Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሉዓላዊ አገር እንጂ ሉዓላዊ ክልል የለም?

ሉዓላዊ አገር እንጂ ሉዓላዊ ክልል የለም?

ቀን:

የሉዓላዊነት ጉዳይ በፌዴራል ኢትዮጵያ

በቢኒያም መንበረ ወርቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት የዜጎች መፈናቀልን በተመለከተ በፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሉዓላዊ አገር እንጂ ሉዓላዊ ክልል የለም፤›› ማለታቸው በግራም በቀኝም መልስ አስተናግዶ ነበር ያለፈው፡፡ በዚሁ ጋዜጣም ታዋቂው የሕግ ምሑርና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ ‹‹ሉዓላዊነት ምንድነው? ምንስ አይደለም?›› በሚል ርዕስ እጥር ምጥን ያለች ጠቃሚ ጽሑፍ አስነብበውን ነበር፡፡ በጽሑፉ የቀረቡት ቁምነገሮች ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል የጽሑፉ ቁጥብ መሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ ሌሎች ተገቢ ነጥቦችንና አነጋጋሪ ጉዳዮችን አፍታቶ ለማየት የረዳው አይመስልም፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተሞከረው ዘርዘር ያለ አቀራረብም ቀድመው የተነሱ ሐሳቦችን እንዳሉ ሳይደግም፣ ነገር ግን በዚህ ረገድ ያልተዳሰሱ መልኮችን ማሳየት፣ ይሁነኝ ብሎም አከራካሪ ጉዳዮችን በመነካካት ጤናማ ውይይት ለማጫር የሚሞክር ነው፡፡

ሉዓላዊነት እንደ ጽንሰ ሐሳብ

ሉዓላዊነት (Sovereignty) እና የሉዓላዊ አገረ መንግሥት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ከአውሮፓ የመካከለኛው ዘመን መቋጫ ላይ ብቅ ያለና በተለይም እ.ኤ.አ. ከ1648 የዌስትፌሊያ ሰላም ወዲህ፣ ተቀባይነቱ ያደገ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በመልክዓ ምድራዊ ሽፋኑም ከአውሮፓ ተነስቶ በመላው ዓለም ሁለንተናዊ ቅቡልነት ለመቀዳጀት የበቃ ነው፡፡ መርሁ ከሌሎች መካከል በፖለቲካ ፍልስፍና፣ በዓለም አቀፍ ሕግና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ የማይናቅ ቦታ አለው፡፡ የዘመናዊ አገረ መንግሥት አንዱ መገለጫም ተደርጎ የሚቀርብበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡ ይህን ያህል ዕድሜ ራሱን ከተለወጡ ሁኔታዎች ጋር እያስማማ እስከ ሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ህልው ሆኖ የቆየው መርህ የዕድሜውንና በለወጥ የማለፉን ያህል በዘፍጥረቱ፣ በምንነቱና በመገለጫዎቹ ላይ ዓይነተ አንድ አረዳድ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ነገረ ሉዓላዊነትን በሚገባ የመረመሩ እንደ ሮበርት ጃክሰን ዓይነት ምሑራን ግን ጽንሰ ሐሳቡ ከፈለቀበትና ከዳበረበት ታሪካዊ ሒደት ሳይነጠል ከተፈተሸ፣ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው የሚታዩ የማይነጣጠሉ ሁለት መልኮችን ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ገጽ አንድ አገረ መንግሥት በዳር ድንበሩ ውስጥ ብቸኛ ወሳኝ የበላይ ሥልጣን አካል መሆኑን (Supremacy/Internal Sovereignty) የሚያስረግጥ፣ በሌላ በኩል በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ከሌሎች አገሮች አኳያ ነፃ አገር ሆኖ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውቅያኖስ ላይ የመቅዘፍ ሁኔታን (Independence/External Sovereignty) የሚገልጽ ነው፡፡ በአጭሩ የተሟላ ውሳጣዊ የበላይ ሥልጣን (ከውጭ ጣልቃ ገብነት የተጠበቀ) እና እንደ አገር እኩል ነፃ ተዋናይ ሆኖ የመታየት ተብሎ ሊጠቃለል ይችላል፡፡

ይሁንና ጽንሰ ሐሳቡ ብዙ ነቃፊዎች ያሉትና አጠያያቂ እየሆነ የመጣ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ካልሆነ በስተቀር በተግባር እንኳን ደሃ አገሮች ሀብታሞቹና ጉልበተኞቹም ፍጹማዊ ሉዓላዊ ሥልጣን አለን ለማለት የሚደፍሩበት ሁኔታ የለም የሚሉ ትችቶች ይሰማሉ፡፡ አገረ መንግሥታትን ከላይ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግሎባላይዜሽን፣ ከጎን ሲቪል ማኅበረሰብና ገበያው (Market)፣ ከታች ደግሞ የአካባቢና የዘውጌ እንቅስቃሴዎች ተቀናቃኝ ሆነው ያጣበቡበት ሁኔታ ብሔረ መንግሥት (Nation-State) ሉዓላዊ ተደርጎ የሚወሰድበትን ሞዴል ጥያቄ ውስጥ ከቶታል የሚሉም አሉ፡፡ ዘመኑ ስለድኅረ ሉዓላዊነት ዓለም ወይም ቅርፀ ለውጥ ስላደረገ ‹‹ሉዓላዊነት›› የምናወራበት ወቅት ነው ብለው ያወጁ፣ በቁምነገር የሚታዩ ጸሐፍትም ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ ስቴፈን ክሬዝነርን የመሰሉ ምሑራን ደግሞ ሉዓላዊነት የሚባለው መርህ ላይ ጀምበር ማዘቅዘቅ የጀመረችው አሁን እንደሆነ አድርጎ መተንተን፣ ከታሪካዊ እውነታው ጋር የማይጣጣም መሆኑንና ከጥንስሱ ጀምሮ ቢሆን በተግባር ሲሸራረፍ የኖረ የተደራጀ ማስመሰል (Organized Hypocrisy) እንደሆነ በመግለጽ ያጣጥሉታል፡፡

በእርግጥም ዓመታዊ በጀታቸውን በልመና የሚያሟሉ፣ ለብድርና ለዕርዳታ ሲሉ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚቀርብላቸውን የፖሊሲ ክኒን እየመረራቸውም ቢሆን የሚውጡ፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ከግዙፍ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች ትዕዛዝ የሚወርድላቸው፣ የውጭ ግንኙነታቸውን አቅጣጫ የአበዳሪና የለጋሾቻቸውን ፊት እያዩ የሚወስኑ፣ በአገር ውስጥ በሁሉም አካባቢ ሥልጣናቸውን ማስረገጥና ውጤታማ አስተዳደር ማስፈን ያልቻሉ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን ሕዝባዊ አገልግሎት ማዳረስ የማይሳካላቸው መንግሥታት ያላቸው አገሮች ሉዓላዊነታቸው ከወሬ ማሳመሪያነት ያለፈ ሚና እንዳለው መጠየቅ የተገባ ይመስላል፡፡

በአንፃሩ እነዚህ የአገረ መንግሥት መዳከምን ማዕከል አድርገው የሚቀርቡ ትችቶች በሥልጣን (Authority) እና በኃይል (Power) መካከል ያለውን ልዩነት ያላገናዘቡ ተደረገው ራሳቸው ይተቻሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ከበድ ያሉ ተግባራዊ ጥያቄዎች ይነሱበት እንጂ በአንፃራዊነት በተግባር ያለውን ያህል፣ እንደ ኖርማቲቭ መርህም በአገሮች የእርስ በርስ ግንኙነት ውስጥ የማይናቅ ሚና መጫወቱ ላይ እምብዛም ልዩነት የለም፡፡ በዘመናዊ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት ኅልዮት ውስጥም መርሁ ድርሻ አለው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርም ግንባር ቦታ የተሰጠው ነው፡ በመሆኑም ከላይ በመግቢያው የተነሳው ኮርኳሪ አጋጣሚ በሌለበት ሁኔታ እንኳ ቢሆን ትችቶቹና ጥያቄዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ጽንሰ ሐሳቡን በንድፈ ሐሳብ ደረጃና በአገረ መንግሥታት ሥሪት ውስጥ ያለውን ቦታ መፈተሽ የተገባ ነው፡፡

በሉዓላዊነት ላይ የሚደረግ ውይይት ከሌሎች መካከል ማን ነው ሉዓላዊ? የሉዓዊነት ባህሪያት ምንድናቸው? ሉዓላዊነት የማይከፋፈል/ፍፁማዊ ነውን? ሉዓላዊ ሥልጣን የት ነው የሚያርፈው/የሚመነጨው? የሚሉት ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮችን በመተወር ረገድ ዦን ቦዲን፣ ቶማስ ሆብስ፣ ጆን ሎክ፣ ዦን ዣክ ሩሶ በቅድሚያ የሚጠቀሱ ፈላስፎች ናቸው፡፡ በተለይ በዦን ዣክ ሩሶ በሚገባ ቅርፅ ይዞ እንደተቀመረ የሚወሳው የሕዝብ ሉዓላዊነት (Popular Sovereignty) ጽንሰ ሐሳብ የሉዓላዊነት አንዱ አንጓ ሲሆን፣ ከዴሞክራሲና ከዘመናዊ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት ጋር በጊዜ ሒደት ጥብቅ ትስስር ማዳበር የቻለ ነው፡፡ የሕዝብ ሉዓላዊነት የአገረ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ምንጭ (ባለቤት) የሚሾመው፣ የሚሽረውም የመጨረሻ ሉዓላዊ ዳኛ ሕዝብ ብቻ ነው የሚለውን መርህ የሚወክል ነው፡፡ ሉዓላዊ ሥልጣን ከላይ (ም) ይመነጫል ከሚሉትም ፈላስፎች በተቃራኒ የቆመ ሐሳብ ነው፡፡

ሉዓላዊነት በፌዴራል ሥርዓት

ዕውቁ የፌዴራሊዝም ሊቅ ዳንኤል ኤላዛር ሉዓላዊነት የፌዴራሊዝም ጉዳይ መሆኑን ይጠይቃል፡፡ በእሱ እምነት የፌዴራል መርህ ለዘመናዊ የሉዓላዊነት ሐሳብ አማራጭ ሆኖ የመጣና አለፈ ሲልም ጽንሰ ሐሳቡ ላይ የተቃጣ ነቅናቂ ጥቃት ነው፡፡ በእርግጥ የኤላዛርን ሐሳብ በመስመሮች መሀል ንባብ ስንፈትሸው ትኩረቱ አጠቃላይ የሉዓላዊነት ጽንሰ ሐሳብ ከመሆን ይልቅ፣ በተለይም በዦን ቦዲን የተተለመውንና ጠንካራ አገረ መንግሥታዊነትን፣ ፈላጭ ቆራጭ፣ ፍጹማዊና በጥብቅ የተማከለ የ‹‹ሉዓላዊነት›› ጽንሰ ሐሳብ የሚተች ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ የፌዴራል መርህ ይዞት መጥቷል የሚለው አማራጭ ሐሳብም ቀደም ሲል ‹‹ሕዝባዊ ሉዓላዊነት›› ተብሎ ከተዋወቀው ሐሳብ ጋር ‹‹ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ›› ነው፡፡ ‹‹በፌዴራል ሪፐብሊክ ውስጥ ሉዓላዊነት ሁሌም የሚያርፈው ሕዝብ ላይ ነው፡፡ ሉዓላዊ የሆነው ሕዝብ እንደ አስፈላጊነቱ ኃይል (Power) ሊከፋፈልና ሊወከል (Delegate) የሚችል ቢሆንም፣ ሉዓላዊነት ግን ኢተነጣጣይ የሕዝብ ይዞታ ሆኖ ነው የሚቆየው፤›› ብሎ ሲጽፍ ይህንኑ አረዳድ እያንፀባረቀ ከመሆን አያመልጥም፡፡

ሮበርት ጃክሰን በበኩሉ በየትኛውም ዓይነት ሥርዓተ መንግሥትና የመንግሥት ቅርፅ ውስጥ የአገረ መንግሥታት ሉዓላዊነት መሠረታዊ ባህሪይ አይቀየርም፣ ውስጣዊ የበላይነትና ውጫዊ ነፃ አገርነት የሁሉም መገለጫ ነው ሲል ይከራከራል፡፡ ሉዓላዊነት የተፈለገው ዓይነት ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ዘዴ የሚቆምበት የሕግና የፖለቲካ መሠረት በመሆኑ፣ ሥርዓተ መንግሥታትና የመንግሥት ቅርፅ (ዘውዳዊም ይሁኑ ሪፐብሊካዊ፣ አምባገነንም ይሁን ዴሞክራሲያዊ፣ ፌዴራላዊም ይሁኑ አሀዳዊ) የአገረ መንግሥቱን የበላይ ሥልጣንን (Supremacy) በሚያደራጁበት፣ መልክና ቅርፅ በሚያሲዙበት መንገድ ካልሆነ በስተቀር በሉዓላዊነት ቁልፍ መገለጫዎች ላይ ልዩነት አይፈጥሩም፡፡ በእሱ እምነት ከሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የፌዴራል ሕገ መንግሥቶች በአንድ የተለየ ጉዳይ ላይ የሚኖር የበላይነት (Supremacy) በየትኛው የመንግሥት እርከን ላይ እንደሚያርፍ ከመወሰን ያለፈ ሥራ አይሠሩም፡፡ ይህ ነጥብ በርካታ የጉዳዩ አስተያየት ሰጭዎች የሚስማሙበትን በአንድ አገረ መንግሥት አንድ ሉዓላዊነት ነው ሊኖር የሚችለው፣ ያም ሉዓላዊነት የማይከፋፈልና ምሉዕ ነው ወደሚለው ሐሳብ ነው የሚወስደን፡፡ አንዳንዶች ጠንከር አድርገው እንዳስቀመጡት አገረ መንግሥታት ሉዓላዊ ይሆናሉ ወይም አይሆኑም፣ በሁለቱ መሀል ከፊል ሉዓላዊነት፣ ግማሽ ሉዓላዊነት ብሎ ነገር የለም ነው ክርክሩ፡፡ ይህ አረዳድ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች በእንግሊዝኛው ‹‹ስቴት›› የሚለውን መጠሪያ ያገኙ ክልሎች እንደ ሉዓላዊ ወይም የሉዓላዊነት ተካፋይ መሆን የሚችሉበት መንገድንም ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ዝግ የሚያደርግ ነው፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን ሉዓላዊነትን ከፌዴራል ሥርዓት ጋር አያይዞ ማንሳት ያልተለመደ አይደለም፡፡ ዘመናዊው ፌዴራሊዝም ነባሩን የአገረ መንግሥት ሞዴል እሳቤዎችና መሠረቶች በመጋፋት አዲስ ዓይነት ሥርዓት ሆኖ ብቅ ሲል፣ ሉዓላዊነት የራሱን ቅርፅ የያዘና የሰፋ ተቀባይነት የነበረው መርህ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሉዓላዊነት በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ያለው ቦታ ማነጋገሩ አልቀረም፡፡ በአሜሪካ የፌዴራል ሥርዓት ምሥረታና ዕድገት ውስጥ የታየውም ይኼው ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓት ቀድሞ አሀዳዊና አንድ የተማከለ አስተዳደር የነበረው አገረ መንግሥትን በተለያዩ እርከኖች ሲደለደል፣ ሉዓላዊነት በወሉ (ፌዴራል) መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ይከፋፍላል የሚለው አቀራረብ በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው፡፡ በአንፃሩ ፌዴሬሽኖች ቀድመው ሉዓላዊ ከነበሩ አገሮች ሲመሠረቱ ወይም እንደ አውሮፓ ኅብረት ባሉ የፌዴራል አላባ (ኤለመንት) ባላቸው መዋቅሮችም ኅብረቱ ሲቋቋም፣ አገሮቹ ቀድሞ አላቸው ተብሎ የሚታመነውን ሉዓላዊነት አሳጥቶ ይመሠረታል/ቀንሶ ይወስዳል (Pooled Sovereignty) የሚለው ሐሳብም ይነሳል፡፡ ከዚህም በመነሳት ይመስላል ፌዴራሊዝም ሉዓላዊነትን ለሁለት የሚከፍል የማደራጃ መርህ ነው የሚሉ ብያኔዎችን ሲቀርቡ የምናየው፡፡ በተለይም በአሜሪካ የተመሠረተው የፌዴራል ሥርዓት በመሠረቱ ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነትን›› (Divided Sovereignty) መሠረት ያደረገ ቢያንስ በጅማሬ ዘመኑ ክሌአዊ ፌዴራሊዝም ነበር የሚል ክርክር አለ፡፡ ሥልጣንና ኃላፊነትን በሁለቱ የመንግሥት እርከኖች በሚገባ ዘርዝሮ በመከፋፈል፣ ሁሉም የራሳቸውን ራስ ገዝነት ጠብቀው እንዲሠሩ ያለመ ክሌአዊ ፌዴራሊዝም (Dual Federalism) ሆኖ መነሳቱ ላይ ብዙም ውዝግብ ባይኖርም፣ ከጽሑፍ መሽከርከሪያ ነጥብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውን ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› ጉዳይ ዘርዘር አድርጎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

ቀድመው የነበሩ የቅኝ ግዛቶችን ወደ አንድ አገርነት የቀየረው የአሜሪካ ፌዴራሊዝም በጣም ልል ኮንፌዴራላዊ አወቃቀር እንዲፀና በሚፈልጉና የበለጠ የተዋሀደ ኅብረት እንዲመሠረት በሚፈልጉ ኃይሎች መካከል በተደረገ ፍትጊያ የተፈጠረ ሥርዓት መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህ ድባብ ውስጥ የፌዴራሊዝሙ አባቶች የሉዓላዊነትን ጉዳይ ሊያስተናግዱት የሞከሩበት መንገድ የፌዴራል መንግሥቱና ስቴቶችን (Governments) በአንድ በኩል፣ አጠቃላይ አገሩ (Union) በሌላ በኩል ነጣጥሎ በማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ መንግሥቱ ሕግ የማመንጨት ሥልጣን የተሰጣቸው የፌዴራሉ መንግሥትና ስቴቶች በራሳቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ሉዓላዊነት አላቸው፡፡ የኅብረቱ አገረ መንግሥት ሉዓላዊነት ግን የመጨረሻ ሉዓላዊ አካል የሆነው ሕዝብ ይሆናል እንደ ማለት ነው፡፡

ቻርለስ ሜሬየም የተሰኘ ደራሲ ‹‹የሉዓላዊነት ኀልዮት ታሪክ ከሩሶ ጀምሮ›› በሚል መጽሐፉ እንዳሰፈረው ይህ የመመቻመች ውጤት ‹‹ሉዓላዊነት አይከፋፈልም›› የሚል ተመሳሳይ አቋም ባላቸው፣ ነገር ግን በአንድ በኩል በመላው የአሜሪካ ሕዝብ የሚያርፍ አንድ አጠቃላይ ሉዓላዊነት ነው ያለው፣ የአባል ስቴቶች ሉዓላዊነት ንዑስ መንግሥታዊ (Governmental) ሉዓላዊነት ነው በሚሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል ሥርዓቱ ያለው ሉዓላዊነት አንድ ነው ይህም የአባል ስቴቶች ዘንድ የሚያርፈው ብቻ እንደሆነ በሚያምኑ ኃይሎች መካከል ውጥረት ምክንያት ብዙ ሳይሰነብት ቀረ፡፡ ውዝግቡ በቀዳሚዎቹ አሸናፊነት እልባት ያገኘው ከእርስ በርሱ ጦርነት በኋላ ነበር፡፡

ቀደም ሲል እንደ ተጠቆመው ሉዓላዊነት አይከፋፈልም የሚለው አረዳድ በርካታ ደጋዎችና ጠንካራ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረት ያለው ቢሆንም፣ አንዳንዶች ከዚህ የሚቃረነውን ሐሳብ በተግባራዊ ምክንያት የሚጠቀሙበት፣ ተገቢነቱንም የሚሞግቱለት አሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ሁለት ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶችን (‹‹የአገር ሕዝብ››ና ‹‹የክልል ሕዝብ›› (የኋለኛው በቀዳሚውም እንደሚካተት ልብ ይሏል/የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥት) እንደሚፈጥር ተደርጎ የሚቀርብበት ሐሳብ በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሐሳቡን ቀደም ሲል የቀረቡትን ሁለቱን የሉዓላዊነት ገጾች አያሟላም ብሎ መዝጋት የሚቻል ቢሆንም፣ በብያኔው ላይ ጥያቄ በማንሳት ብቻ ክርክሩ ውድቅ የሚደረግበትን አግባብ ለመድፈን አፍታቶ ማየቱ የተገባ ነው፡፡

ይህን ክርክር የሕዝብ ሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ስናየው ሁለት ህፀዎች መንቀስ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው የክልሉ ሕዝብ ‹‹ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት›› እንደሆነ የሚነገርላቸው ክልላዊ ሥልጣኖች፣ በአንድ አገራዊ የፌዴራል ሕገ መንግሥት ተደንግገው የሚገኙና ከምሉዕ ሉዓላዊ ሥልጣን የሚቆነጠሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም የእነዚህ ሥልጣኖች ምንጭ የጠቅላላው የአገሩ ሕዝብ መሆኑ ታውቆ ያደረ በመሆኑ፣ በክልል ሕገ መንግሥት ሌላ ‹‹ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት›› መፍጠር አዲስ ሥልጣን በሌለበት ሁኔታ ቀድመው ለተፈጠሩና ባለቤት ላላቸው ሥልጣኖች አዲስ ሐሳባዊ ‹‹ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት›› መፈብረክ ከመሆን አያመልጥም፡፡

በተጨማሪም ክልሎች በክልላዊ ወሰናቸው ውስጥ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች ላይ በተግባርም በንድፈ ሐሳብም ‹‹ምሉዕ ሥልጣን›› ባለቤት አለመሆናቸው ልብ ሊባል  ይገባል፡፡ ሥልጣናቸው በግዛቱ ክልል ውስጥ የተገደበ ቢሆንም፣ በግዛቱ ክልል ውስጥ በተሰጣቸው ኃላፊነት ብቻ ነው ሕግ ማውጣትም፣ መተግበርና መዳኘትም የሚችሉት፡፡  ከክልሎች ጎን ለጎን የፌዴራል መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን በክልሎች ወሰን ውስጥ የራሱን ኃላፊነት ይወጣል፡፡ በመሆኑም የክልሎች ወሰን በመሠረቱ የክልሎች የሥልጣን ሕጋዊነት የሚያከትምበት መስመር ነው፡፡ ወሰኑን በመላው አገር የሚንሰራፋ ሥልጣን ካለው የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር አንፃር ካየነው ትርጉም አልባ ከመሆን አያልፍም፡፡ 

የፌዴራል መንግሥቱ ከክልሎች በተለየ በመላው አገር መልክዓ ምድር የማይገድበው ሥልጣን ይኑረው እንጂ፣ ሥልጣኑ ግን እንደ ክልሎች ሁሉ በሕገ መንግሥት ተቆጥረው በተሰጡት ጉዳዮች ላይ የተገደበ መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ ቀደም ሲል በቀረበው ሀተታ ውስጣዊ ሉዓላዊነት ብለን የጠቀስነውን የሉዓላዊነት አንዱ ገጽታ የሚመለከት ሲሆን፣ ውጫዊ በተመለከተ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ የፌዴራል ሥርዓቶች የውጭ ግንኙነት ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ ሙሉ ሥልጣን በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ክልሎች ምንም ሚና እንደሌላቸው መረዳትም ይገባል፡፡ ከዚህ በተነሳም ሉዓላዊ አገሩን ወክሎና ሆኖ የሚታየው የፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ በመሆኑም ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ሁለቱም የመንግሥት እርከኖች በተሰጣቸው ሥልጣን ራስ ገዝ ናቸው እንጂ፣ ሉዓላዊ ናቸው ማለት ቀደም ሲል ስለ ‹‹ሉዓላዊነት›› ምንነት ከተነሳው ሐሳብ ጋር ዓይን ለዓይን የሚተያይ አይሆንም፡፡

እውነት ነው፣ ክልሎች በሕገ መንግሥት በተሰጣቸው ሥልጣን የበላይ ናቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱም በተመሳሳይ፣ የአካባቢ አስተዳደሮችም ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና በተሰጣቸው ሁኔታም እንዲሁ፡፡ እውነት ነው፣ በአግድሞሽ የሥልጣን ክፍፍልም የአስፈጻሚው ሥልጣን ጣልቃ የማይገባበት የራሱ ሥልጣን ነው፣ የሕግ አውጭውም የዳኝነቱም ዘርፍ እንዲሁ፡፡ እነኝህ ሁሉ ሥልጣኖች ግን በመሠረቱ ሕዝብ ባለቤት የሆነባቸው የአገረ መንግሥት ሉዓላዊነት ቅርፆች እንጂ በራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣን ያይደሉ፣ ገባሪዎቻቸውንም ‹‹ሉዓላዊ›› ሊያስኙ የማይችሉ ናቸው፡፡ በአነጋገር ክልሎች በተሰጣቸው ሥልጣን ‹‹ሉዓላዊ›› ናቸው ወይም የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ተብሎ ሊጠቀስ ቢችል እንኳ፣ ይህን አምታች የቋንቋ አጠቃቀም ቀደም ብሎ ከቀረበው የ‹‹ሉዓላዊነት›› ጥብቅ ጽንሰ ሐሳባዊ ፍች ጋር ማያያዝ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡

በእርግጥ እዚህ ላይ በጽንሰ ሐሳቡ ዕድገት ውስጥ ሉዓላዊነት ከሥልጣኑ ይዘት (Content) እንጂ፣ ከሥልጣኑ መጠን (Extent) አንፃር መታየት የለበትም የሚል ሐሳብም የቀረበበት አጋጣሚ እንደነበር ማንሳት ይገባል፡፡ የዚህ ሐሳብ አስኳል ምንም እንኳ መጠኑ የተገደበ ቢሆንም የክልል መንግሥታትና የአካባቢ መስተዳድሮች በተሰጣቸው ሥልጣን ያላቸው ቁጥጥር፣ በይዘቱ ገደብ የማይቀመጥለትና ሉዓላዊ በመሆኑ ሉዓላዊነትን የሚካፈሉ ተደርገው ቢቆጠሩ ትክክል ነው የሚል ነው፡፡ ይህንን ክርክር ተችተው ተቀባይነቱን በአጭር እንዲቀጭ ያደረጉት የንድፈ ሐሳብ ቀማሪዎች፣ ሉዓላዊነት ከሥልጣኑ ይዘት ጋር የተያያዘ መሆኑ ላይ ጥያቄ አያነሱም፡፡ የእነሱ ትችት ግን ሉዓላዊነት የተገደበን ሥልጣን በበላይነት ከመያዝ ባሻገር ራሱ ገደቡን ማስቀመጥን ሊያካትት እንደሚገባ አጥንኦት የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም በይዘቱ ሉዓላዊ የሆነ ሥልጣን ያለው ሕገ መንግሥት ያቆመው ኃይል እንጂ፣ በሕገ መንግሥት የተሸነሸነ ሥልጣንን ተግባሪ ሆነው የተገኙት አካላት አይደሉም እንደ ማለት ነው፡፡

ከላይ ከቀረበው ሉዓላዊነትን ከፌዴራል ሥርዓት አንፃር የሚያስስ ሀተታ በመነሳት፣ ቢያንስ ሁለት መደምደሚያዎች ላይ መስማማት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› እንደ ጽንሰ ሐሳብ የፌዴራሊዝም፣ እንደ ሥርዓተ መንግሥት የሁሉም ፌዴሬሽኖች መገለጫ ነው ብሎ መደምደም ያለ ጥርጥር ስህተት መሆኑ ላይ ነው፡፡ ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የፌዴራሊዝምና የፌዴሬሽን ብያኔዎችና ዋና መገለጫዎች አካል ሆኖ የማናገኘውም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ በተግባርም በርካታ ፌዴሬሽኖች ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› መገለጫ ተደርገው ሊቀርቡ የሚችሉ ምልክቶችን በማያሻማ ሁኔታ የማይቀበሉ ሕግጋተ መንግሥታት ላይ፣ መመሥረታቸውም ፌዴራል መሆን ሉዓላዊነት መክፈልን ያስከትላል የሚል ክርክርን ፉርሽ የሚያደርግ ነው፡፡

ሁለተኛው መደምደሚያ ደግሞ በንድፈ ሐሳባዊ ሀተታ የተከፋፈለ ሉዓላዊነት የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል መተንተን የሚቻል ቢሆን እንኳ፣ በተግባር የሚመሠረቱ ፌዴራል ሥርዓቶች የፖለቲካ ኀልዮት እስረኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ለተግባራዊና መሰል ሌላ ፍላጎታቸው ወይም ‹‹ሉዓላዊነትን ይከፋፈላል›› የሚል አረዳድ ተገቢ ነው ብሎ በማመን ሉዓላዊነትን የተከፋፈለ አድርገው ሊያቀርቡት፣ ወይም ሉዓላዊነት በፌዴሬሽኑ መሥራች አባላት ላይ የሚያርፍ አድርገው በሕግጋተ መንግሥታቸው ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› ንድፈ ሐሳባዊ መሠረት የለውም ብሎ መከራከር እንጂ፣ ‹‹የተከፋፈለ ሉዓላዊነት›› መገለጫችን ነው የሚሉ ፌዴራል ሥርዓቶች ሊኖሩ የሚችሉበት ዕድል ዝግ ነው ብሎ መደምደም ስህተት ነው የሚሆነው፡፡

ሉዓላዊነት በፌዴራል ኢትዮጵያ

ሉዓላዊነትን ከፌዴራሊዝም ጋር በማገናኘት የተነሱት ነጥቦች ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል እያንዳንዱ ፌዴሬሽን የራሱ የሆነ ዘፍጥረት፣ ርዕዮተ ዓላማዊ መግፍኤ፣ አወቃቀርና ታሪካዊ ዕድገት ያለው ከመሆኑ አንፃር ‹‹ሉዓላዊነት››ን በተመለከተ ያላቸው የሕግ ፍልስፍናም አንድና ያው ነው ብሎ ግምት መውሰድ ለስህተት ይዳርጋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቶች ሉዓላዊነትን የተረዱበትን መንገድ ለመገንዘብ ሕገ መንግሥታቸውን፣ በሒደት የዳበሩ ተግባራትና አድማሳዊ ተቀባይነት ያገኙ የሕግ ፍልስፍናዎቻቸውን መዳሰስ ጠቃሚ ነው፡፡ የዚህ ንዑስ ርዕስ ሙከራም ሉዓላዊነት ከፌዴራል ሥርዓት ጋር ተያይዞ የተነሳው አጠቃላይ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አወቃቀርና አሠራር ጋር ምን ያህል እንደሚገጣጠም መፈተሽና በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ተገቢ መልስ መሻት ነው፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ‹‹ሉዓላዊነት›› የሚለው ቃል ዘጠኝ ጊዜ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሉዓላዊነትን በተዘዋዋሪ መልኩ የሚገልጹ ወሳኝ ቁም ነገሮችን የያዙ አናቅጽም አሉ፡፡ በቅድሚያ መወሳት ያለበትና የጽሑፉ ማዕከል የሆነውን ጉዳይ በቀጥታ የሚያነሳው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8 ነው፡፡ ‹‹የሕዝብ ሉዓላዊነት›› የሚል ርዕስ የተሰጠው አንቀጽ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው›› ብሎ በመደንገግ፣ የሉዓላዊ ሥልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው የሚለውን ቀደም ሲል የሕዝብ ሉዓላዊነት ተብሎ የቀረበውን የሉዓላዊነት አረዳድና የዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ልማድን ተከትሏል፡፡ ይህ ሉዓላዊ አካል የኢትዮጵያ ሕዝብ ተብሎ አይጠቀስ እንጂ፣ ዓላማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት ማስረገጥ መሆኑ ግልጽ ይመስላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ይፋዊ ማብራሪያም በግልጽ ይህን ሐሳብ ነው የሚያንፀባርቀው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ እንደተቀመጠው ‹‹ዊ ዘ ፒፕል››ን የተካው ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብብሕዎች›› በዚህ አንቀጽም ሲደገም፣ ኢትዮጵያን ‹‹ብሔረ ብዙ›› (Multinational) አድርጎ ዳግም ከመበየን (Redefine ከማድረግ) ባሻገር ሁሉም ‹‹ብብሕዎች›› በተናጥል ሉዓላዊ ናቸው ለማለት እንደፈለገ አድርጎ መውሰድ (ቢያንስ ከዚህ አንቀጽ ጋር በተያያዘ) ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያን ሕዝብን ተክተው፣ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነው እያንዳንዳቸው በተናጥል ሳይሆን በጋራ (“None of ‘Nations, Nationalities and Peoples’ Alone, But all Taken Together”) የኢትዮጵያ ‹‹ብብሕዎች›› የሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ናቸው እንደ ማለት ተደርጎ ቢቆጠር ትክክል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ነው፣ ይህ የሥልጣን ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የኢትዮጵያ ‹‹ብብሕዎች›› ድምር ነው ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ አንቀጽ 8 (3) ሥልጣኑን በምርጫ ውክልናና በቀጥታ ተሳትፎ እንደሚተገብሩት ማመልከቱ ቀደም ተብሎ ከተጠቀሰው የሕዝብ ሉዓላዊነት ጽንሰ ሐሳብ ጋር የተናበበ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ አንቀጽ ጋር ተያይዞ ‹‹ብብሕዎች›› በተናጠል ‹‹ሉዓላዊ›› ናቸው ተብሎ የሚቀርበው ክርክርን ለመቀበል  አስቸጋሪ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ የማያከራክርና በማንም የሚታወቅ ነጥብ ሳያነሱና አጽንኦት ሳይሰጡ ማለፍ ለርዕሰ ጉዳይ ፍትሕ መንፈግ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መሠረት ሁሉም የኢትዮጵያ ‹‹ብብሕዎች›› ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በቀላሉ አገር የመሆንና በማያጠያይቅ ሁኔታም ሉዓላዊነትን ያለ አንዳች ቅደመ ሁኔታ የሚቀዳጁበትን ‹‹መብት›› በኪሳቸው ይዘው እንደ ተቀመጡ ብዥታ ሊኖር አይገባም፡፡ በአንቀጽ 39 የተካተተው የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለው መብት ‹‹ብብሕዎች››ን ሉዓላዊ ሊያደርጋቸው ባይችል እንኳ፣ ‹‹መጣሁ መጣሁ›› የሚሉ ‹‹ዕጩ ሉዓላዊ›› አድርጓቸዋል ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ማለት ብዙ ግሳንግስ ያሉት ራሱ አነጋጋሪ መርህ ሲሆን፣ ከሉዓላዊነት ጋር በተለይም ውሳጣዊ ሉዓላዊነት ተብሎ ከቀረበው የሉዓላዊነት ገጽ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለው ነው፡፡ ይሁንና ለ‹‹ብብሕዎች›› የተሰጠው መብት በተግባር በየደረጃው ራስን በማስተዳደር የሚገለጽ፣ ትንሽ ቢጋነን ውስጣዊ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን በመሆኑ፣ ከተፈለፈለ የሉዓላዊነት ጫጩት ሊሆን የሚችል ሁኔታን ከመፍጠር አልፎ ‹‹ብብሕዎች››ን ሉዓላዊ ያደርጋቸዋል ብሎ ለመከራከር አያበቃም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከቀረበው የሉዓላዊነት ብያኔና የፌዴራል ሥርዓትና ሉዓላዊነት ግንኙነት ሀተታ አንፃር ከታየም፣ ‹ብብሕዎች››ን ሉዓላዊ ሊያደርግ የሚዳዳው ክርክር ድክመት ጠጋግነው ሊያቋቁሙት ቢሞክሩ አቅም የሚያንሰው ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡

ጉዳያችን የክልል ሉዓላዊነት ጥያቄ ሆኖ ሳለ የ‹‹ብብሕዎች››ን ሉዓላዊነት የተመለከቱ ሐሳቦችን ለማንሳት የምንገደደው፣ በቀደሙት ሁለት አናቅጽ እንደተቀመጠው በሕገ መንግሥቱ የሉዓላዊነት ጉዳይ ከ‹‹ብብሕዎች›› ጋር ተሳስሮ በመሥፈሩ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር ‹‹ክልልም፣ ብሔርም ነን›› የሚሉ ክልሎች በመኖራቸውም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ይጠቀሳሉ፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ሁለት የተለያዩ መሥራች አሀዶች ያሉት ይመስላል፡፡ የፌዴሬሽኑ አባል እንደሆኑ በግልጽ የተጠቀሱት ክልሎች (አንቀጽ 47) በአንድ በኩልና በሕገ መንግሥቱ መግቢያና በዋናው የሕገ መንግሥቱ አካል በገደምዳሜና በቀጥታ እንደ መሥራች የተጠቀሱት ‹‹ብብሕዎች›› ናቸው፡፡ እነኝህ ሁለት አካላት የተለያየ ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ እንደተሰጣቸውም እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ በአንቀጽ 39 የተጠቀሱት መብቶች በቀጥታ ክልሎችን አይመለከቱም፣ ለ‹‹ብብሕዎች›› በተናጠል የተሰጡ ናቸው፡፡ ለሕዝብ ብዛት የተሰጠው ተጨማሪ ዋጋ እንዳለ ሆኖ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሠረቱ ‹‹ብብሕዎች›› ውክልና የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣንን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤቱ ሥልጣኖችም ‹‹ብብሕዎች›› በወኪሎቻቸው በኩል በጋራ የሚወስዷቸው ናቸው፡፡ በአንፃሩ የክልሎች ሥልጣኖች በተለይም በአንቀጽ 52 ተዘርዝረው ተደንግገዋል፡፡ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታም ከዝርዝር ያመለጡ ሥልጣኖችም ወደ እነሱ የሚወድቁ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ሚና እንዲኖራቸው የተደረጉት ክልሎች ናቸው፡፡

እዚህ ላይ  በተለየ ትኩረት ሊታዩ የሚገባቸው ከዘውጌ ማኅበረሰብ ጋር የተያያዘ ስያሜ ያላቸውና በትርክትም ሆነ በክልላዊ ሕገ መንግሥት የአንድ ዘውጌ ማኅበረሰብ ክልል ተደርገው የሚቀርቡት ናቸው፡፡ እነኝህ ‹‹ክልልም ብሔርም ነን›› የሚሉ ክልሎች በክልል ደረጃ የተመሠረቱ ‹‹ባለ አንድ ብሔር›› (Mono-National) መንግሥታት ተደርገው የሚታዩበት ሁኔታ የተለመደ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ክልሎች ግን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በመሠረቱ ትርጉም ባለው መልኩ ዘውገ ብዙ (Multi-Ethnic) ናቸው፡፡ ክልላዊ ተቋማትም ዘውገ ብዙ በሆነ የክልሉ ሕዝብ የተመረጡና የተቋቋሙ መሆናቸው ጥያቄ አይነሳበትም፡፡ ምናልባትም በአንድ ብሔር አባላት ብቻ በተመረጡ ሰዎች የተመሠረተ መንግሥታዊ ተቋም ከሐረሪ ሕዝብ ምክር ቤት ውጭ ሌላ የለም፡፡ ሌሎቹ በዘውገ ብዙ ማኅበረሰብ ተመርጠው በአብዛኛው ሕዝብ ስም የሚጠሩና ‹‹ውክልናችንም ለብዙው ብቻ ነው›› ለማለት የሚዳዳቸው ናቸው፡፡

ለምሳሌ የሲዳማ ምክር ቤት በሐዋሳና በዞኑ የሚኖሩ የሌሎች ዘውጌ ማኅበረሰብ አባላትም ጭምር ተወካይ ነው፡፡ የጨፌ ኦሮሚያም የክልሉ ሕዝብ በሆኑ አማራዎች፣ ጉራጌዎችና ተጋሩ ጭምር የተመረጠ ነው፡፡ የክልል ትግራይ ምክር ቤትም ከሌሎች መካከል የኩናማና የኢሮብ ማኅበረሰቦች ውክልና ያለው ነው፡፡ ክልሎች በሕገ መንግሥታቸው ‹‹ሉዓላዊ ሥልጣን የአንድ ብሔር ነው›› ማለታቸውና ራሳቸውን ‹‹ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት›› ብለው መሰየማቸው ይህን ያፈጠጠ ሀቅ  ሊፍቀው አይችልም፡፡  እግዜር ይስጠውና የፌዴራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥትም ክልሎችን ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ብሎ አያውቃቸውም፡፡ ‹‹ክልል›› ብቻ ብሎ ነው የሚጠራቸው (አንቀጽ 47)፡፡ ይሁንና በተግባር እነዚህ ክልሎች የአንድ ዘውጌ ማኅበረሰብ ክልል ተደርገው የሚታዩብት ሁኔታ የደደረ ሲሆን፣ በውጤቱም እነኝህ ክልሎች ለክልሎች የተሰጠውን ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለ‹‹ብብሕዎች›› የተሰጡ ሥልጣኖችንም ጠቅልለው እንደ ያዙ ነው የሚቆጠሩት፣ ራሳቸውንም የሚያዩትም፡፡ ይህ ጉዳይ በሚገባ ለብቻው መታየት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሕገ መንግሥቱም ክልሎችን ሉዓላዊ የሚያደርግና ከዚሁ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ አንቀጽ ባለመኖሩ ከተነሳው ርዕሰ ጉዳይ አንፃር ‹‹ክልልም፣ ብሔርም ነን›› የሚሉት ክልሎች፣ ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ነን በማለታቸው ምክንያት ከሌሎቹ በይፋ ዘውገ ብዙ ከሆኑት ክልሎች በተለየ በ‹‹ብሔር›› በኩል የሚቀዳጁት ሉዓላዊነት አለመኖሩን አስቀምጦ ማለፍ ይገባል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊነትን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጡት ሌሎች አናቅጽ የሚሰጡን አጠቃላይ ሥዕል ላይ የተለየ ዓይነት ወይም የተከፋፈለ ሉዓላዊነትን እንድናስብ የሚያደርግ ነጠብጣብ አናገኝም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ የተቀመጡት ሐሳቦችም ፌዴሬሽኑ የተመሠረተበትን አግባብና ዓላማ ከማስቀመጥ ባለፈ፣ የተመሠረተው ፌዴሬሽን ሉዓላዊነት ላይ የሚሉት ያን ያህል ነገር የለም፡፡ ስለውጭ ግንኙነት መርህ የሚያስረዳው አንቀጽ 86፣ ስለአገር መከላከያ መርህ የሚያትተው አንቀጽ 87፣ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነግገው አንቀጽ 93 ሥር የምናገኛቸው ንዑሳን አናቅጽ በማያሻማ ሁኔታ ስለመደበኛው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አንድ ሉዓላዊነትን ነው የሚያትቱት፡፡ ሕገ መንግሥቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ ፈትሸን የተለየ ዓይነት ሉዓላዊነት አረዳድ ለማስተዋወቅ የሞከረበትን አግባብም አናገኝም፡፡ ክልሎችን በተመለከተም ከኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ከላይ በሀተታው ካቀረብነው የተለየ ተደርጎ የሚወሰድበት ባህሪይ የለውም፡፡ በእርግጥ የክልል ሕገ መንግሥታት ስለሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ማመልከታቸው ‹‹ሉዓላዊ›› ሊያሰኛቸው ይችላል የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ከሞላ ጎደል በመዋቅር ብቻ ያለና በተግባር ሙት ሆኖ ከመሰንበቱ የተነሳ፣ የክልል ሕገ መንግሥቶች ይዘት ከፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንፃር በሚገባ የሚፈተሽበት ዕድል ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አልታየም፡፡ እንዲህም ሆኖ ሕግጋተ መንግሥቱ ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ሲቀዱ ሳያላምጡ እንዳለ የገለበጡት እንጂ፣ ‹‹የተራቀቀ›› የሉዓላዊነት ዓይነት ለማስተዋወቅ ይሁነኝ ብለው ያደረጉት ነው ብሎ ለመውሰድ ያዳግታል፡፡ እነሱ ሉዓላዊነት ብለው የገለጹት በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ያላቸውን የበላይነት እንጂ፣ ጥብቁን የሉዓላዊነትን ባህሪይ ያገናዘበ አለመሆኑ ደጋፊ የሕግ ፍልስፍና በጉዳዩ ላይ ቀድሞም ሆነ ተከትሎም አለመዳበሩ የሚያሳብቀው ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑም ‹‹ብብሕዎች››፣ ራሳቸውን ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ብለው የሚጠሩ ክልሎችም ወይም ዘውገ ብዙ ክልሎች ሉዓላዊ ተደርገው የሚቆጠሩበት፣ ወይም የሉዓላዊነት ተካፋይ (ተጋሪ ማለት አይደለም) ሁኔታ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለማጠቃለል በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንድ ኢትዮጵያ የምትባል ሉዓላዊ አገረ መንግሥት ስትኖር፣ የዚህች አገረ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትም ሕዝብ ነው (በሕገ መንግሥቱ አነጋገር የኢትዮጵያ ‹‹ብብሕዎች›› ናቸው) የሚል መንፈስ ያለው ሐሳብን ያዘለ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ክልሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እነ ኬንያ ካላቸው ሉዓላዊነት ጋር በአቻነት የሚቀመጥ ሉዓላዊነት የሌላቸው መሆኑን፣ በመካከላቸው ያለው ወሰንም በሉዓላዊ አገሮች መካከል ካለው ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ መደምደም ትክክል ነው የሚሆነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌዴራል ጥናቶች የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በትሬንቶ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...