የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ሲያካሂድና ክስ ሲመሠረትባቸውም አድራሻቸው በደፈናው ‹‹ትግራይ ክልል›› ሲባል የነበሩት እነ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤትን ጠየቀ፡፡
ዓቃቤ ሕግ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ጥያቄ ያቀረበው ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ትግራይ ክልል ብዙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ያሉት ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ክስ የተመሠረተባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ በተቋሙ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ይሠሩ የነበሩት አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልዑል በምርመራም ወቅት ሆነ ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላ፣ አድራሻቸው ‹‹ትግራይ ክልል›› ተብሎ ከመጠቀሱ ውጪ፣ ቋሚ አድራሻቸው በትክክል ስላልተጠቀሰ ሊገኙ አለመቻላቸውን ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ይኼንን የተናገረው ፍርድ ቤቱ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት ተከሳሾች በአድራሻቸው መጥሪያ ደርሷቸው እንዲቀርቡ የሰጠው ትዕዛዝ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ከፌዴራል ፖሊስ የተላከለትን ደብዳቤ በችሎት እንደገለጸው፣ የፌዴራል ፖሊስ ከፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ፣ ትግራይ ክልል ለሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ በፋክስ ልኳል፡፡ የፋክስ መልዕክት የደረሰው በክልሉ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ በሰጠው ምላሽ፣ የተከሳሾቹ አድራሻ ‹‹ትግራይ ክልል›› ከማለት ውጪ ትክክለኛ አድራሻቸውን ማወቅ ስላልተቻለ፣ በቀጣይ ቀጠሮ አፈላልጎ ለመስጠት የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ትብብር እንዲያደርግላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው የሚል መሆኑን ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ የደረሰውን ደብዳቤ ከገለጸ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ የተከሳሾቹን አድራሻ ከምርመራ ጊዜ ጀምሮ ክስ እስከ ተመሠረተበትም ወቅት ማወቅ አልተቻለም፡፡ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ደግሞ ከ12 ዓመታት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ክርክሩ በሌሉበት እንዲካሄድ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሌላው ሰጥቶት የነበረው ትዕዛዝ አንድ የቀረ የማስረጃ ሲዲ አባዝቶ እንዲቀርብ፣ አቶ ሰይፈ በላይ የተባሉ ተከሳሽ ባቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ፣ ዓቃቤ ሕግ የሰጠውን ምላሽና እንዲሁም የምስክሮቹን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃር በአዋጁ በተሰጠው ድንጋጌ መሠረት የሚሰጡት ምስክርነት በዝግ ሊሆን እንደማይገባ ተከሳሾች ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡
ሲዲውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ቀደም ብሎ ከሰጣቸው ሲዲዎች ውስጥ 16ኛው ሲዲ ላይ አብሮ ተካቶ የተባዛ መሆኑን በመናገር በዚያው እንዲያዝለት ጠይቋል፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ብይን የተሠራ ቢሆንም፣ ዳኞች ስላልተወያዩበት በዕለቱ ብይኑን መስጠት እንዳልተቻለ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄና ብይን በተሠራባቸው ሁለት ክርክሮች ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡