Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሕገወጥ ደላሎች ይታቀቡ!

የገበያውን ጤና የሚነሱ የዋጋ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ መሠረታዊ ከሚባሉ ሸቀጦች ጀምሮ እስከ ፋብሪካ ውጤቶች ከወትሮው በተለየ አኳኋን የዋጋ ጭማሪ እየታየባቸው ነው፡፡ የሰብል ምርቶች፣ አልባሳትና መጫሚያ፣ የቤት መገልገያ ዕቃዎችና ማስዋቢያዎች፣ መድኃኒትና መሰል ሸቀጦች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ዕድገት ጤናማነት ጎሎታል፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ወርኃዊ የሸማቾች ጠቋሚ መመዘኛ አኃዞችም ይህንኑ እያረጋገጡ ነው፡፡

የአብዛኛዎቹ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ መንግሥትም በዚህ አስተሳሰብ በተለይ ‹‹ስግብግብ ነጋዴዎች›› እያለ የሚጠቅሳቸው ለዋጋ ንረት ተጠያቂ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ይሁንና አነስተኛ የዋጋ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ይኼ ነው የሚባል ምክንያት ሊቀርብላቸው የማይችሉ ምርቶች ሁሉ ዋጋቸው እየጨመረ መጥተዋል፡፡ ለወትሮው በብዙ ችግር የተበተበው የግብይት ሥርዓቱ በሽታው እንዲባባስበት የሚያደርግና ሆን ተብሎ የሚፈጸም የገበያ ደባ እንዳለ መዘንጋት የለብንም፡፡ ከወትሮ የተለየ የምርት እጥረት በሌለበት ወቅት፣ እንዲሁ በአቦ ሰጥ ዋጋ በመጨመር ገበያ እያተራመሱና ሸማቹን እያሸማቀቁ እንዲማረር የሚያደርጉ ሸፍጠኞች ተበራክተዋል፡፡ አንዳንድ ምርቶች ላይ የዋጋ ለውጥ ሊኖር የሚችልበት እውነተኛ ምክንያት እንደሚኖር አያጠያይቅም፡፡ ችግሩ ግን ምክንያታዊ ጭማሪ ሊደረግባቸው በሚችሉ ምርቶች ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ግን ቅጥ ያጣ እየሆነ ገበያውን የጋለ ብረት ማስመሰሉ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት የዋጋ ጭማሪዎች አንፃራዊ ጤናማነት በሚታይባቸው የግብይት ሒደቶችንም እየበከሉ የተረጋጋውን በማደፍረስ የሚያደርጉት ጫና እየተበራከተ ነው፡፡ ገበያው ውስጥ የሚፈጥረውን መተረማመስና የሸማቾችን ምሬት ከቁብ ሳይቆጥሩ ከገዙበት ዋጋ በላይ ትርፋቸውን አክለው ብቻ ሳይሆን፣ ህዳጉን ከመቶ በመቶ በላይ  ለጥጠው፣ ያላወጡትን ወጪ ሰማይ አንረው ዋጋ የሚያጋግሉ፣ ያልተፈጠረውንና የሌለውን የምርት እጥረት ልክ እንደ መዓት እያወሩና እያስወሩ ገበያውን የሚያተራምሱ ደላሎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ሕግ የማያውቃቸው የዋጋ ፈላጭ ቆራጭ ደላሎች የንግድ ምዝገባ የሌላቸው፣ ባልዋሉበትና ባላዩት፣ በማያውቁት ምርትና አገልግሎት ላይ የዋጋ መዛባት እንዲፈጠር በማድረግ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የማይታጠፍ ረዥም እጅ ያላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ደላሎች በየከተማው ስርቻ ተበራክተዋል፡፡  

ያለ ከልካይና ተመልካች ገበያውን እየበረዙት ኖረዋል፡፡ አሁንም ይኖራሉ፡፡ ቤት ኪራይና ሽያጭ፣ የዕቃ ኪራይና ሽያጭ፣ የቦታ፣ የሥራ ሠራተኛ አገናኝ በመሆን ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ የገዥኛ ሻጭ ራስ ምታቶች በርካታ ናቸው፡፡ የእነዚህ ደላሎች ዋጋ ከፍተኛ ለመሆኑ አንዱ ማሳያው፣ ከሰሞኑ በነዳጅ ጭማሪ ሰበብ እንዲሁም በኃይል እጥረት ሰበብ ገበያው እንዲጋጋል ያደረጉበት ክስተት እየታየ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ብናይ እንኳ፣ ከምርቱ መነሻ ቦታ ላይ ጭማሪ ሳይኖር መድረሻው ላይ ግን ዋጋው የተቀጣጠለበት የተደረገበት ምክንያት የደላሎች እጅ ለመሆኑ አስረጅ አያሻውም፡፡

ምንም ዓይነት ምርት የማያመርቱና እሴት የሚጨምሩበት እንቅስቃሴና ተግባር የሌላቸው፣ ነገር ግን መደበኛው ነጋዴም ሆነ አምራች ከሚያገኘው የበለጠና የተትረፈረፈ ‹‹ትርፍ›› የሚያጋብሱ፣ ሱቅ ተከራይቶ የሚቸረችረው ነጋዴ እየሠራ በሚያገኘው ገቢ እንደ ልቡ ጥሪት መቋጠር ሲቸግረው፣ ስግብግቦቹ ‹‹የአየር ባየር›› ነጋዴዎችና ግብር የማያውቃቸው እነዚህ አካላት፣ ልጓም ያልተበጀላቸው ጡንቸኞች እየሆኑ ነው፡፡ ደላሎች የማይገቡበት ቦታ የለምና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተፈጠረ ነው የተባለውን አጋጣሚ በመጠቀም የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎችን ጭምር እንዲያዝ በማድረግ ከእጥፍ በላይ ዋጋ እንዲሸጥ ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪው ቅናሽ በነበረበት ወቅት የገባ ዕቃ ሁሉ ለስንጥቅ ትርፍ እንዲመች ከገበያ ተሸሽጎ ቀን እየተጠበቀ በሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ግብይትና ሸማች ግራ እስኪገባቸው የሚጦዙት በእንዲህ ያሉት መታወቂያ አልባ ነጋዴዎች ምክንያት ሆኗል፡፡

በእርግጥ ከሰሞኑ የመሬት ወረራ ላይ ተሳታፊ በመሆን፣ የከተማዋ የመሬት ሊዝ ዋጋ ላይ ሳይቀር ተፅዕኖ በማሳደር የመሬት ዋጋ አልቀመስ እንዲል በማድረግ አባሪና ተባባሪ የተባሉ የመንግሥት ኃላፊዎች እስር ቤት እየወረዱ ነው፡፡ መሬትን በሕገወጥ መንገድ በመያዝ እንዲሸቀጥ ሆነ ብለው፣ ሸንሽነው በመሸጥ በማሻሻጥና መሬትን እንደ ሸቀጥ በመቸብቸብ ዓይነተኛ ሚና የነበራቸው ደላሎች ስለመያዛቸው ግን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ በመሬት ይዞታ ላይ የሚፈጸመው ደባ፣ የመሬት ዋጋ ሰማይ ጠቀስ የሆነበት ምክንያት ይኸው የደላሎች ገደብ አልባ ውንብድና መሆኑ የቆየ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ስለዚህ ይወሰዳል የተባለው ዕርምጃ መልካም የመሆኑን ያህል ሕገወጥ ደላሎችም ‹‹እኔን ያየህ ተቀጣ›› የሚሉበት ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች  በርካታ የግብይት ሒደቶች እየተሰገሰጉ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱትንም በመለየት ዕርምጃ መውሰድ ግድ ይላልና፣ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ለዚህ ሥራ ከእንቅልፉ ነቅቶ ይሰለፍ፡፡

 ከሕገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ባሻገር፣ በኃላፊነት መሥራት ጡር የሆነባቸው ነጋዴዎችም አንዳንድ ምርቶችን ሆ ብለው በማከማቸትና ከገበያው በመሰወር  ለሚፈጥሩት ጡዘትና ምስቅልቅል በሕግ ለመጠየቅ የሚያበቃቸው ሥርዓት በመኖሩ፣ ይህንን ሕግ በአግባቡ በማስፈጸም ገበያውን ማረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ምርት ሸሽጎ ማስቀመጥ በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር እንደመሆኑም፣ በዚህ ተሳታፊ የሆኑ ሕገወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች ሊቆነጠጡ ይገባቸዋል፡፡

የጤፍ ዋጋ ለምን ጨመረ? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ትንሽ ጥናት ቢደረግ ምላሹ በሚገባ እንደሚገኝ እየታወቀ ይህንን ለመከላከል የሚያስለችል ሥራ ግን እምብዛም አልተሠራም፡፡ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸውን ምርቶች በማጥናትና ዋጋቸውን ማንና እንዴት እንዳወጣው በመለየት የችግሩን ምንጭና መንስዔ ማወቅ ይቻላል፡፡ ከሰሞኑም የተለያዩ የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች በገበያ ውስጥ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በደላሎች የተፈጸመ ነው ብለዋልና ይህ ከታወቀ ዕርምጃው ለምን አልተወሰደም? እንዲህ ያለውን የቁጥጥር ሥራ የመሥራት ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት የሥራ መሪዎች አሁን ያለውን ችግር እንደሚገነዘቡ ማሳወቃቸው ብቻ በቂ ባለመሆኑ ገበያውን ለማረጋጋት ዕርምጃቸውም ይታይ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት