Saturday, January 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጥ!

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝርና በጥልቀት የሚከታተሉም ሆኑ ለዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን፣ ከምንም ነገር በፊት ለአንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የሚወተውቱት፡፡ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው እንስሳ፣ ከምንም ነገር በፊት የአገር ህልውና መቅደም አለበት፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝ የሚሆነው ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ሲቻል ነው፡፡ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ችግሮች እየበዙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደተባለው ሕግና ሥርዓት ማስፈን ካልተቻለ ሥርዓተ አልበኝነት ይሰፍናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ የጦር መሣሪያ ዝውውር አለ፡፡ ከነፍስ ወከፍ እስከ ጦር ሜዳ የቡድን መሣሪያዎች ድረስ በገፍ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ድንበሮችን አቋርጠው አዲስ አበባ ከተማ የደረሱ በርካታ የጦር መሣሪያዎች በተለያዩ ጊዜያት መያዛቸው ይታወሳል፡፡ ከሕግ አስከባሪዎች አምልጠው በየቦታው የተበታተኑ መጠናቸው ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በተለያዩ ክልሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የጦር መሣሪያ መታጠቅ ተለምዷል፡፡ ድግሶችና የለቅሶ ሥነ ሥርዓቶች በጦር መሣሪያ እየታጀቡ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም በተለያዩ ሥፍራዎች በሰዎች ሕይወት ላይ አደጋ ደርሷል፡፡ ይህንን ጉዳይ በፍጥነት ፈር ማስያዝ ካልተቻለ መጪውን ጊዜ መተንበይ አይከብድም፡፡ ይህ ችግር ከቀዳሚ መፍትሔ ፈላጊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡

በተለያዩ ሥፍራዎች የተለመዱ ግጭቶች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ደጃፍ ማንኳኳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በተማሪዎች መካከል የሚያጋጥም አለመግባባት የብሔር ገጽታ እየተላበሰ ለሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች መዳረሻቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ መጪውን ጊዜ ያከፉታል፡፡ በግለሰቦች የዕለት ጊዜያዊ ፀብ የሚነሱ አለመግባባቶች ከፍ ወዳለ ብሔር ተኮር ግጭት እየተለወጡ በርካታ ጉዳቶች አድርሰዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ አንድ ተማሪ በአሳዛኝ ሁኔታ ግድያ ከተፈጸመበት በኋላ፣ መሰንበቻውን ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ በሌላ ተማሪ ላይ ግድያ ተፈጽሟል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከግጭት አዙሪት ውስጥ የማውጣት ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም ከፍተኛ ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የብቀላ ጥቃቶች በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እየቀጠሉ መመለሻው ይቸግራል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ድርጊት መታደግ የግድ ነው፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራው በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጥ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡ ይህም ሌላው ቅድሚያ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቦታው መንገድ መዝጋት፣ የጦር መሣሪያ መተኮስ፣ ቦምብ መወርወር፣ ሰዎችን መግደል፣ የግለሰቦችን ንብረት ማውደምና መዝረፍ፣ የሰዎችን በነፃነት ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር መብት መገደብና በአጠቃላይ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ሥጋቶችን መደቀን ከመጠን በላይ እየተለመደ ነው፡፡ ከእነዚህም አልፎ የታችኛውን አስተዳደራዊ መዋቅር በማፍረስ ሥርዓተ አልበኝነትን ማንገሥ የዘወትር ተግባር እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ራሳቸውን ከሕግና ከሥርዓት በላይ ያደረጉ ጉልበተኞች አገር ሲያተራምሱና ሕዝብ የደኅንነቱ ጉዳይ ሲያሠጋው፣ ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር በላይ የሆነ ያጋጠመ ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ትጥቁን ያልፈታ ኃይል ወለጋ ውስጥ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር አሁንም እየተዋጋ ነው ሲባል ግራ መጋባቱን ያንረዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች የታጠቁ ኃይሎች ያለ ማንም ጠያቂ እንደፈለጋቸው ሲፏልሉ፣ ወዴት እየተጓዝን ነው ያሰኛል፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች ከአካባቢ ርቆ ለመሄድ ፍራቻ ተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሲገደብ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሆነውን ግን ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ብቻ ነው፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት እየተስፋፋ ትዕግሥትን ማማከኛ ማድረግ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ለዚህ ችግር  ቅድሚያ አለመስጠት ይዋል ይደር እንጂ ያስጠይቃል፡፡

በሌላ በኩል የኢኮኖሚው ሁኔታ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኑሮ ውድነቱ እየተባባሰ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የውጭ ብድር ጫና፣ የምርትና ምርታማነት ማሽቆልቆል፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ከአቅም በታች ማምረት፣ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የሚደረገው ጥረት አናሳነትና የመሳሰሉት የኢኮኖሚው ጨፍጋጋ ገጾች ናቸው፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በየቀኑ ዋጋቸው ሲጨምርና የሕዝቡ የመግዛት አቅም ሲመናመን በስፋት  እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የዘረፋ ወንጀሎች ሲበዙ፣ ወደ ጎዳና የሚወጡ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር፣ ሴተኛ አዳሪነት ሲስፋፋና የመሳሰሉት አሳዛኝ ነገሮች ሲንሰራፉ ለሰላምና ለመረጋጋት መጥፋት ሰበብ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ጉዳይ ሲነሳ መሠረታዊ የሆነው የዳቦ ጥያቄ ግዙፍ ሆኖ ይቀርባል፡፡ የመጠለያ ጉዳይ አንገብጋቢነት ይጨምራል፡፡ ኢኮኖሚው እንደ በረዶ ሲቀዘቅዝ ደግሞ የሥራ አጡ ቁጥር ያሻቅባል፡፡ ሥራ አጡ ኃይል አማራጭ ሲያጣ በጠራራ ፀሐይ ለዘረፋ ይንቀሳቀሳል፡፡ አሁንም ተጀምሯል፡፡ ይህ ይዋል ይደር የማይባልበት ችግር በርብርብ ቅድሚያ ተሰጥቶት መፍትሔ እንዲያገኝ፣ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት፡፡ የግድ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ የሥራ መስኮች ከተሰማሩ ባለሙያዎች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች መወያየታቸው አይዘነጋም፡፡ በውይይቶቹ ላይ ከቡድን ጥቅሞች በላይ ማየት የተሳናቸው አስተያየቶች የተሰሙትን ያህል፣ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችም በስፋት ተሰንዝረዋል፡፡ በጥያቄም ሆነ በአስተያየት መልክ የቀረቡትን ጠቃሚ ሐሳቦች መነሻ በማድረግ፣ እያጋጠሙ ላሉ መጠነ ሰፊ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመፈለግ መነሳት የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ በተለይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ የጠቆሙ ባለሙያዎችን ማሳሰቢያ ቸል ማለት አይገባም፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ለሥልጣንና ለተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ሲሉ ከከበቡት አስመሳዮችና አድርባዮች ራሱን ማጥራት አለበት፡፡ እነዚህ መንግሥትን ከማሳጣት ያለፈ ሚና የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚፈቱት ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ጭምር በሚያደርጉት ተሳትፎ ነው፡፡ ይህ ተሳትፎ ደግሞ በዕውቀት፣ በልምድና በሥነ ምግባር የታጀበ ስለሚሆን ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ይህንን ጉዳይ በአጽንኦት ቢያጤኑት መልካም ነው፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው በርካታ ችግሮች ባሉባት አገር ውስጥ፣ ችግሮችን ለመፍታት አቅምና ብቃት ያላቸውን ዜጎች ማፈላለግ ላይ ማተኮር የግድ ይሆናል፡፡ ሌላው ሸብረብ ለሚዲያ ፍጆታና ለዝና ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም፡፡ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ እንተባበር ማለት የወቅቱ መሠረታዊ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም ለአንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት በፍፁም አይዘንጋ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

ቤተ መንግሥት የያዘ ”የጫካ ሃውስ” እየተገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋገጡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቤተ መንግሥት የያዘ “የጫካ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቀጥሎ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት  አቅም ግንባታ እንቅስቃሴ

በኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ታሪክ ረዥም ዘመናትን ማስቆጠሩ የሚነገርለት መከላከያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...

የመንግሥት አንዱ ኃላፊነት ዜጎችን ማዳመጥ ነው!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ድጋፍ የሚሰጠውን ወገን ብቻ ሳይሆን፣ በተቃውሞ ጎራ ያለውን ጭምር በአንክሮ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ የዕለት ኑሮዋቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ከሚሉ ዜጎች...