Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 በውጭ ምንዛሪ ሽኩቻ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በርካሽ እየተቸበቸቡ እንደሆነ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን የዱቤ ሽያጭ መመርያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተቃወመው

ከውጭ አገር ሸቀጣ ሸቀጥ አስመጥተው በውድ ዋጋ ለመሸጥ ሲሉ ብቻ ወደ ኤክስፖርት ሥራ የገቡ ነጋዴዎች፣ የአገሪቱን የግብርና ምርቶች በርካሽ ዋጋ እየቸበቸቡ መሆኑ ተነገረ፡፡

በግብርና ዘርፍ በብዙ ውጣ ውረድ የሚመረቱት ቡና፣ ሰሊጥና የተለያዩ የቅባት እህሎች፣ ጥራ ጥሬና የቁም እንስሳት በአገር ውስጥ ገበያ በተጋነነ ዋጋ እየተሸጡ፣ በውጭ አገር ገበያ ግን ዋጋቸው እየወደቀ ነው ተብሏል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመከሩበት ስብሰባ ላይ፣ ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት፣ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ወይም ረቡዕ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አንድ ኩንታል ሰሊጥ 2,800 ብር ተሸጧል፡፡ ነገር ግን ለዓለም ገበያ የቀረበው ይህ አንድ ኩንታል ሰሊጥ የተሸጠው 1,600 ብር ብቻ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በውድ የተገዛ ምርት በውጭ አገር ገበያ ለምን በርካሽ ተሸጠ ቢባል መልሱን እናውቀዋለን፡፡ ኪሳራው በሌላ መንገድ ስለሚካካስ ነው፤›› ሲሉ ምክንያቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የኢትዮጵያ የኤክስፖርት እጅግ አደገኛ አዘቅት ውስጥ እየገባ ነው ተብሏል፡፡ ነጋዴዎች ወደ ኤክስፖርት ሥራ እየገቡ የሚገኙት ወደ ውጭ ከሚልኳቸው የግብርና ምርቶች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ የመጠቀም ቅድሚያ ስለሚያገኙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለአብነት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከዘርፉ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የተገኘው 1.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ወ/ሮ ፈትለወርቅ በግልጽ እንደተናገሩት፣ የአገር ሀብት እየተጣለ በመሆኑ ከኤክስፖርት የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ የነዳጅ ወጪ እንኳ አይሸፍንም፡፡

‹‹አገሪቱ ለነዳጅ ግዥ በዓመት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች፡፡ ባለፈው ዓመት ከኤክስፖርት የተገኘው 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የነዳጅ ወጪን እንኳ አልሸፈነም፡፡ በዚህ ዓመት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከዚህም ያነሰ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ኤክስፖርቱ ያለበትን አሳሳቢ ደረጃ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በስብሰባ ላይ የተገኙ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሀብቶች እንደሚሉት፣ ኤክስፖርት ሥራ መሆኑ እየቀረ ነው፡፡ በአንፃሩ ወደ ኤክስፖርት የገቡ ነጋዴዎች የአገሪቱን ሀብት በርካሽ እየሸጡ፣ በገበያ ውስጥ የጠፉ ዕቃዎችን እያስመጡ ገበያውን በመረበሽ ሀብት እያካበቱ ናቸው ይላሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም አንድ የአገር ውስጥ ነጋዴ ለውጭ ዜጋ ምርቱን ሲሸጥ፣ ሌላ የአገር ውስጥ ነጋዴ ባላንጣ ሆኖ እየተነሳ ዋጋ ቀንሶ እየሸጠ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እከሌ ከሰጠህ ዋጋ በአምስት በመቶ ቀንሼ ልሽጥልህ እየተባሉ አገሪቱ ከማትወጣበት አረንቋ ውስጥ እያስገቧት ነው ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡ ከሞራል አንፃር እጅግ አስነዋሪ ነው ሲሉም ሕገወጡን የንግድ ውድድር ባለሀብቶቹ ይኮንናሉ፡፡

ሚኒስትሯም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ መንግሥት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በስንት ተገዝቶ በውጭ አገር ደግሞ በስንት እንደሚሸጥ መረጃ አለው ይላሉ፡፡ ‹‹ከሞራል አንፃር ኃላፊነት ሊሰማ ይገባ ነበር፡፡ በመንግሥት አስተዳደራዊም ሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ዕርምጃ ከመወሰዱ በፊት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ሥራዎች ስላሉ ነው ዕርምጃ ያልወሰድነው፤›› በማለት ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

‹‹ለኤክስፖርት የተሰጡ ማበረታቻዎች ለአጓጉል ተግባራት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ኤክስፖርት እየተገደለ ኢምፖርት እየተበረታታ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ለአብነት ብረት አምራቹ እየተንገዳገደ የህልውና አደጋ ሲጋረጥበት፣ ብረት አስመጪው ግን እየተበረታታ ነው፡፡ ይህ በፍጹም ሊሆን አይገባም፣ አሠራሩ ይስተካከላል፤›› ሲሉ ችግሩን ገልጸዋል፡፡

ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተለይ ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ተክተው የሚሠሩ ባለኢንዱስትሪዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ መመርያ መገለላቸውን ባለመቀበል አጋርነቱን አሳይቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 3 ቀን 2017 ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የውጭ አገር ብድርና ዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተመሠረቱ ማምረቻዎችን ያገለለ በመሆኑ፣ ለከፍተኛ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር ያደረገ ነው ተብሎ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ በዚህ አሠራር ኤክስፖርት የሚያደርጉ የውጭ ኩባንያዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ አገር በቀል አምራቾች ግን ተገልለዋል ነው የሚባለው፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ  ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገር ውስጥ አምራቾች በብሔራዊ ባንክ መመርያ መገለላቸው አግባብ አይደለም የሚል አቋም ተይዟል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር እየተነጋገርንበት ነው፤›› ሲሉ አቶ ተካ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች