ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሥራ እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ጫፍ መድረሱ እየተነገረ ካለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት ጋር ሊወያዩ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለበት አሳሳቢ ሁኔታ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሠራተኞች ጭምር አደጋ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ውይይቱ የሚደረገው ከአገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለድርሻ ከሆኑት ወሳኝ ባለሀብቶች፣ ከፌዴራልና የክልል አመራሮች ጋር ሲሆን፣ በፖሊሲዎችና በማስፈጸሚያ ሥልቶች ላይ ተገቢውን ግንዛቤ ለመያዝ መሆኑን ሪፖርተር ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ምንጮች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
በማኅበር ለታቀፉትና ከማኅበር ውጪ የሆኑ የዘርፉ ባለድርሻዎች ብዙ በመሆናቸው እንደ ብዛታቸው ታይቶ የተሳታፊዎቹ ቁጥር በኮታ እንዲሆን ተወስኖ፣ እስካለፈው ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚወያዩትን ሰዎች ስም ዝርዝር ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲልኩ የተነገራቸው ቢሆንም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚያደርጉት ውይይት መቼ እንደሆነ አለመታወቁን አክለዋል፡፡
የተቀዛቀዘውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት፣ ፖሊሲውን ለመተግበርና ውጤት ላይ ለመድረስ ባለድርሻ አካላቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚያደርጉትን የምክክር መድረክ አስመልክቶ ሪፖርተር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማኅበር የቦርድ አባላትን አነጋግሯል፡፡
የቦርድ አባላቱ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ከ1,500 በላይ የተመዘገቡና ከ800 በላይ ደግሞ ማኅበሩን በመደገፍ የሚንቀሳቀሱ አባላት አሉት፡፡ ተቋራጮቹ ወደ ዘርፉ የገቡት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን፣ ገና 30 ዓመት ያልሞላቸው የግል ዘርፍ ተዋናይ በመሆናቸው በበርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ራሱን የቻለና ዘርፉን የሚያበረታታም ሆነ የሚደግፍ ሕግም ሆነ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች እንደሌላት የገለጹት ተቋራጮቹ፣ በተለይ አገር በቀል ተቋራጮች ያለውን የልምድ፣ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ አቅም ፈጥረው ወደ ዘርፉ መግባት መቻላቸው ለአገሪቱ ያለው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ ድርጅት በአገሩ ቢሠራና ቢያተርፍ መልሶ ኢንቨስት የሚያደርገው በአገሩ መሆኑን የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ 99 በመቶ የሚሆነው የሥራ ድርሻም የሚሰጠው ለኢትጵያውያን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉትና የአንድ አገር ጥንካሬም የሚለካው ወይም የሚታየው አገር በቀል ድርጅቶችንና ባለሙያዎችን ማፍራት በመቻሉ፣ እንዲሁም ዘላቂ ዕድገት ሲያስመዘግብ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ተግዳሮቶች እንደገጠሙትና ተግዳሮቶቹም መቀጠላቸውን የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ የአቅም ውስንነት፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ልምድ ችግሮች፣ በተጨማሪ የምንዛሪ ተመን መውረድ ትልቁና ዋናው ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዘርፉ የሚሆን ማሽንና ግብዓት በትክክለኛው ጊዜና በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ከፍተኛ ችግር እንደገጠመውም አክለዋል፡፡
የማኅበሩ ቦርድ አባላት አበክረው እንደገለጹት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የምንዛሪ ተመን መውረድ በተለይ በተጀመሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ የውጭ አገር ተቋራጮች ግን ይኼ ችግር እንደሌለባቸውና ፍራንኮ ቫሉታም ይፈቀድላቸዋል ብለዋል፡፡ ግዥና ጨረታ ላይ ለውጭ አገር ተቋራጮች የሚሰጣቸው የተለየ መብት ሲኖር፣ ለኢትጵያውያን ድርጅቶች ግን አንዲት ብሎን እንኳን ለማስመጣት ቢፈለግ ሁሉም ነገር በባንክ በኩል እንዲሆን በመደረጉ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡
ኮንትራክተሮች ፕሮጀክት የሚወስዱት መጀመርያውና መጨረሻው ጊዜ በተወሰነና በሕግ ውል ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሪ የሚገኘው መኖር አለመኖሩ ታይቶ በወረፋ ስለሆነ አሁን አሁን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የመኖርና ያለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን የማኅበሩ ቦርድ አባላት ተናግረዋል፡፡ በምንዛሪ መውረድ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች መዘጋታቸውን ጠቁመው፣ አሁንም በመዘጋት ሥጋት ውስጥ የገቡ በርካታ ድርጅቶች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡
አገር ውስጥ ያሉና ባለድርሻ አካላት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ያላቸው ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ በባንኮች ኤልሲ ከፍቶ ብድር ለማግኘት ያለው ችግር እንኳን ግምት ውስጥ ባልገባበት ሁኔታ ከ50 እስከ 100 ዓመታት ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ የዘርፉ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ መሆን የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውጭ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ሦስት በመቶ የወለድ መጠን ብድር እየተሰጣቸውና ፍራንኮ ቫሉታ እየተፈቀደላቸው ያለ ምንም የባንክ ሒደት የፈለጉትን ማሽንና የግንባታ ግብዓት እያስገቡ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ለማወዳደር ማሰብ የማይቻል መሆኑንም የቦርድ አባላቱ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ምንዛሪ የወረደው 15 በመቶ እንደሆነ ቢነገርም፣ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጭ ማኅበር በባለሙያዎች ጥልቅ ጥናት አስደርገው ከ60 በመቶ በላይ እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡
አገሪቱ እየተከተለች ያለው ገበያ መር ኢኮኖሚ በመሆኑ የብር ምንዛሪ መውረድን ተከትሎ ነጋዴዎችም በግብዓቶች ላይ ያንኑ ያህል ጭማሪ ስለሚያደርግ ኮንትራክተሩ የሚገዛው በገበያ ዋጋ መሆኑን ጠቁመው፣ የዘርፉ ተዋናዮች ከአራት እስከ ስድስት እጥፍ ሥራ ሲጀምር ከነበረበት ዋጋ ጨምሮ በመግዛት ኪሳራ ላይ መውደቁን ተናግረዋል፡፡
ለግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎች ከሚጠበቀው በላይ ዋጋውን ያናረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት፣ ዕቃዎቹም በተፈለገው መጠን ወደ አገር ውስጥ መግባት አለመቻላቸውም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮንትራክተሮች ሥራቸው በውል የታሰረ በመሆኑ ግብዓቶች ሲጨምሩ የኮንትራት ዋጋ ማሻሻል እንደማይችሉ የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ የዕቃዎቹን አቅርቦት እንደፈለገ ለመግዛትና የተጀመረውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ የግብዓት ውስንነትና የአቅም ማነስ ስለሚያጋጥም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁ እንዳልቻም አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶችም ሙሉ በሙሉ መቆማቸውንም አክለዋል፡፡
ለድርጅቶች መዘጋትና ፕሮጀክቶች መቆም ሌላው ችግር ደግሞ የፕሮጀክት አስተዳዳሪ አማካሪ መሐንዲሶች መሆናቸውን የጠቆሙት አባላቱ፣ ፕሮጀክቱ በተወሰነለት ጊዜ አላለቀም በሚል ቅጣት መጣልና ውል ማቋረጥ ውስጥ በመግባት ለመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና ከባንክ በብድር ያስያዙትን ገንዘብ በመውሰዱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ባንኮችም በወቅቱ ካልተከፈላቸው ዕርምጃ መውሰድ ስለሚጀምሩ፣ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ውድቀት ውስጥ ስለሚገቡ ድርጅቶቹ እየተዘጉ መሆናቸውንና ሊዘጉ ጫፍ የደረሱም እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ ምክንያት ሴክተሩ ባለቤት የሌለው በመሆኑ ነው የሚሉት የቦርድ አባላቱ፣ በዘርፉ ስም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ብሎ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም ቢኖርም፣ ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የፕሮጀክት ባለቤት በመሆናቸው ዘርፉ ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማኅበራቸው በአሜሪካውያን አስጠንቶ በኢትዮጵያ ደረጃ ሊቀየር ይገባዋል በማለት ያስቀመጠው ነጥብ፣ ወጥ የሆነ አገር አቀፍ የግዥና የፕሮጀክት ዲዛይን ተሠርቶና ጨረታ ወጥቶ ሥራ አፈጻጸሙ ፋይናንስ ተደርጎ ሥራው አልቆ እስከሚሰጥበት ድረስ፣ ያለውን ጊዜ መከታተል የሚያስችል የቁጥጥርና የአስተዳደር ማዕቀፍ መኖር እንዳለበት መሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም የሚያስፈጽም ራሱን የቻለ ተቋም ሊኖር እንደሚገባም እምነታቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
አገራዊ የሆነ፣ አስተዳደሩን የጠበቀ፣ ቅደም ተከተሉ የታወቀና ወጥ የሆነ ለአስተደደር የሚመች፣ የሚታወቅና ግልጽ የሆነ አሠራር መኖር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በጣም ጥቂት በሚባሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የሚመጥን ባይሆንም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ብቻ የኮንትራት አስተዳደር እንዳለው ገልጸው፣ በአብዛኛው ግን እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲከሰት፣ ምንዛሪ ሲወርድ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት ዋጋ ሰማይ መድረሱ እየታወቀ ለኮንትራክተሩ ምንም የሚታሰብለት ነገር እንደሌለ የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ ጉዳዩን በባቤትነት ወስዶ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ወይም ከውል ውጪ ውልን ማስተዳደር የሚችልና ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ የዘርፉን ችግር እያሰፋው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሁሉም ችግሮች ለበላይ አካል፣ የበላይ አካሉም ለቀጣዩ የበላይ አካል በመግፋት ለችግሩ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ በርካታ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ መድረሳቸውንና ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶና በራሱ ተነሳሽነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ መፍትሔ በመስጠት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲያልቁ ማድረግ የሚችል ብቃት ያለው አካል እንደሌለም፣ የሚታዩት ችግሮች ምስክሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አወቃቀርም ይኼን ለማድረግ የማያስችል መሆኑንም አክለዋል፡፡
ፕሮጀክቶች በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከሚበታተኑ ለአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቢሰጡ ውጤታማ ይሆኑ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ እንደ ስያሜያቸው ለተለያዩ ዓላማ ቢቋቋሙም፣ የማመለከታቸውን ሥራ እንዲሠሩ በመደረጋቸው ውጤታማ እንዳልሆኑ ፀሐይ የሞቀው እውነታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኮንትራክተሩ ፍላጎት ዘርፉ ጤናማ ሆኖ ለትውልድ መሻገርና የሚጠበቅበትን ሠርቶ መስጠት የሚችል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣና የሚያድግ፣ በዘርፉ ለሚመረቁ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ተገቢውን ድርሻ የሚያበረክት እንዲሆን ማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ይኼ የሚሆነው ደግሞ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመገናኘት፣ በመወያየትና በማንኛውም መንገድ መደጋገፍ ሲቻል ብቻ መሆኑን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ በግብፅ በተመሳሳይ ሁኔታ የምንዛሪ ዋጋ መውረድ አጋጥሞ እንደነበር የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ የአገሪቱ መንግሥት ያደረገው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ሰብስቦ ካወያየ በኋላ፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁበትን መንገድ በመፍጠርና በማገዝ የተፈጠረውን ችግር መቀረፉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ካውንስል የሚባል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቋቁሞ በሕግ የፀደቀና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ አካል እንደነበር ያስታወሱት የቦርድ አባላቱ፣ የት እንደደረሰ ባይታወቅም አሁንም አባላቱን በማሰባጠርና በማጠናከር ወደ ሥራ የሚገባበት መንገድ እንዲፈጠር ከከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር አብሮ እንዲሠራ ፕሮፖዛል ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
አንድ ችግር አገራዊ በሆነ ደረጃ ከመጣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ችግር ብቻ ሳይሆን የአገር፣ የመንግሥትና የሕዝብ ችግርም መሆኑን የገለጹት የቦርድ አባላቱ፣ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ኮንትራክተሩ ሳይሆን መንግሥት መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ የመንግሥት ጥያቄ መሆኑንና የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ጥያቄ ስለሆነ መንግሥት መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ችግሮቹ ከመንግሥት የሚሰወሩ ሆነው ሳይሆን፣ ችግሮቹን በድንብ አጥንቶና ለይቶ የሚያቀርብለት ኃላፊነት የሚወስድ ተቋም ባለመኖሩ መሆኑንም ግምት ውስጥ ከተዋል፡፡ የፕሮጀክቶች ወቅታቸውን ጠብቀው አለማለቅ የአገር ዕዳና የሕዝብ ችግር መሆኑን የጠቆሙት የቦርድ አባላቱ፣ አንድ ፕሮጀክት በሦስትና በአራት ዓመታት ማለቅ እየተገባው ስምንት ዓመት መቆየቱ ውድቀቱ የኮንትራክተሩ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የሚገኘው የኢኮኖሚም መሆኑን አሳስበዋል፡፡ የኮንትራክተሩ መውደቅ ሁለተኛ መሆኑንና ፕሮጀክቱ ግን ለአገርና ለሕዝብ ጭምር መሆኑም መታሰብ እንዳለበት አክለዋል፡፡ በአንድ ፕሮጀክት እስከ 2,000 እና ከዚያም በላይ ሠራተኞች እንደሚሰማሩና ደመወዝና አበል እንደሚከፈልና ቋሚ ወጪ መሆኑን ጠቁመው፣ ኮንትራክተሩ መክፈልና መኖር የሚችለው በየጊዜው መሥራትና ወቅቱን ጠብቆ ማስረከብ ሲችል በመሆኑ፣ ይኼንን ለማድረግ የመንግሥት ድጋፍ ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ኮንትራክተር የሚሠራው ከባንክ ጋር በመሆኑና ባንክ ደግሞ ወለዱ ስለማያቋርጥ፣ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ መንግሥት መድረክ በማዘጋጀትና በማወያየት የክፍያ ጊዜ ማስተካከያ ወይም ማሻሻያ እንደሚያደርግላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሠሩ ያሉ የሚመስሉ ኮንትራክተሮች እስከሚችሉት ድረስ ከአንዱ ፕሮጀክት ወደ ሌላው በማዘዋወር እንጂ፣ ቢበዛ ቢበዛ ከስድስት ወራት የበለጠ ጊዜ ሊያቆይ የሚችል አቅም ሊኖራቸው እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡
የሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል ከአንዱ ፕሮጀክት ክፍያ ወደ ሌላው በማዘዋወር፣ ንብረቶቻቸውን በማስያዝና ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላኛው በማዘዋወር እንጂ በቂ አቅም ያለው ድርጅት እንደሌለ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የባንክ ክፍያ ሲመጣ ሁሉንም አስረክበው ባዶአቸውን እንደሚቀሩና ድርጅቶቹ ተዘግተው ፕሮጀክቶቹ እንደሚቆሙ አስረድተዋል፡፡
አሁን ያሉበት ሁኔታ ‹‹የጊዜ ቦምብ›› ላይ በመሆኑ አንድ ቀን ሁሉንም ነገር እንደሚያጡት ተናግረዋል፡፡ ኮንትራክተር ሲሞት አብሮት በትስስር ያለው ስለሚሞት እንደ አገርም አደጋ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የተሳሰረ ነገር ሲወድቅ ለማንሳትም ከባድ ስለሚሆን ጥንቃቄው የመንግሥት ጭምር እንዲሆንም ጠቁመዋል፡፡
በሴክተሩ ተሰማርተው የሚገኙ ሠራተኞች ቁጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር በመሆኑ፣ ዘርፉ የሚሞት ከሆነ የሠራተኛው ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መግለጽ ለቀባሪው አረዱት ስለሚሆን መንግሥት አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ ችግር ያስከትላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
መንግሥት ጉዳዩን በባለቤትነት ወስዶ ከሥራ ተቋራጭ ማኅበርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ቁጭ ብሎ ችግሮቹ ምን እንደሆኑ፣ እንዴት እያደጉ እንደሆነ፣ የአካሄዳቸው አዝማሚያ ወዴት እንደሆነ፣ ነገ የሚያስከትሉት ምን እንደሆነና ሌሎች እውነታዎችን በማንሳት ውይይት አድርጎ መተማመን ላይ በመድረስ ውሳኔ መስጠት እንዳለበትም የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የኮንትራክተሩ ትልቅ ጭንቀት ከገንዘብ ምንዛሪ መውረድ ጋር ተያይዞ በመጣው ችግር ተጀምረው የቆሙ ፕሮጀክቶች ችግር ፈትተው የሚያልቁበትን መንገድ መፈለግ እንጂ፣ ትርፍ ማግኘት አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሮጀክቶቹ ዓይነት የተለያዩ ግብዓቶች ማለትም አስፋልት፣ ፈንጂ፣ ብረትና ሌሎች ግብዓቶችን መንግሥት ራሱ በጅምላ አስመጥቶ ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች በቅደም ተከተል እንዲያልቁ እንዲያደርግም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዘርፉ 40 ቢሊዮን ብር እንዳጣች ቢነገርም፣ ማኅበሩ ግን በግርድፍ ጥናት ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ማጣቷን ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ የስኳር፣ የዘይትና የስንዴ ችግሮች መንግሥት በጅምላ ከውጭ በማስመጣት ማሠራጨቱንና ችግሩን ለጊዜው መቅረፉን አስታውሰው፣ በኮንስትራክሽን ዘርፉም ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ ወይም የሦስትዮሽ (Tripartite) ኮሚቴ በማቋቋም የዋጋ ንረቱን በሚመለከት ዕቃው በገበያ ላይ ያለው ዋጋ ታይቶና ተጠንቶ የሥራ ተቋራጩ ትርፍ ሳይታሰብ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም እንዲቻልም አማራጭ አቅርበዋል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ለቡና ላኪዎች መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን አሠራር በኮንስትራክሽን ዘርፉም በመድገም፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከባንኮች ጋር በማወያየት የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲሻሻልላቸው እንዲያደርግ በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት የጠቀሷቸውን ዕርምጃዎች ከወሰደ ማንሰራራት እንደሚችሉም አክለዋል፡፡
የውጭ ሥራ ተቋራጮች በአገር ውስጥ ገብተው መሥራታቸው የሚደገፍ ቢሆንም፣ በሽርክና እንዲሠሩ የሚገደቡበትና ኢትዮጵያውያንን በኮንትራት አቅፈው የሚሠሩበት አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡
ሌላው ደግሞ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚያከናውኑት የፕሮጀክት ዓይነትና የዋጋ መጠን በሕግ ቢቀመጥ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን አሁን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የውጭ ድርጅቶች መንደር ውስጥ ገብተው እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይኼ በሌሎች አገሮች የማይደረግና የአገሪቱ ዜጎችና ድርጅቶች የሚያቀጭጭ በመሆኑ በሕግ ክልከላ እንደተጣለበት ጠቁመዋል፡፡ የውጭ ድርጅቶች የአገራቸው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶና ፍኖተ ካርታ (Road Map) አዘጋጅቶ ኮንትራክተሮቹ በሌላ አገር ሄደው በመወዳደር አሸናፊ እንዲሆኑ ፕሮግራም አውጥቶ ስለሚልካቸው፣ ከእነሱ ጋር ተወዳድሮ ለማሸነፍ አስቸጋሪና የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዘርፉን ችግር እንኳን የሚፈታ ባለቤት በሌለበት ሁኔታ ተወዳዳሪ መሆን የማይቻል እንደሆነ አክለዋል፡፡
መንግሥት በዘርፉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይዞ መሥራት እንዳለበትና የሚወጡ ደንቦችና መመርያዎች እየሰነጣጠቁ ከተጠያቂነት ለመዳን ሳይሆን፣ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ለተሻለ ውጤት ኃላፊነት ወስዶ መሥራት ምርጫ የሌለውና ጊዜው የሚፈልገው አካሄድ መሆኑን የማኅበሩ የቦርድ አባላት አሳስበዋል፡፡