Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የተለወጠ ፖሊሲ ስለሌለ የምንከተለው የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ነው›› ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተጓዘ ያለበት መንገድ ብዥታ የፈጠረባቸው አገር በቀል ባለኢንዱስትሪዎች የፖሊሲ ለውጥ ተደርጓል ወይ በማለት ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፈትለ ወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ላስመዘገበችውም ሆነ ወደፊት ለምታስመዘግበው ዕድገት ብቸኛው መንገድ የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ብቻ ነው አሉ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ መንገዶች ላይ ከዋና ተዋናዮች ጋር፣ ሐሙስ ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል መክሯል፡፡

በወቅቱ በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ሳቢያ ለመውደቅ እየተንገዳገዱ የሚገኙ አገር በቀል የፋብሪካ ባለቤቶች በኢትዮጵያ የፖሊሲ ለውጥ ተደርጓል ወይ? ለአገር በቀል ኢንዱስትሪያሊስቶች ወይስ ለንግዱ ዘርፍ ነው ድጋፍ እየተሰጠ ያለው? በአጠቃላይ በኢኮኖሚው መስክ መንግሥት የሚከተለው አዲስ አቅጣጫ አለ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡

የባለሀብቶቹ ብሶት ማጠንጠኛ መንግሥት ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩ ድጋፎችና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቶች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ እየያዙ የሚገኙት በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች በመሆናቸውና በአንፃሩ በርካታ ሠራተኛ ይዘው፣ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ እየተኩ የሚገኙ ኢንዱስትሪያሊስቶች ችላ በመባላቸው ነው፡፡

ወ/ሮ ፈትለወርቅ፣ ‹‹መንግሥት ከልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ የተለየ አቅጣጫ አላስቀመጠም፣ ማስቀመጥም አይችልም፡፡ ካስቀመጠም መጨረሻው ጥፋት ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ከልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ውጪ የሄዱ የላቲን አሜሪካን የመሳሰሉ አገሮች መጨረሻቸው ውድቀት ነበር፡፡ በአንፃሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት ያስመዘገቡት የምሥራቅ እስያ አገሮች በልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ ተጉዘው ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ አዲስ ነገር አልፈጠረችም፡፡ የተደረገው ነገር የትኛውን መንገድ ብንከተል ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት እናመጣለን የሚለው ጉዳይ ተጠንቶ፣ ልማታዊ መንግሥት አቅጣጫን መከተል አዋጭ ሆነ፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ፈትለወርቅ ጨምረው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ በመጓዟ ዓለም የመሰከረለት ፈጣን ልማት ተመዝግቧል፡፡ ‹‹አሁን እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ይህንን ፈጣን ዕድገት አጠናክረን ይዘን እንድንቀጥል የሚያስችሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አገር በቀል ኢንዱስትሪያሊስቶች አገሪቱ የምትከተለውን ኢኮኖሚዊ አካሄድ ለውጥ ተደርጎበት ይሆን የሚል ጥርጣሬ ውስጥ ስለገቡበት ሁኔታ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በንግድ ሥራዎች ውስጥ የቆየውን የንግዱ ማኅበረሰብ በማግባባትና ድጋፍ በመስጠት ወደ ወጪ ንግድ እንዲገባ፣ ቀጥሎም እሴት የሚጨምሩ የማምረቻ ዘርፎች ውስጥ ገፋፍቶ አስገብቷል ብለዋል፡፡

በዚህ ሒደት በርካታ ጥሩ ነገሮች የታዩትን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች እንደገጠማቸውም ባለሀብቶች አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት አዳጋች ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዕጦት የአገሪቱ ችግር ነው ብለን ብንቀመጥም፣ ንግድ ሥራ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ደግሞ በሰፊው የውጭ ምንዛሪ ያገኛሉ፡፡ እንዲያውም ፋብሪካዎቻችን የሚፈልጉትን ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡልን ነጋዴዎችም አሉ፤›› በማለት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የፋብሪካ ባለቤት፣ ከአምራቾቹ ይልቅ ለነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ በሰፊው እየተሰጠ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

ሚኒስትሯ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ከተከለሉ የሥራ ዓይነቶች በስተቀር የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የተለየ ማበረታቻ የሚገኝበት ሁኔታ አልነበረም በማለት የገለጹት ወ/ሮ ፈትለወርቅ፣ ‹‹ለአገር በቀል ባለሀብቶች ማበረታቻ መስጠት የሚያስችል ፓኬጅ እየቀረፅን ነው፡፡ ጥናቱን እንደጨረስን ለመንግሥት እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች