ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና እሳቸውን ለመደገፍ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ በወጣ ሕዝብ ላይ፣ ቦምብ በመወርወር ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው አምስት ግለሰቦች እንዲከላሉ ብይን ተሰጠ፡፡
በእነ ጌቱ ግርማ ቶሎሳ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስና የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ብይኑን የሰጠው፣ ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ በብይኑ ተከሳሾቹ በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን በተወረወረው ቦምብ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ምስክርነትን፣ ሲፈተሹ ያዩ የደረጃ ምስክሮችን የሕክምና ማስረጃዎችንና ለፖሊስ የሰጡትን ቃል ማስተባበል ባለመቻላቸው እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ የመከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በተወረወረ ቦምብ ከ60 በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን መዘገቡ ይታወሳል፡፡