ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬት የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበትንና ተፈናቃዮች በድጋሚ የሚቋቋሙበትን የሚደነግግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
የካሳ አዋጅ ቁጥር 455/1997 ተደንግጎ በሥራ ላይ ከዋለ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን አዋጁ ወቅታዊነት የሚጎድለው በመሆኑ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታ የማስነሳት ጉዳይ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በቀጥታ የሚነካ ከመሆኑም በላይ፣ ሕይወቱ የሚነካው ሕዝብ ቁጥር እጅግ ብዙና በአመዛኙም ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማኅበረሰብ በመሆኑ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ተብሏል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ፣ ረቡዕ ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ውይይት ተደርጎበት በዋናነት ለከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ፣ በተባባሪነት ደግሞ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቶታል፡፡
‹‹የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበትንና ተነሺዎች የሚቋቋሙበትን ለመወሰን የወጣ አዋጅ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል፡፡
ረቂቁ የተዘጋጀው የፌዴራል ፖሊስ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የግብርና ሚኒስቴርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያካሄዷቸውን ጥናቶች መሠረት አድርጎ ነው ተብሏል፡፡
በመንግሥታዊ ተቋማቱ ጥናት መሬት ለሕዝብ ጥቅም ለልማት ሲፈለግ ከመነሻ ፕላን ጀምሮ የቦታው ነባር ተጠቃሚዎች አያያዝ፣ የካሳ አሰጣጥና ድጋፍ ዙሪያ የተስተዋሉ ችግሮች ካልተፈቱ ከዚህ በኋላ ለሚካሄዱ የተለያዩ ልማቶች ትልቅ ተግዳሮቶች እንደሚሆኑ መግባባት ላይ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
ማሻሻያ ከተደረገባቸው መካከል ካሳና ምትክ ሳይሰጥ ተነሺዎች ይዞታቸውን እንዳይጠቀሙ ለረዥም ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ መደረጉ፣ ካሳ ሲከፈልም ከረዥም ጊዜ በፊት በተገመተ ዋጋ መሆኑ ቅሬታ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡
በማሻሻያው ላይ ተነሺው አካል የካሳ ግምት በጽሑፍ እንዲያውቅ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተገቢው ካሳ ካልተከፈለው በመሬቱ ላይ ከቋሚ ተክልና ግንባታ በስተቀር ሌሎች ሥራዎችን፣ እንዲሁም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማንኛውንም ሥራ መሥራት እንደሚችል ሐሳብ ቀርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተነሺዎች በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ የሚደረግበት አሠራር እስከ ፈንድ ማቋቋም፣ እንዲሁም በልማቱ ምክንያት የተፈናቀሉና የገቢ ምንጫቸውን ላጡ ተነሺዎች በድጋሚ የሚቋቋሙበት አሠራር እንዲዘረጋ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ከዚሁ ጋር ንብረት መገመት የሚገባው አካል አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታና ወደፊት መሆን ከሚገባው አንፃር በአማራጭነት ማስቀመጥ፣ ከንብረት ግምት ጋር በተያያዘ ቅሬታና አቤቱታ የሚስተናግድባቸው አሠራሮችና እነዚህ አሠራሮች ተጠብቀው የሚተገበሩበት አሠራር በማሻሻያው ላይ ተካቷል፡፡
ረቂቅ አዋጅ ከከተማና ከገጠር መሬት ላይ የሚነሱ ተነሺዎች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች አስፍሯል፡፡ ባለፉት አሥርት ዓመታት በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በመንገድ ግንባታ በቴሌኮም በኤሌክትሪክ ዝርጋታዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በተለያዩ መሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከነባር ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አብዛኞቹ የልማት ተነሺዎች በልማት ምክንያት መነሳታቸውን ባይቃወሙም፣ በካሳና በምትክ ቦታ አሰጣጥ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን የመሠረተ ልማት አውታር የሚዘረጉ መንግሥታዊ ተቋማትን አቀናጅቶ እንዲመራ፣ የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የተሰኘ ተቋም አቋቁሟል፡፡
ኤጀንሲው የመሠረተ ልማት ተቋማትን አቀናጅቶ ከመምራት ባሻገር፣ የተነሺዎችን ካሳና ተያያዥ ጉዳዮችንም እንዲመለከት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡