የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ፣ የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) በፈረንሣይ በሚያካሂደው ጉባዔ ለመታደም ባቀኑበት ወቅት፣ የፈረንሣይ ፖሊስ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ለምርመራ ቢያስራቸውም ባለፈው ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ ሳይመሠረትባቸው መለቀቃቸው ተሰምቷል፡፡
ይህም ሆኖ ፕሬዚዳንቱ በሙስና ወንጀል ያስጠረጠራቸው፣ ከጀርመኑ የስፖርት ትጥቅ አምራች ፑማ ኩባንያ የጨረታ ውጤት ጋር በተያያዘ የቀረበባቸው ቅሬታ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ፑማን ጨምሮ ሌሎችም ትጥቅ አምራቾች በተወዳደሩበት ጨረታ፣ 830 ሺሕ ዶላር መደለያ በመቀበል የፑማን የጨረታ ውጤት ውድቅ አድርገዋል፡፡ ለተቀናቃኙ ቴክኒካል ስቲል ኩባንያ ጨረታውን አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ቆይተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አህመድ ይህንን ውንጀላ ሲያስተባብሉ ቢቆዩም በ69ኛው የፊፋ ጉባዔ ለመታደም ወደ ፈረንሣይ ባቀኑበት ወቅት ነበር በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው በነፃ መለቀቃቸው የታወቀው፡፡
‹‹ውሳኔዎች በሙሉ በጋራና ግልጽነት በሰፈነበት አግባብ ነው የተወሰኑት፤›› በማለት የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለዋል፡፡ ፊፋም ራሱን እንዲህ ካሉ የወንጀል ተግባራት ማፅዳቱን በማስታወቅ የሚስተር አህመድን መታሰር በማስመልከት ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡት የፈረንሣይ መርማሪዎችን ጠይቆ ነበር፡፡