Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለፊስቱላ ተጠቂዎች ተስፋ

ለፊስቱላ ተጠቂዎች ተስፋ

ቀን:

ዕድገቷ ደቡብ ክልል ሜሎ በተባለች ገጠራማ አካባቢ ነው፡፡ ከወላጆቿ ጋር የማደግ ዕድሉ አልገጠማትምና ያደገችው ከአያቷ ቤት ነበር፡፡ አባቷ ከሜሎ ወጣ ብላ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ላይ እንደሚኖር በሰማች ጊዜ ጓዟን ሸክፋ ይኖርበታል ወደ ተባለው አካባቢ አቀናች፡፡ ኑሮ በአባቷ ቤት እንዳሰበችው አልነበረም፡፡ ሕይወቷን አደጋ ላይ የጣለው አጋጣሚ የተከሰተው እንግድነቷን እንኳ ሳትጨርስ በቀናት ውስጥ ነበር፡፡

የቅርብ ዘመድ እንደሆነ የምትናገረው ግለሰብ በ13 ዓመቷ ሀና (ስሟ ተቀይሯል) ላይ ዓይኑን የጣለው እንደ መጣች ነበር፡፡ እሱም እንግዳ ስለነበር ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የሚፈጥር ነገር አላሳየም፡፡ የተመቻቸ አጋጣሚ እስኪፈጠርለትም አንዳችም የተለየ ነገር ሳያደርግ ቆየ፡፡ አንድ ቀን ባዶ ቤት ውስጥ ያገኛታል፡፡ ጊዜ ሳያጠፋ ሀናን ጠልፏት ወደ ሚኖርበት ገጠር ፈረጠጠ፡፡

የመጀመሪያ ሚስቱን በሞት የተነጠቀው ጎልማሳ የ13 ዓመቷን ታዳጊ ጠልፎ እንደወሰዳት ነበር የደፈራትና የፀነሰችው፡፡ የሃና ማርገዝ በሕግ እንዳይጠየቅ፣ ወደ ቤተሰቦቿ እንዳትመለስ ሚስቱ ሆና እንድትቆይ ቀብድ ስለሆነው፤ እንደ ባለትዳር አብረው ይኖሩ ጀመሩ፡፡ ሀና ማርገዟን ያወቀችው ሆዷ መግፋት ሲጀምር ነበር፡፡

ምዕተ ዓመቱን ለመቀበል ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽር ጉድ ሲል፣ የተለያዩ ካርኒቫሎች ሲዘጋጁ፣ ኅብረ ዝማሬዎች ሲደመጡ ምድር ሸብረብ በምትልበት በሚሊኒየም መግቢያ ወቅት ሀና እንደ ፍጥርጥርሽ በተባለችበት የጨለማ ዓለም ውስጥ ከደፈራት ሰው ጋር በትዳር ለመኖር ተገደደች፡፡ እንደ ልጅ ተጫውታ ሳትጠግብ ማኅበረሰቡ ከሚስት የሚጠብቀውን እያደረገች ስትኖር ወራት ተቆጠሩ፡፡

ፅንሱም መወለጃው ደርሶ ምጥ ያፋፍማት ጀመር፡፡ በአቅራቢያው ሆስፒታል አልነበረምና ምታምጠው እዚያው ቤት ውስጥ ሆና ነበር፡፡ የልምድ አዋላጇ ሊያዋልዷት ሞከሩ፡፡ የሀና ምጥ ግን ብርቱ ነበረና እንደዋዛ መውለድ አልቻለችም፡፡ ከባዱ የምጥ ስቃይ ሀና ላይ ውሎ አደረ፡፡ ሁለተኛ ቀን ስታምጥ ውላ ራሷን ሳተች፡፡ በሦስተኛው ቀን ሕፃኑ ማህፀኗ ውስጥ ሞተ፡፡ ወደ ጤና ጣቢያ የወሰዷት ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ካማጠች በኋላ ነበር፡፡ ሁኔታው ከአቅም በላይ ስለነበር ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር ተደረገች፡፡ በወቅቱ ማህፀኗ በር ላይ ተቀርቅሮ የቀረውን ሕፃን ማውጣት ትልቁ ፈተና ነበር፡፡ ከአንደኛው ወደ ሌላኛው ሆስፒታል ካመላለሷት በኋላ የሞተው ልጅ ሊወጣላት ቻለ፡፡ ያልጠበቀችውና ሰምታው እንኳ የማታውቀው አደጋ ግን በዚያው አጋጣሚ አብሯት ቀረ፡፡ የሽንት ቱቦዋ በከፍተኛ መጠን ተጎድቶ ስለነበር ሀና ሽንቷን እንኳ መቆጣጠር የማትችል “ጉድ” ሆነች፡፡ ስለ ሀና ሁኔታ የሰሙ ሁሉ ከፊሉ አዝኖ ከፊሉ ደግሞ የሰማው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ እየሄደ ይጠይቃታል፡፡ “ባሏም” ብቻውን ማስታመም ስላልቻለ ወደ ወላጆቹ ቤት ወስዷት እዚያው ሆኖ ያስታምማት ያዘ፡፡

የሀና ሕመም ግን በጊዜ የሚሽር አልነበረም፡፡ ሽንቷን በላይዋ ላይ ትለቃለች ይህም የሚፈጥረው ጠረን ብዙዎችን የሚያርቅ ነበር፡፡ ጠያቂዎቿም አንድ ሁለት እያሉ እስከነ አካቴው ቀሩ፡፡ አስታማሚው ባሏም ገሸሽ አደረጋት፡፡ ይብስ ብሎም ሌላ አግብቶ ወለደ፡፡ ቤተሰቦቹም ምንተዳዬ ብለው ሀናን አውጥተው ጣሏት፡፡ ‹‹ቀንና ሌሊት ቁጭ ብሎ ማልቀስ ሆነ ሥራዬ፣ ሁሉ ነገር ጨለመብኝ፤›› የምትለው ሀና፣ ከሰው ተራ ያወጣት ሕመሟ እንዲድንላት ጥረት ጀመረች፡፡  

ያድኑኛል ብላ ያሰበቻቸውን ሆስፒታሎች በር ብታንኳኳም፣ ፈውስ ግን የማይታሰብ ሆነ፡፡ እንደ እሷ ያሉን አክሞ የሚያድን ራሱን የቻለ አንድ ተቋም አዲስ አበባ እንዳለ ስትሰማ ሐሳቧ ሁሉ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ሆነ፡፡ ነገር ግን ለትራንስፖርት የሚሆናት ሰባራ ሳንቲም እንኳን አልነበራትም፡፡ ሜዳ ወጥቶ ለመለመን፣ ለመሥረቅም አልቃጣትም፡፡

በዝና ወደ ማያውቋት አካባቢ ሄዳ ለትራንስፖርት የሚሆናትን ለማግኘት የቤት ሠራተኛ ሆና ተቀጠረች፡፡ ቀጣሪዋ ጠዋት ወጥተው ምሽት የሚመለሱ በመሆናቸው ስለሀና የቀን ውሎ ወይም አጠቃላይ ሁኔታ የሚያውቁት የለም፡፡ ሀናም ከመምጣታቸው በፊት በሽንት የበሰበሰ ልብሷን ቀይራና አጣጥባ ስለምትጠብቃቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ መልኩ ለአራት ወራት ከሠራች በኋላ አዲስ አበባ ለመምጣት የምትችልበትን የትራንስፖርትና ሌሎችም ወጪዎች የምትሸፍንበት 2000 ብር አገኘት፡፡ ጊዜ ሳታጠፋም አዲስ አበባ ከተፍ አለች፡፡ ሀና እንደ እሷ ላሉ ማኅበረሰቡ ለገፋቸው እንስቶች የተስፋ ምድር ወደ ሆነው ሀምሊን የፌስቱላ ሕክምና ማዕከል የገባችው በጥር 2011 ዓ.ም. ላይ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ሕክምናዋንም አልጋ ይዛ እየተከታተለች ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ የሚፀየፋት የለም፣ የሚያሳስባት ጠረንም የላትም፡፡ ታሪኳን ሰምቶ የሚታዘባትም የለም፡፡ በአራት ረድፍ በተደረደሩት አልጋዎች ላይ ተኝተው የሚታከሙት በሙሉ እንደ እሷ ያሉ የፌስቱላ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ በማዕከሉ ሦስት የሕሙማን ማረፊያ ክፍሎች አሉ፡፡

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕክምናውን ፈልገው የመጡ ሕሙማን በማዕከሉ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ  እንደ ሀና በተራዘመ ምጥ ምክንያት ለፌስቱላ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ቤት ውስጥ የሚወልዱ እናቶች እስከ አራት ቀን የሚቆይ ብርቱ ምጥ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የሚናገሩት የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አስቻለው ታደሰ ‹‹እዚህ የሚመጡት ከሞት የተረፉ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡

በማዕከሉ እንደ ሀና ያሉ 100 የሚሆኑ ታካሚዎች ይገኛሉ፡፡ እንደ ጉዳታቸው መጠን ሕክምናቸው የሚወስደው  ጊዜ ይለያያል፡፡ የደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል ቢሆን ሕክምናው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ከማዕከሉ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ የደረሰው ጉዳት ከበድ ያለ ከሆነ ግን ሕክምናው ከዓመት የዘለለ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ‹‹የፌስቱላ ችግር በጣም በቀላል ሕክምና ሊድን የሚችል ነው፡፡ የቀዶ ሕክምናው ከሌሎቹ የቀዶ ሕክምናዎች በተለየ ሁኔታ 80 በመቶ ስኬት አለው፡፡ ትልቁ ችግር የሚደርሰው በታማሚዎች ሥነ ልቦና ላይ ነው፤›› የሚሉት አቶ አስቻለው ናቸው፡፡

ፈስ አመለጠኝ ብሎ ራሱን እስከ ማጥፋት በሚደርስ ወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ ውስጥ ሽንት መቆጣጠር አለመቻል የውርደት መጨረሻና ከማኅበረሰቡ የሚነጥል ‹‹የእግዜር ቁጣ፤›› ሆኖ ይታያል፡፡ ፌስቱላ ያጋጠማት አንዲት እናት ከሕመሙ ይልቅ የሰዎች መጠቋቆሚያ መሆኗ ይበልጡኑ ያማታል፡፡ በፌስቱላ ምክንያት ትዳሯ መበተኑ፣ ቤተሰቧ ስሙ መጥፋቱ እርጥቡ ቀሚሷ ዝነኛ መሆኑ የማይሻር የሥነ ልቦና ጠባሳ ይጥልባታል፡፡ በአካባቢው ብቸኛዋ የፌስቱላ ታማሚ ስለምትሆን ጭንቀቷን የሚጋራት አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ ታክሞ እንደሚድን ስለማይታሰብም ፌስቱላን የዘለዓለም ሕመም አድርጎ የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ስለዚህም ብዙዎች የሕክምናውን መኖር ባለማወቅ ለዓመታት ከማኅበረሰቡ ከሚነጥላቸው ፌስቱላ ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡

‹‹በ20 ዓመቷ ፌስቱላ የተከሰተባት በ60 ዓመቷ እዚህ መጥታ ታክማለች፡፡ አብዛኞቹም ከ10 እስከ 15 ዓመት ድረስ ሳይታከሙ ይቆያሉ፡፡ አሁን ግን እንደ በፊቱ አይደለም፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በየቀበሌው ስለገቡ እንደበፊቱ ሳይቆዩ መረጃው ይደርሳቸዋል፤›› ይላሉ አቶ አስቻለው፡፡

ከያሉበት ጥግ መጥተው በሃምሊን ማዕከል የሚገቡት፣ ወደየመጡበት እስኪመለሱ ክትትልና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ በሃምሊን አንዲት እናት ሽንቷን መቆጣጠር አለመቻሏ ትዝብት ላይ አይጥላትም፣ እሷም አታፍርበትም፡፡ በቀላል ሕክምና ታክሞ የሚድን ዕክል መሆኑን ታውቃለች፡፡ ከጎኗ ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ ድነው ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ታያለች፡፡ ሕመምተኞቹን የሚንከባከቡት አብዛኞቹ ነርሶችም ከዓመታት በፊት በፌስቱላ ሲሰቃዩ የነበሩ ሴቶች ናቸውና የመዳን ተስፋቸው በቅርብ ዕውን የሚሆን እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ የሴቷን ውስጠ ሚስጥር የሚያውቁት ነርሶቹ አልጋዋ ሽታ እንዳይፈጥር ቁስሏ እንዳያመረቅዝ ደከመኝ ሳይሉ ይንከባከቧታል፡፡

የነርሶቹ ኃላፊ ሲስተር ውዴ ፋንታውን በማዕከሉ ለመሥራት ፍላጎት ስላላቸው ከመንግሥት ሆስፒታል ወጥተው በማዕከሉ ከተቀጠሩ 13 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

እንደ ሌሎቹ ነርሶች የፌስቱላ ታሪክ ባይኖራቸውም አዋላጅ ነርስ ሆነው በመንግሥት ሆስፒታል ሠርተዋልና በፌስቱላ ስለሚሰቃዩ ሴቶች ብዙ ያውቃሉ፡፡ ችግሩ ይበዛበት በነበረው በአማራ ክልል በየቀኑ ወደ ሆስፒታል ከሚሄዱ እናቶች መካከል የተወሰኑት በፌስቱላ የሚሰቃዩ እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ በሀምሊን የፌስቱላ ማዕከል የማገልገል ፍላጎት ያደረባቸውም ያኔ ነው፡፡ በማዕከሉ የመሥራት ፍላጎታቸውንም ያሳዩት መጀመሪያ ያለ ደመወዝ በነፃ በማገልገል እንደሆነ  ይናገራሉ፡፡

‹‹በመንግሥት ቤት በምሠራበት ወቅት በቂ የአዋላጅ ነርሶች፣ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ቁጥር ያነሰ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ኅብረተሰቡ በቂ የሥነ ተዋልዶ ጤና ዕውቀት አልነበረውም፡፡ እናቶች ምጥ ሲይዛቸው ፈጥነው ወደ ሆስፒታል ያለመሄድ ችግር ስለነበር፣ ለፌስቱላ የመጋለጥ ሰፊ ዕድል ነበር፡፡ ከአንዱ ወደ ሌላው ሆስፒታል ሪፈር ሲደረጉ ከሚያጋጥም መጉላላት በተጨማሪ የሕክምና ወጪያቸውን  ለመሸፈን ይቸገሩ እንደነበር ታዝቤያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ብዙዎች ተሻሽለዋል፡፡ የሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ የእናቶች ሕክምናም ነፃ መሆኑ ትልቅ ዕፎይታ ሆኗል፡፡ በፌስቱላ ለሚሰቃዩ እናቶች ደግሞ በአምስት የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፉን ከፍቶ እየሠራ ያለው የሀምሊን ማዕከል ተገን ሆኗል፡፡

ማዕከሉ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በወሊድ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው እናቶች ላይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የፌስቱላ ችግር ያጋጠማቸው ዜጎች የማዕከሉን በር ያንኳኳሉ፡፡ የፌስቱላ ችግር ኖሮባቸው የሚፈጠሩ ወንዶችም ሴቶችም ዕርዳታቸውን ለመጠየቅ ወደ ሃምሊን ጎራ ይላሉ፡፡ የሽንት ፊኛቸው ከውጭ ክፍት ሆኖ የተወለዱ፣ ዓይነ ምድራቸው የሚወጣበት ክፍተት ድፍን ሆኖ የተወለዱ እንዲሁ መፍትሔ ፍለጋ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ብልታቸው ዝግ ሆኖ የተፈጠሩ ልጃገረዶችም የሕክምና ዕርዳታ ፍለጋ ወደ ሀምሊን ይሄዳሉ፡፡ በከባድ ምጥ የወለዱ አንዳንድ እናቶች ብልታቸው ላይ ጠባሳ ይፈጠራል፡፡ ይህ ጠባሳ ብልታቸውን እስከ መዝጋት እንደሚደርስ፣ እንዲህ ያለ ችግር ያጋጠማቸው እናቶችም በሀምሊን የሕክምና ዕርዳታ እንደሚያገኙ ሲስተር ውዴ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሆስፒታል ሄደው በጤና ባለሙያዎች ዕገዛ ወልደውም የዓይነ ምድር መውጫቸው ላይ የመተርተር አደጋ አጋጥሟቸው ሰገራ የሚያመልጣቸው በብዛት እየመጡ ነው፡፡ ልጃቸውን በቀዶ ሕክምና የተገላገሉም ሳይቀሩ ሽንት እየፈሰሳቸው ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ የማህፀን ዕጢ የወጣላቸው እናቶችም ሽንት የመፍሰስ ችግር እያጋጠማቸው ወደ እኛ እየመጡ ነው፤›› የሚሉት ሲስተሯ፣ ማዕከሉ ከወንዶች በስተቀር የተለያዩ የፊስቱላ ችግር የተከሰተባቸው ሴቶችን ተቀብሎ እያስተናገደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ለፊስቱላ የተጋለጡ ወንዶች ሴቶችን ብቻ ወደ ሚያገለግለው ሐምሊን ተደብቀው ይሄዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ በአባላዘር በሽታዎች ምክንያት ሽንት መቆጣጠር የተሳናቸውና ባህላዊ ሕክምና ሞክረው በጎንዮሽ ጉዳቱ በእጅጉ የቆሰሉም ናቸው፡፡ ‹‹አንድም ወንድ አክመን አናውቅም፡፡ የከፉ ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት በመንግሥት ሆስፒታል ስለሆነ እዚህ ቦታ ሂዱ ብለን እንጠቁማቸዋለን፡፡ ብዙዎቹ ስለሚያፍሩ በጊዜ ሆስፒታል አይሄዱም፡፡ ለዚህ ነው ችግሩ እስኪከፋ ድረስ የሚቀዩት፤›› የሚሉት ሲስተር ውዴ፣ በሆነው ነገር እንዳያፍሩና እንዳይሸማቀቁ ቀለል አድርገው እንደሚያናግሯቸው ይናገራሉ፡፡

ያለምንም ጉዳት በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ምክንያት ሽንታቸውን ለመቆጣጠር የሚቸገሩ ሰዎችም እየታዩ ነው፡፡ እነዚህ አጋጣሚዎች ፌስቱላ በተራዘመ ምጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሁኔታዎች የሚፈጠር የጤና ችግር መሆኑን ያሳያሉ፡፡ መውለድ የምትችልበት ዕድሜ ላይ ሳትደርስ የፀነሰችም ሆነች በትክክለኛው ዕድሜ ላይ ሆና ያረገዘች ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ካላደረገች በፌስቱላ የመጠቃት ዕድል እንዳላት ግልጽ ነው፡፡ አንዲት እናት ለፊስቱላ የምትጋለጠው የማህፀኗ ቆሬ ትንሽ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሕፃኑ አመጣጥ በማያመች አቅጣጫ ስለሆነም ነው፡፡

እንደ ሲስተር ውዴ ገለጻ፣ ጽንሱ ትክክለኛ አመጣጥ ላይ ነው የሚባለው ጭንቅላቱን አስቀድሞና እጆቹን ሰብስቦ ወደ ታች አዘቅዝቆ ሲታይ ነው፡፡ አሥር ሴንቲ ሜትር በሆነው የእናቲቱ የማህፀን ቆሬ ማለፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን የጽንሱ አመጣጥ አግድሞሽ ከሆነ በተፈጥሮ መንገድ ለመውለድ ያስቸግራል፡፡ ምጥ ቢይዛትም ማህፀኗ ሊተረተር ይችላል እንጂ መውለድ አይቻላትም፡፡ ሁለትና ሦስት የወለዱ እንደ ዕድል ሆኖ በምጥ ጊዜ አመጣጡን ሊቀይር ይችላል፡፡ የመጀመርያ ልጃቸውን የሚወልዱ ግን ይህ ዕድል ፈፅሞ አይኖራቸውም፡፡ ብዙዎቹን እናቶች ለፊስቱላ እየዳረገ ያለውም ከጽንሱ አመጣጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ለረዥም ሰዓታት የሚቆይ ብርቱ ምጥ ነው፡፡

‹‹የጽንሱ አመጣጥና የእናትየው ማህፀን ሳይጣጣም ሲቀር ነው ችግሩ የሚፈጠረው፡፡ የእናትየው የማህፀን ስፋት፣ ቅርፅ የአጥንቶቿ ዓይነትም በወሊድ ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው፤›› ብለዋል፡፡ አንዲት እናት ምጧ ከ24 ሰዓታት ከበለጠ ችግር እንዳለ መጠርጠር ነው፡፡ ስለዚህም የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት ይኖርባታል፡፡ በሐምሊን ማዕከል የሚታከሙት ሴቶች አብዛኞቹ ለቀናት ያማጡና ከጤና ጣቢያ ጤና ጣቢያ፣ ከአንዱ ሆስፒታል ወደ ሌላው የተጉላሉ ናቸው፡፡

ለቀናት የሚቆይባቸው ምጥ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡  አንዱ ጉዳት የሽንት ፊኛ ላይ የሚደርስ ሽንቁር ነው፡፡ የሽንት ፊተኛው ደህና ሆኖ ደግሞ የሽንት ማውጫው ሙሉ በሙሉ ይጎዳል፡፡ ፊኛው ደህና ቢሆንም ተቆጣጥሮ የሚያስወጣው ከተጎዳ ሽንት መፍሰሱ አይቀርም፡፡ ፍሳሽን ከኩላሊት ተቀብለው ወደ ሽንት ፊኛ በሚያሳልፉ ቱቦዎችም ላይ እንዲሁ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ ምጧ በበረታ መጠን በእነዚህ አካል ክፍሎቿ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ ሆኖ የሽንት ፊኛዋ ሙሉ ለሙሉ ሊበተን ይችላል፡፡ በሀናም ላይ ያጋጠመው ይኸው ነው፡፡ በደረሰባት ሕመም እግሮቿ ለወራት መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር፡፡ ከባዱ ምጥ ፊኛዋን ሙሉ ለሙሉ በትኖታል፡፡

‹‹ለረዥም ጊዜ የተቀረቀረ ምጥ አጥንትን ይጎዳል፡፡ ፈጽሞ ያለ ሕክምና ዕርዳታ ሊወጣ የማይችል ጽንስ ሲሆን፣ እግራቸው መራመድ አይችልም፡፡ እንዲህ ያለ ከባድ ችግር ያለባቸውን እናቶች በመጀመርያ እንዲያገግሙ፣ ኢንፌክሽን ካላት ማፅዳት የመሳሰሉት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ አንዳንዴ እስኪያገግሙ እስከ ዓመት ሊፈጅ ይችላል፤›› ሲሉ ሲስተር ውዴ ያስረዳሉ፡፡ አንዲት እናት በማዕከሉ ስትቆይ ከ1,000 ዶላር በላይ ወጪ ይወጣባታል የሚሉት ሲስተር ውዴ፣ ሕክምናው ቀላል የሚባል ወጭ እንደማያስወጣ፣ በየጊዜውም ውስብስብ እየሆነ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...