Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፀረ ሽብር ሕጉን የሚተካ ረቂቅ ሕግ በምክር ቤቱ እየታየ ነው

ፀረ ሽብር ሕጉን የሚተካ ረቂቅ ሕግ በምክር ቤቱ እየታየ ነው

ቀን:

ኅብረተሰቡን ያላሳተፈ ነበር የተባለውና ለአሥር ዓመት ከነአወዛጋቢነቱ ሲተገበር የቆየውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደረገበት፡፡ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ረቂቅ ሕጉ ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር›› በሚል ስያሜ የቀረበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ስድስት ክፍሎችና 47 አንቀጾችን ይዟል፡፡ ረቂቁ በተለይም የሰብዓዊ መብትን ይጥሳሉ የተባሉ ድንጋጌዎችንና ለትርጉም ክፍተት በመስጠት ፖሊስ አሻሚ ዕርምጃ እንዲወስድ በር ይከፍታሉ የተባሉ ቃላቶችንና ዓረፍተ ነገሮችን እንደገና በማሻሻል መቅረቡን የረቂቁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አምባሳደር መስፍን ቸርነት የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትና ይዘት ዙሪያ ለአባላቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አጀንዳው ቀዳሚ ያደረገው በዓለም ሰላምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ከሆኑ ወንጀሎች አንዱ የሆነውን የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እንዲሁም ባለፉት ጊዜያት ተግባራዊ የሆነውን ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመቆጣጠር ጭምር ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የረቂቅ አዋጁ ሌላኛው ዓላማ የሽብር ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግና ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ፣ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችልና የመንግሥትንና የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዲጠበቁ ለማስቻል እንደሆነ በማብራሪያው ተመላክቷል፡፡

በ2001 ዓ.ም. ተግባር ላይ ውሎ የቆየው የፀረ ሽብር አዋጅ በይዘትም ሆነ በአተገባበር እንከኖች እንደነበሩበት የገለጹት የመንግሥት ተጠሪው፣ ተሻሽሎ የቀረበውና ሽብርን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ አዋጅ በነባሩ አዋጅ ጥያቄዎች የሚነሳባቸውን ክፍተቶችን ለማስተካከል በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን የረቂቁ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡ የዚሁ የአዲሱ ረቂቅ ሕግ የመግቢያ አንቀጽም ነባሩ የፀረ ሽብር አዋጅ የዜጎችን መብትና ነፃነት ያለአግባብ እንደሚገድብ ገልጾ፣ መንግሥትም የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካትና የሚቃወሙትን ለማጥቃት ያወጣው ሕግ ነው የሚል ትችት ሲቀርብበት እንደነበር ያብራራል፡፡ ረቂቁ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ያለመ መሆኑን በመግለጽ፣ ሕግን በማስከበር ሒደት ሕግ የሚተላለፉ የፀጥታ ኃይሎችን ተጠያቂና ኃላፊነት እንዲወስዱ ለማድረግና ለተጎጅዎች ካሳ ለመጠየቅ የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል። ለአብነትም በነባሩ ሕግ ማንኛውንም ግለሰብ በሽብር የሚጠረጠር ከሆነ የፀጥታ አካላት በድብቅ ምርመራና መረጃ መሰብሰብ እንዲችሉ ይፈቅዳል፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግን ይህ አሠራር በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠን የግለሰቦች መብት የሚጥስ በመሆኑ ድንጋጌውን አስወግዶታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ረቂቁ በክፍል ሁለት የአዋጁን ዋና ይዘት የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይም በአንቀጽ 3 የሽብር ድርጊት መቼ እንደሚያስቀጣ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ እንዲሁም የሽብር ድርጊት ከሽብር ወንጀል ጋር እንዳይምታታ በትርጉም ክፍል የሽብር ድርጊትን እንዲይዝ ተደርጎ መዘጋጀቱም በማብራሪያው ተገልጿል፡፡ በዚሁ ድንጋጌም የአዋጁ መሠረት ተደርጎ የተቀመጠ ሲሆን፣ በሽብር ድርጊት የተሳተፈ ሰው ሊቀጣ የሚችልበትን የቅጣት ወሰን በሦስት እርከኖች ተከፍሎ ተቀምጧል፡፡ የመጀመርያው ከ10 እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ ሲደነግግ፣ ሁለተኛው እርከን ከ15 እስከ 25 ዓመት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የመጨረሻውና ሦስተኛው የቅጣት እርከን ደግሞ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ ሆኖ መደንገጉን በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ ይህ የቅጣት ደረጃ በነባር አዋጅ በጥቅሉ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ ሆኖ ነበር የተደነገገው፡፡ በዚሁ በአዲሱ ድንጋጌም ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም ርዕዮተ ዓለምን ለማራመድ በማሰብ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የአካል ጉዳት ያደረሰ፣ የገደለ ወይም ያገተ እንደሆነ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ ለተጠቀሰው ዓላማ ሲባል በተፈጥሮ ሀብት ወይም በአካባቢ ላይ ጉዳት ማድረስም ተመሳሳይ ቅጣት ያስከትላል፡፡

በተጨማሪም የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የዛተ ሰውም ዛቻው ሊፈጥር የሚችለውን ድንጋጤና ፍርኃት እንዲሁም ድርጊቱን ለመፈጸም ዕድሉን ቢያገኝ የሚያስከትለውን ጉዳት በማገናዘብ፣ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ረቂቅ ሕጉ ያስረዳል፡፡ የረቂቅ ሕጉ ማብራሪያ የሲቪል መብትን በመጠቀም መንግሥትን ለማስገደድ መሞከር መብት ነው ይላል፡፡ በመሆኑም ከሥራ ማቆም አድማ ጋር ተያይዞ ሆን ተብሎ የሚደረግና አገልግሎት ማቋረጥን የሚያስከትል ቢሆንም፣ እንደ ሽብር ድርጊት እንደማይቆጠር ረቂቁ ደንግጓል፡፡ ድርጊቱ መብትን ለመጠየቅ የሚያስችል ልዩ ሁኔታ ከሌለው ግን እንደ ሽብር ድርጊት ይቆጠራል ይላል፡፡

ምክር ቤቱ በማሻሻያ አዋጁ ላይ በተብራሩ ሕጎች በተለይ በ2001 ዓ.ም. የወጣው የፀ ሽብርተኝነት አዋጅ ኅብረተሰቡን ያላሳተፈ፣ የዜጎችን መብትና ነፃነት አላግባብ የገደበ እንዲሁም መንግሥት ሕጉን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ብሎም ትችት ሲቀርብበት እንደነበረ አስተውሶ፣ የዜጎችን መብትና ነፃነቶች ላይ አላግባብ ገደብ የሚያደርጉ ሕጎች በተገቢው መንገድ የሚፈጸምበት ሒደትን ያካተተ እንዲሆን የቀረበው ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 57/2011 ሆኖ በዋናነት ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በተባባሪነት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲታይ በሙሉ ድምፅ መርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...