጨዋታ እየታወሰኝ ደግሞ በሌላ በኩል ትንሽ እንኳ ፈቀቅ ያለውን የተሻሻለውን ነገር ሳነፃፅረው ሰማይና ምድር ሆነብኝ፡፡ ከትናንት ወዲያ አንስተን የጣልነው የስደትና የተፈናቃይ ነገር በነገር ተጣሞና በሕገወጥ ደላላ ተደምድሞ ፀጥ ይባልና ደግሞ ቀን ቆጥሮ መልኩን ቀይሮ ይነሳል፡፡ ዴሞክራሲና ድራማውም እንዲያ፡፡ የአገር ሰላም ዕጦት በአክራሪ ብሔርተኝነት ጥፍጥሬ እየተሟሸ፣ ሌላ አምባገነንነት ይጋገርና እዬዬ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላውም ሌላ ይሆናል፡፡ እና ዛሬ ጥያቄዬ አንድ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ወረት አገሩ ወዴት ነው? ወረት ላይ ሆኖ ዕውን የሚሰማን አለ? የወረት ተረኞች ሆድ አታስብሱን ማለት የለብንም? እስኪ እናንተም ተጠያየቁ፡፡ እኛም እንጠያየቅ፡፡ ካልተጠያየቅን መልስ ከየት ይመጣል? መልካም ሰንበት!