የመንግሥት ባንኮች የፋይናንስ መግለጫ ሰነዶችን በጋዜጣ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ግዴታ ይጣልባቸዋል
በሥራ ላይ የሚገኘውን የባንክ ሥራ አዋጅ በማሻሻል የአገሪቱ ባንኮች አካላዊና ውስጣዊ የፋይናንስ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ፣ የሕግ ማሻሻያ ሊደረግ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ ማስረጃ ያመለክታል።
ሰነዱ እንደሚያስረዳው በሥራ ላይ የሚገኙት የአገሪቱ ባንኮች ተደጋጋሚ ዝርፊያና መሰል ሙከራዎች እየገጠሟቸው በመሆኑና ውስጣዊ የፋይናንስ ደኅንነታቸውም በአመዛኙ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ የሕግ ማሻሻያ በማድረግ ግዴታ መጣል እንደሚገባ ሰነዱ ያስረዳል።
በዚህም መሠረት የባንኮችን አካላዊ ደኅንነት አስተማማኝ ለማድረግ ባንኮች ማሟላት የሚገባቸውን የደኅንነት ደረጃዎች በሕግ መደንገግ፣ በመንግሥት መታመኑንና በቅርቡ በሚሻሻለው የባንክ ሥራ አዋጅ ውስጥ እንዲካተት መወሰኑን በሰነዱ ተመልክቷል።
አሁን ባለው ሁኔታ ባንኮች ከደኅንነት ካሜራ አንስቶ እስከ ነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ድረስ የተሟላ የደኅንነት መሠረተ ልማቶችን ሳያሟሉ እየሠሩ የሚገኙ መሆናቸው፣ ለዝርፊያ ሥጋት የዳረጋቸው በመሆኑ ባንኮች ማሟላት ስለሚገቧቸው የደኅንነት ደረጃዎችን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ መመርያ እንዲያወጣ የሚፈቅድ ድንጋጌ በማሻሻያ አዋጁ እንዲካተት መወሰኑን ሰነዱ ያመለክታል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የባንክ ሥራ አዋጅ የባንክ ሥራ ፈቃድ የሚሰረዝባቸውን ምክንያቶች በተመለከተ ሁለት ድንጋጌዎችን የያዘ ቢሆንም፣ ባንኮች የፋይናንስ ደኅንነት ሥጋት በሚገጥማቸው ጊዜ በሥራ ላይ መቆየት ስለመቻላቸው የተቀመጠ ድንጋጌ ባለመኖሩ፣ የፋይናንስ ደኅንነት ሥጋት ፈቃድ ለመሰረዝ የሚያስችል ድንጋጌ በማሻሻያ አዋጁ እንዲገባ ታምኖበታል። በመሆኑም ባንኮች “የገንዘብ አከል ንብረት እጥረት” ሲያጋጥማቸው ወይም ዕዳ መክፈል ወደማይቻልበት ወሰን ሲደርስ፣ ወይም ሕግንና መመርያን ለማክበር ፈቃደኛ ሳይሆኑ የባንክ ሥራ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ የሚያስችል የማሻሻያ ድንጋጌ በባንክ ሥራ አዋጁ የሚካተት መሆኑን የሰነድ መረጃው ያመለክታል።
በሌላ በኩል የባንኮችን ጤናማነት ለማረጋገጥ በብሔራዊ ባንክ የሚመደብ መርማሪ በአካል ተገኝቶ ድንገተኛ ምርመራ ማድረግ የሚያስችል የማሻሻያ ድንጋጌም፣ በባንክ ሥራ አዋጁ የሚካተት ሆኖ ቀርቧል። ሌላው የባንኮችን የፋይናንስ ጤንነት ለመጠበቅ በማሻሻያነት የሚቀርበው የባንክ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ባለድርሻ ከሆኑበት ባንክ፣ አክሲዮናቸውን በማስያዝ ብድር እንዳያገኙ ገደብ መጣል ይገኝበታል።
የባንኩ ካፒታል ማለት የባንኩን አክሲዮን የሚያካትት በመሆኑ፣ ይህንን የባንኩን ካፒታል ለባንኩ ብድር እንደ ዋስትና ማስያዝ ጤናማ አሠራር አለመሆኑን ሰነዱ በምክንያትነት ያስቀምጣል፡፡
በሥራ ላይ ያለው የባንክ ሥራ አዋጅ የፋይናንስ ግልጽነትን ለማረጋገጥ ሁሉም የግል ባንኮች የፋይናንስ መግለጫዎቻቸውን በየዓመቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ሲያስገድድ፣ የመንግሥት ባንኮችን ግን በዚህ ግዴታ ውስጥ አለማካተቱ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ፣ የመንግሥት ባንኮችም የፋይናንስ መግለጫዎቻቸውን በየዓመቱ በጋዜጣ በማሳተም ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ በባንኩ ሥራ አዋጁ ውስጥ የማሻሻያ አንቀጽ ሆኖ እንዲካተት መቅረቡን ሰነዱ ያመለክታል።
በተጨማሪም ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጎች በባንክ ሥራ ውስጥ በባለአክሲዮንነት እንዳይሳተፉ የተጣለው ክልከላ እንዲነሳ፣ ያለገደብ በባንክ ሥራ ውስጥ በግልም ሆነ እነሱ ባቋቋሙት ኢትዮጵያ ውስጥ በተመዘገበ ድርጅት አማካይነት የአክሲዮን ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል የማሻሻያ ድንጋጌ በአዋጁ እንዲካተት ይፈቅዳል። ይህ ቢሆንም የአክሲዮን ባለቤት የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአክሲዮን ድርሻቸው የሚያገኙትን ትርፍ በብር እንጂ በውጭ ምንዛሪ መውሰድ እንደማይችሉ በሰነዱ ተብራርቷል።
እነዚህንና ሌሎች ማሻሻያዎችን የያዘው ረቂቅ የባንክ ሥራ አዋጅ በቀጣዮቹ ቀናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።