Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትመድኃኒት ያልተገኘለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ መቋጫው ምንድን ነው?

መድኃኒት ያልተገኘለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ መቋጫው ምንድን ነው?

ቀን:

የኢትዮጵያ ስፖርት አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት መዋቅሩን በቀያየረ ቁጥር አብሮ ሲቀየር፣ የራሱ የሆነ ስያሜና ቁመና እንዲሁም ተቋማዊ ቅርፅ ሳይኖረው ለዓመታት ዘልቋል፣ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከብዙዎቹ ስፖርቶች የሰዎችን ቀልብ በመሳብ ብቻ ሳይሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው እየታመነበት የሚገኘው እግር ኳስ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ እግር ኳስ በኢትዮጵያ የተወዳጅነቱን ያህል ውጤታማ አልሆነም፡፡ ይባስ ብሎ በዘረኝነት ‹‹ቫይረስ›› ተበክሎ ለሰዎች ሕይወትና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል፡፡ በችግሩ መንስዔና መፍትሔው ላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የዳሰሳ ጥናቶችና ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ የተለወጠም ሆነ የተገኘ አዲስ ነገር ሳይኖር ፕሪሚየር ሊጉ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ የመደረጉ ዜና ይፋ ሆኗል፡፡

‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ መርሐ ግብሩ ሊጠናቀቅ የሦስት ሳምንት ጨዋታ ዕድሜ ሲቀረው መቋረጡ ‹‹ተገቢ›› ነው፣ ‹‹አይደለም›› በሚል የፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ የከፍተኛና የብሔራዊ ሊግ  ክለቦች በፌዴሬሽኑ ውሳኔ አሁንም ከስምምነት ይልቅ ልዩነታቸው እንዲሰፋ ምክንያት መሆኑ አልቀረም፡፡ መቋረጡን የሚደግፉት ክለቦች አሁን ያለው የውድድር አካሄድ (ፎርማት) በአጠቃላይ እግር ኳሱን መነሻ በማድረግ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልና ዘረኝነት እንዲባባስ ከማድረጉ ባሻገር ክለቦችን ለከፋ የፋይናንስ ውድቀት፣ እንዲሁም ለእግር ኳሱ ዝቅጠት መንስዔ በመሆኑ፣ የስፖርቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን አጋጣሚው የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ሊጉ መቋረጥ የነበረበት ጊዜ እንዳለፈ፣ ይሁንና ቀደም ሲል ከነበረው አንፃር በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሥጋት የሚጋሩት ሆኖ የፌዴሬሽኑ የአሁኑ ውሳኔ ግን ግምት ያስገባው ችግሩን ሳይሆን የአንዳንድ ክለቦችን ተፅዕኖ በመሥጋት እንደሆነ በመግለጽ ውሳኔውን እንደማያምኑበት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

- Advertisement -

በእግር ኳስ ረዳት ዳኝነት ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ ለ21 ዓመታት ከፌዴራል እስከ ኢንተርናሽናል የዳኝነት አገልግሎት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ፍሬው ይኼይስ ኃይለ ሥላሴ ከኢትዮጵያ ሚሌኒየም ጀምሮ በፈረንሣይ መኖሪያቸውን ቢያደርጉም፣ ከዚያ በፊት በስፖርቱ ባሳለፉባቸው ዓመታት ውስጥ መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎች እንዳሳለፉ ሁሉ መጥፎ የሚባሉ ክስተቶችን ማለፋቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በእግር ኳስ ውስጥ የሚታየውና የሚሰማው ከእግር ኳሱም አልፎ ‹‹አገራችን›› ብለን ለምንናፍቃት ኢትዮጵያ ሳይቀር ሥጋት እየሆነ ስለመምጣቱ ያምናሉ፡፡

እሳቸውን ጨምሮ አምስት ወንድሞቻቸው መርሻ ይኼይስ፣ ዘውዴ ይኼይስ፣ ባህሩ ይኼይስና ገብረየስ ይኼይስ ሁሉም የእግር ኳስ ዳኞች በመሆን ማሳለፋቸውን የሚናገሩት አቶ ፍሬው፣ ዓመተ ምሕረቱንና ቀኑን ቢዘነጉትም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና ከደሴ ከተማ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ አራተኛ ዳኛውን ጨምሮ ሦስት ወንድማማቾች ያጫወቱበትን አጋጣሚ አሁን ቢሆን ሲሉ ትውስታቸውንና ትዝብታቸው ያጋራሉ፡፡ በጊዜው ሦስት ጊዜ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ኮከብ ዳኛ በመሆን መመረጣቸውን የሚናገሩት አቶ ፍሬው፣ ዳኛ ከመሆናቸው በፊት ተጨዋች የመሆን ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በወቅቱ እንደነመቻል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አየር ኃይል፣ መብራት ኃይልና ከዚያም ትግል ፍሬና ዕርምጃችን፣ ወደ ክፍለ ሀገር ወጣ ስንል ከኤርትራ እስከ ድሬዳዋ የነበረው እግር ኳስ እንዲህ እንደ አሁኑ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ቴክኒካዊ ክህሎቱም ሆነ ብቃቱ የተሟላ ስለነበረ ያንን ሁሉ ሰብሮ ለመግባት የተለየ ችሎታን መታደል የሚጠይቅ እንደነበርም ያስረዳሉ፣ ምስክርነቱን በወቅቱ የነበሩ ሊሰጡ እንደሚገባም ያክላሉ፡፡

በወቅቱ ለነበረው አስደሳችና ውጤታማ እግር ኳስ ከፌዴሬሽን አመራሮች እስከ ጨዋታው ሥሪት (ፎርማት) ብቃት ካልሆነ እንደ አሁኑ በ‹‹ብሔር ካባ›› ሳይሆን በብቃት የሚከናወን መሆኑ ነው የሚሉት አቶ ፍሬው፣ ‹‹ውድድሮች በየአካባቢው ስለሚከናወኑና ጠንካራ ፉክክር ስለሚኖር ለምሳሌ ድሬዳዋን ወክሎ ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚወከሉትን ሁለት ወይም ሦስት ቡድኖችን ለይቶ ማውጣት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ለማስታወስ ከድሬዳዋ ባቡርና ኮተን፣ ከአዲስ አበባ መቻል፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና ወይም መብራትና ሌሎች ሊሆኑ ይችላል፣ ከአስመራ ኤርትራ ጫማ፣ ቀይ ባህርና የመሳሰሉት ጠንካራውን የአካባቢያቸውን ፉክክር አሸንፈው ስለሚመጡ ሻምፒዮናው የሚጠበቀው በጉጉት ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድኑም የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በመሆኑ ታላላቆቹ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ካልሆነ በዞን ደረጃ በጠንካራነቱ የሚጠቀስ ነበር፤›› በማለት አሁን ያለውን አካሄድ አይቀበሉትም፡፡

ምክንያቱን አስመልክቶ የቀድሞ ረዳት ዳኛ ሲያብራሩም፣ ‹‹በእርግጥ ፕሪሚየር የሚለው አካሄድ እግር ኳስ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከተደራሽነቱ በሻገር ፖለቲካውና ዘረኝነቱ በሙያው ውስጥ ስለገባ የታሰበውን ያህል እንዲራመድ አላስቻለውም፡፡ ከክለብ አወቃቀር እስከ አመራር መሠረት አድርጎ የሚነሳው ማንነትን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድ ሰው የቱንም ያህል የተማረ ቢሆን ብሔሩን ከማስቀደም ወደ ኋላ አይልም፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ደቡብ ከሆነ ቅድሚያውን ለደቡቦች፣ አማራውም ሆነ ትግራዩ በተመሳሳይ በመሆኑ፣ ይህም በሌሎችም ዘርፎች እየተዛመተ አሁን ላይ የክልል ቡድኖች ሲዋቀሩ ችሎታና ብቃት ቀርቶ ቅድሚያ ለአካባቢው ተወላጅ በሚል ቀመር ሁሉም ነገር ብልሽትሽቱ እንዲወጣ መንስዔ ሆነ፡፡ ‹ብልህ ከራሱ ሞኝ ከራሱ› እንዲሉ አሁንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከስህተቱ ተምሮ ወደ ትክክለኛው አካሄድ መመለስ እንዳለበት ይሰማኛል፤›› ይላሉ፡፡

በሚኖሩበት ፈረንሣይ ከትልልቆቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጀምሮ እንደነ ባርሴሎና፣ ባየር ሙኒክ፣ ፓሪስ ሴንት ዤርመንና ሌሎችም ሲጫወቱ የመመልከት ዕድሉ እንደገጠማቸው የሚናገሩት አቶ ፍሬው፣ ‹‹ስለ ጥንካሬያቸው ሲነገር የምንሰማው ተክለ ሰውነት እየተባለ ነው፡፡ በተክለ ሰውነት ደረጃ ከሄድን ብዙዎቹ ከኢትዮጵያውያን ምንም ልዩነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ታዲያ ልዩነቱ ምንድነው ስንል፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በእኛው አገር በነበረው ዓይነት ማለትም በትምህርት ቤቶቻቸውና ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ሳይቀር ማዘውተሪያዎች በበቂ ሁኔታ ስላላቸው ታዳጊዎች እንደየዝንባሌያቸው እንደ ልባቸው መሥራት እንዲችሉ ማድረጋቸው ብቻ ነው፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ቀደም ሲል የነበሩት ሜዳዎችና ክፍት ቦታዎች በግንባታና መሰል መሠረተ ልማቶች አልቀዋል፡፡ የትምህርት ቤቶች፣ የወረዳዎችና የሠራተኞች እየተባሉ የሚታወቁ ቀደምቶቹ ውድድሮች አሁን ላይ ለሠልፍ ካልሆነ እንዲጠፉ ተደርጓል፡፡ ቀደምቶቹ ከዋክብት የሩቆቹን ትተን የቅርቦቹን ብንመለከት ሙሉጌታ ከበደ፣ ገብረ መድኅን ኃይሌ፣ ነፍሱን ይማረውና አሰግድ ተስፋዬና ሌሎችም የተገኙት ከሠፈር ሜዳዎች ነው፤›› በማለት ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ጥናት ላይ ያልተመሠረተ አካሄድና ፖለቲካው ጭምር ለእግር ኳሱ ውድቀት ተጠያቂዎች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ከብሔራዊ ፌዴሬሽን እስከ ክለብ ክልላዊ ስሜት ያለው አወቃቀር በኢትዮጵያ ካልሆነ በሌሎች አገሮች እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ፍሬው፣ ‹‹ውዝግቡም ሆነ ትርምሱ ባልተሠራ ነገር ላይ ነው፡፡ ዝርዝር ነገሩን መናገር ባልችልም በአገሪቱ አሁን ላይ ያለው፣ በብሔርተኝነትና ክልላዊ ስሜት የሕዝብን ሀብት ማባከን አለፍ ሲል ደግሞ ለዓመታት ሰላማዊ የሕይወት መስተጋብር የነበራቸውን ሕዝቦች በቋንቋና በማንነት ተከፋፍለው እንዳይተማመኑና እንዲለያዩ እግር ኳሱ ሽፋን እንዲሆን ተደርጓል፤›› ብለው ያምናሉ፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ እንዲቋረጥ ተደርጓል፣ በዚህም በየደረጃው የሚገኙ ሁሉም ክለቦች ተመሳሳይ አቋምና አመለካከት አልያዙም፣ አንዳንዶቹ የአቶ ፍሬውን አስተያየት የሚጋሩ ሲሆን በሌላ ወገን በተቃራኒው የሚናገሩ አሉ፡፡ የቀድሞ ረዳት ዳኛ አሁን በመከናወን ላይ የሚገኘው የፕሪሚየር ሊጉም ሆነ ሌሎች ሊጎች የተዟዝሮ ጨዋታን ማከናወን ሲጀምሩ ያስቀመጧቸውን ዓላማና ግቦች ምን እንደነበሩ፣ ከዚያ በመነሳት አሁን ላይ ምን ዓይነት ውጤት እንዳስገኘና ጉዳቱን ጭምር በዝርዝር በማስቀመጥና በመነጋገር የተሻለውን መንገድ መምረጥ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ በእሳቸው እምነት የዚህ የተዟዝሮ የጨዋታ መርሐ ግብር ቢቋረጥና እንደ ቀድሞ ተደርጎ፣ ከዚያም የተሻሉት ቡድኖች ተመርጠው በአንድ ማዕከል የሚወዳደሩበት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ አገሪቱን በቀጣይ በአኅጉራዊ መድረክ የሚወክለውን አንድ ቡድን ማቅረብ እንደሚቻል ጭምር አቶ ፍሬው ያምናሉ፡፡ ምናልባት ፎርማቱ ቢቀየር የሚኖረው ጉዳት ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በመዟዟር ሊገኝ የሚችለው ጥቅማ ጥቅም ካልሆነ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አሁን ከሚስተዋለው ሁኔታ በመነሳት ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከንትርኩና ውዝግቡ በፊት የሊጉን ሁኔታና እያስከተለ ያለውን ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ ላይ በግልጽ መነጋገር ችግሩ ምንድነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ሌላው ክለቦች በደንብ ሊያስቡበት የሚገባው አሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት ይቀጥል ቢባል በእያንዳንዱ ክለብ የፋይናንስ አቅም ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ አስገብቶ መመልከት ተገቢ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ደደቢትና  በሌሎችም ክለቦች በፋይናንስ እጥረት ከክልል ወደ ክልል ተንቀሳቅሰው ውድድር ለማከናወን ምን ያህል እያስቸገራቸው መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ስለመሆኑ አቶ ፍሬው ይናገራሉ፡፡ የተዟዟሮው መርሐ ግብር ጉዳቱ ከክለቦችም አልፎ ለእግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች እንዲሁም ሙያተኞች ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው እንዳይሠሩ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው ለመሆኑ የክልል ቡድኖች በሜዳቸው ሽንፈት የሚባለውን ነገር መስማት አለመፈለጋቸው ማሳያ እየሆነ መምጣቱ አቶ ፍሬው ይናገራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ብቃት ያላቸው ዳኞችና ታዛቢ ዳኞች ማፍራት እየተቻለ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ባምላክ ተሰማናን ሊዲያ ታፈሰን በመጥቀስ ሊከራከሩ የሚችሉ ይኖሩ ይሆናል፡፡ እነዚህ ልጆች ለዚህ ውጤት የበቁት በግል ጥረታቸው ለመሆኑ ከዚህ ቀደም ክንዴ ኃይሉ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ይገኛል፤ በዳኝነት ኢትዮጵያን በትልቅ ደረጃ ሊያስጠራ የሚችል አቅም እያለው ከመንገድ እንዲቀር የተደረገው በሽኩቻ ነው፡፡

ከፍተኛ የሆነ የሙያተኛ መጠላለፍ እንዳለ የሚናሩት አቶ ፍሬው፣ ይህ በራሱ ለእግር ኳሱ ዕድገትም ሆነ ሙያተኞች በበቂ ሁኔታ እንዳይፈሩ ሲያደርግ የቆየ አሁንም ያለ አደገኛ ወረርሽን ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዚህ ጉዳይ እጁን በማስገባት ማስተካከል እንደሚጠበቅበትም ያምናሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...