የትራንስፖርት ባለንብረቶች ጫና ተፈጥሮብናል አሉ
በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ380 እስከ 400 ኩንታል የሚጭኑ ከባድ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በሙሉ ከጂቡቲ ወደብ ማዳበሪያ እንዲያነሱ ብሔራዊ ግዳጅ የተሰጣቸው በመሆኑ፣ ሌሎች በርካታ ዕቃዎች ወደብ ላይ በመከማቸታቸው ጥያቄ ቀረበ፡፡ የማዳበሪያ ግዥ በዕቅድ እየተከናወነ ባለመሆኑ፣ በየዓመቱ በሌሎች ገቢ ዕቃዎችና በከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስንዴ፣ ፓልም የምግብ ዘይት፣ ብረትና የመሳሰሉ በብትን የሚገቡ ምርቶችና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን የያዙ ኮንቴነሮች በወደብ ተከማችተው ይገኛሉ፡፡
ከማዳበሪያ ውጪ በተለመደው ሁኔታ ገቢ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ባለመሆኑ በገበያ ውስጥ የምርት እጥረት እንዲኖር ከማድረግ በላይ፣ ባለኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎቻቸው በመዘግየታቸው ምክንያት ለችግር መዳረጋቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በተያዘው የምርት ዘመን 11 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ይፈለጋል፡፡ ይህንን ማዳበሪያ ለመግዛት የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 2010 ዓ.ም. ላወጣው ጨረታ፣ ለአቅራቢዎች ሥራው የተሰጠው በታኅሳስና በጥር ወር ነበር፡፡
በተለይ 11 መርከቦች ማዳበሪያ ከየካቲት ጀምሮ ይዘው የመጡ ሲሆን፣ የትራንስፖርት ባለሥልጣን የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. 42 የሚጠጉ የከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበራትን ጠርቶ ሙሉ ትኩረታቸውን ማዳበሪያ በማንሳት ላይ ብቻ እንዲሆን ብሔራዊ ግዴታ ጥሎ ነበር፡፡
የትራንስፖርት ባለንብረቶቹ ከመጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ በተለይ ከ380 እስከ 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በዚህ ሥራ ላይ አሠማርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሌሎች ዕቃዎችን ከጂቡቲ ወደብ በማንሳት ላይ የሚገኙት ከ350 ኩንታል በታች የመያዝ አቅም ያላቸው ውስን ከባድ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የትራንስፖርት ማመላለሻ ባለንብረቶች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመንግሥት ተቋማት ባለመናበባቸው ብቻ ለሚፈጠር ችግር ከፍተኛ ጫና እያደረሰባቸው ነው፡፡ ባለንብረቶቹ እየደረሰባቸው ያለውን ጫና ሲገልጹ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ማዳበሪያ የሚያነሱለትን ድርጅቶች ሲመርጥ ተጫርተው ያሸነፉ ድርጅቶች በሰጡት የማሸነፊያ ዋጋ እንዲያነሱ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መሄድ ወደ ማይፈልጉበት መንገድ ሁሉ በግዳጅ ሰበብ እንዲሄዱ እንደሚገደዱ ያክላሉ፡፡
በአጠቃላይ ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ውል አስገዳጅ እንጂ የገበያ ዋጋን ያማከለ አለመሆኑን የሚናገሩት የትራንስፖርት ድርጅት ባለቤቶች፣ የነዳጅ ዋጋ ቢቀያየርም ውሉ ይህንን ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ የትራንስፖርት ታሪፍም ሆነ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ዋጋ ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር እያደረሰባቸው መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ማዳበሪያ ለማንሳት ጂቡቲ ሲገባም እስከ ስምንት ቀናት መቆም ግድ እንደሚል፣ አገር ውስጥ አድርሶ ለማውረድ ደግሞ የተመቻቸ መጋዘን ባለመኖሩ ለተመሳሳይ ቀናት ለመቆም እንደሚገደዱ ይናገራሉ፡፡
‹‹የጫናው ተሸካሚ ሆነን እየኖርን ነው፤›› ሲሉ አንድ የትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የጭነት ትራንስፖርት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ዓለምአየሁ ወልዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራውን በሚያከናውኑት መንግሥታዊ ተቋማት በኩል ያለመናበብ ችግር መኖሩን አምነዋል፡፡
‹‹ማዳበሪያ ከመስከረም ወር ጀመሮ ማምጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የውጭ ምንዛሪ ችግርና በድጋሚ ጨረታ የማውጣት ችግር ስላለ ግዥው እየተፈጸመ ያለው በታኅሳስና በጥር ወር አካባቢ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ኮሚቴ ተቋቁሞ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብ በመንግሥት አቅጣጫ ተሰጥቷል፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት በየካቲት ወር የሰጠው ትዕዛዝ 11 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በግንቦትና በሰኔ ወር ተጠቃሎ እንደሚገባ ነበር፡፡ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ገብቶ እየተከፋፈለ ሲሆን፣ ቀሪው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ገና እየደረሰ በመሆኑ የማንሳቱ ሥራ እስከ ሐምሌ ወር ድረስ ሊገፋ ይችላል ተብሏል፡፡