Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የማስተዳደር ኃላፊነቱን ያልተወጣው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ...

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የማስተዳደር ኃላፊነቱን ያልተወጣው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ዋና ኦዲተር አመለከተ

ቀን:

የተመደበው አሥር ቢሊዮን ብር ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ በኦዲት ማረጋገጥ አልተቻለም

በድሬዳዋ ከተማ ብቻ ከፈንዱ ብድር የወሰዱ 124 ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ አለመገኘታቸው በማሳያነት ቀርቧል

ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተብሎ በ2009 ዓ.ም. የተመደበውን የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲያስተዳድር በአዋጅ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕጋዊ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱና በዚህም ምክንያት ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ በኦዲት ማረጋገጥ ባለመቻሉ፣ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የባንኩ አመራሮች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አመለከተ።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፌዴራል መንግሥትን የ2010 በጀት ዓመት የበጀትና የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ያከናወነውን ኦዲት በተመለከተ ከሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ ካቀረበው የተጨመቀ ሪፖርት በተጨማሪ፣ ዝርዝር የኦዲት ሪፖርቱን በሰነድ ለምክር ቤቱና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።

 ሪፖርተር ያገኘው ይህ ዝርዝር የኦዲት ሰነድ በበጀት አፈጻጸም ላይ ከተከናወነው ኦዲትና ግኝቶች በተጨማሪ፣ የሥራና ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ዋና ኦዲተር በተመረጡ ዘርፎች ላይ ያከናወናቸውን የክዋኔ ኦዲትና ግኝቶቹንም አካቶ ይዟል።

ከእነዚህ የክዋኔ ኦዲቶች ውስጥ መንግሥት በ2009 በጀት ዓመት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጣራ የመደበው አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ፣ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ያደረገው የምርመራ ኦዲት ይገኝበታል።

በዚህ ተዘዋዋሪ ፈንድ አጠቃቀምና ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን አስመልክቶ የተደረገው ኦዲት ውጤትም፣ ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ አረጋግጧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው አዋጅ ቁጥር 995/2009 መሠረት ተዘዋዋሪ ፈንዱን እንዲያስተዳድርና ለታለመለት ዓላማ መዋሉን እንዲያረጋግጥ ሕጋዊ ኃላፊነትን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስጠቱን የሚገልጸው የዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ዝርዝር ሪፖርት፣ ባንኩ ሕጋዊ ኃላፊነት የሰጠው አዋጅ ሳይሻር ወይም ሳይሻሻል ኃላፊነቱን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠቱ ምክንያት ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ማረጋገጥ አለመቻሉን ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 995/2009 አንቀጽ 9/1 እና 2 መሠረት ተዘዋዋሪ ፈንዱን በየክልሎቹ የሚገኙ ወጣቶችን ቁጥር በማገናዘብ በአነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት በኩል እንዲተላለፍ ማድረግ ሲገባው፣ ኦዲቱ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ የተመደበውን ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስተላለፈው በአዋጁ ከተገለጸው ውጪ ውክልና በተሰጣቸው በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮዎች በኩል መሆኑን ያብራራል።

በአዋጁ መሠረት ባንኩ የፈንዱን ሒሳብ በሚመለከት የተሟላና ትክክለኛ የሆነ የሒሳብ መዛግብት መያዝና በየስድስት ወራት ለገንዘብ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በዓመት አንድ ጊዜ ለፓርላማው ሪፖርት እንዲያደርግ ኃላፊነት እንደተጣለበት፣ የተዘዋዋሪ ፈንዱ አፈጻጸምን በተመለከተም ለዋና ኦዲተር ወይም እርሱ ለሚመድበው ኦዲተር ማስመርመር እንዳለበት በአዋጁ ግዴታ ቢጣልበትም ባንኩ አንዱንም እንዳልተወጣ የኦዲት ግኝቱ ያስረዳል።

ባንኩ በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት በማፈንገጥ ኃላፊነቱን ለክልል የፋይናንስ ቢሮዎች ሲያስተላልፍ፣ እነዚህ አካላት ከፈንዱ የተላለፈላቸውን ሒሳብ እንዲይዙ አለማድረጉ ለፈንዱ የተመደበው በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመወዋሉ ወይም ስላለመዋሉ በትክክለኛ ማስረጃ ለማረጋገጥ አለማስቻሉን የኦዲት ግኝቱ ይገልጻል።

የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በኦዲት ምርመራው ወቅቱ ለኦዲተሩ በሰጡት አስተያየት ተዘዋዋሪ ፈንዱ ለቅልጥፍና ሲባል በውክልና ለክልል የፋይናንስ ቢሮዎች እንዲሰጥና አፈጻጸሙንም በመንግሥት በሚቋቋም ኮሚቴ እንዲመራ የተደረገው፣ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር (ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ) ውሳኔ መሆኑን ቢገልጹም ዋና ኦዲተር ምክንያቱን አልተቀበለውም። ለዚህ የሰጠው ምክንያት በፓርላማ የወጣ አዋጅ በፓርላማው እስካልተሻረ ድረስ በባለሥልጣናት ውሳኔ ሊሻርም ሆነ ሊሻሻል የማይችል መሆኑን ነው።

 የፈንዱ ገንዘብ ሕግን ባልተከተለ መንገድ ለክልሎች የተላለፈ ቢሆንም፣ ለወጣቶች ዘላቂ ሥራና ኢኮኖሚያዊ ውጤትን ስለማስገኘቱ ናሙናዎችን በመውሰድ ኦዲተሩ ያካሄደውን የማሳያ ምርመራም በኦዲት ግኝቱ አካቷል። ለአብነት ያህል ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተላለፈው የፈንዱ ድርሻ እንዴት ሥራ ላይ እንደዋለ ለመገምገም በታኅሳስ ወር 2011 ዓ.ም. ከድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያገኘውን መረጃ በማስረጃነት አቅርቧል።

 በዚህ መረጃ መሠረት የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም በድሬዳዋ ከተማ ዘጠኝ ቀበሌዎች ሥር የሚገኙና በድምሩ 8,695,015 ብር ከፈንዱ ብድር የወሰዱ ኢንተርፕራይዞች መካከል፣ በአሁኑ ወቅት 105 ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ የማይገኙ ወይም የሌሉ መሆናቸውን የኦዲት ግኝቱ በማሳያነት አቅርቧል።

በተጨማሪም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በገጠር ከሚገኙ ሦስት ክላስተሮች በድምሩ  1,395,000 ብር ከፈንዱ ብድር የወሰዱ 19 ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ የማይገኙ ወይም የሌሉ መሆናቸውን፣ ከድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ካገኘው የሰነድ ማስረጃ ለማወቅ መቻሉን የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

መጠኑ የተለየ ቢሆንም ይህን መሰል ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሚታይ የኦዲት ግኝቱ ይገልጻል።

በመሆኑም የፈንዱን ሒሳብ በአግባቡ ለመቆጣጠርና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርተው ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ እንዳይችሉ እክል መፈጠሩን፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሚቆጣጠር ተቋም ገንዘቡ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሒደት ውስብስብና አዳጋች እንዲሆን ማድረጉን ያመለክታል።

በተጨማሪም መንግሥት የተዘዋዋሪ ፈንዱን አፈጻጸም በተመለከተ ግልጽ ድምዳሜ ላይ እንዳይደረስ ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ፣ ፈጣን እርማት ሊደረግ እንደሚገባና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ይገልጻል።

በሌላ በኩል ተዘዋዋሪ ፈንዱ የታለመለት ግብን እንዲያሳካ የአፈጻጸም መመርያ የማውጣትና የመከታተል ሕጋዊ ኃላፊነት የተሰጠው የገንዘብ ሚኒስቴርም ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ዋና ኦዲተር ገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...