ከዘንድሮ በ1.6 በመቶ ብቻ ብልጫ ያለው በጀት ለ2012 ዓ.ም. እንዲፀድቅ ለፓርላማ ቀረበ
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት መቀዛቀዙንና ለነገ የማይባል የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ስትራቴጂ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ። ሚኒስትሩ ይኼንን ያሉት የ2012 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት መግለጫን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዙን የተናገሩት አቶ አህመድ፣ በአገሪቱ የተከሰቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋቶችና የተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን ክፍተት በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተጀመረ አንስቶ ለሦስት ዓመታት የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በአማካይ 8.6 በመቶ እንደነበር፣ በ2010 ዓ.ም. የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት 7.7 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን አምስት ዓመታት ከተመዘገበው የ10.1 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት በእጅጉ ያነሰና ኢኮኖሚው በአንፃራዊነት እየተቀዛቀዘ እንደሚገኝ አመላካች እንደሆነ ለፓርላማው ጠቁመዋል። የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረታዊ ግብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የታለመና ለዚህም ስኬት የኢንዱስትሪ ዘርፉ በየዓመቱ ከ20 በመቶ ያላነሰ ዕድገት እንዲያስመዘግብ በዕቅዱ የተመለከተ ቢሆንም፣ በተለይ ለዚህ መሳካት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚጠበቀው ተጨማሪ እሴቶችን በምርቶች ላይ የመጨመር ዕቅድ መሻሻል ባለማሳየቱ በዘርፉ የሚጠበቀው ሽግግር ሳይሳካ እንደቀረ አስረድተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው በ2010 በጀት ዓመት 5.5 በመቶ የሆነ አዝጋሚ ዕድገት ማስመዝገቡ የታቀደው የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር እንደማይሳካ አመላካች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ጎልብቶ ትርፍ የሆነውን የግብርና ዘርፍ ምርትና የሰው ኃይል እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያፈሩትን የተማረ ወጣት ሥራ ፈላጊ ሊቀበል ባለመቻሉ የታሰበው የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር ዕውን እንደማይሆን በግልጽ እንደሚጠቁም ተናግረዋል።
የወጪ ንግድ ዘርፉ ከ2007 በጀት ዓመት ጀምሮ አፈጻጸሙ እየቀነሰ መጥቶ የገቢ ንግድ ወጪን የመሸፈን አቅሙ በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ 18 በመቶ እንደወረደ፣ ለዚህም የዓለም የሸቀጦች ዋጋ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ዋነኛውን ድርሻ ያበረከተው የውስጥ ችግር መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከልም ተስፋ የተጣለባቸው የመንግሥት ትልልቅ አምራች ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ማምረት አለመቻላቸውንና የሕገወጥ ወጪ ንግድ መስፋፋትን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የውጭ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራቾችን ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ማሟላትና በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሠረታዊ ዕቃዎች አቅርቦትንም ቢሆን ማቅረብ አለመቻሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ይኼንንም ተከትሎ የአንዳንድ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ በማሳየት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአገሪቱ የኤክስፖርት ንግድ መዳከም የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ፣ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ሥጋት ደረጃ በመጨመር ተጨማሪ የልማት ብድር እንዳይገኝና መንግሥት በጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል። በሌላ በኩል የገቢ ንግድ መጠኑ እየቀነሰ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ ይህም የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲቀዛቀዝ፣ በተለይም በታክስ ገቢ ላይ የማይናቅ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አገሪቱ ከታክስ የምታገኘው አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ በ2003 በጀት ዓመት 59 ቢሊዮን ብር፣ በ2007 በጀት ዓመት 165 ቢሊዮን ብር፣ ከ2008 እስከ 2010 በጀት ዓመታት እንደ ቅደም ተከተላቸው 190 ቢሊዮን ብር፣ 210 ቢሊዮን ብርና 235 ቢሊዮን ብር እንደነበር ሚኒስትሩ ያቀረቡት የበጀት መግለጫ ሰነድ ያመለክታል። በ2011 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ ታክስ ይሰበሰባል ተብሎ በበጀት አዋጁ የታወጀው የገቢ መጠን 211 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ባለፉት አሥር ወራት መሰብሰብ የተቻለው 143.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ መረጃው ያሳያል።
በዚህ አፈጻጸም መሠረት በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ቀሪው የታክስ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ መገመት እንደማይቻል የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ይህም መንግሥት ያፀደቀውን የወጪ ግዴታ ለማሟላት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል። በአጠቃላይ የተገለጹት ሁኔታዎች በመንግሥት ገቢም ሆነ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በመሆናቸው፣ የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችን በመንደፍ ችግሩ የሚቃለልበትን ሥልት መዘርጋት ለነገ የማይባል ተግባር መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።
መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በቅርቡ የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕርምጃዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚል አስፈላጊ የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን የያዘ ሰነድ በማፅደቅ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።
ለቀጣዩ የ2012 በጀት ከአጠቃላይ 387.9 ቢሊዮን ብር በላይ ረቂቅ በጀት ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ለዘንድሮ በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከተመደበው በ1.6 በመቶ ወይም በስድስት ቢሊዮን ብር ብቻ ብልጫ እንዳለው መረጃው ያሳያል።
ከዚህ አጠቃላይ በጀት ውስጥ የመደበኛ ወጪ ድርሻ 109.5 ቢሊዮን ሲሆን፣ የካፒታል በጀት ድርሻ ደግሞ 130.7 ቢሊዮን ብር መሆኑን ሰነዱ ያሳያል። ቀሪው 140.8 ቢሊዮን ብር ለክልሎች በድጎማ የሚከፋፈል መሆኑን፣ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ብር በረቂቁ ተደግፎ ቀርቧል።
ፓርላማው የፌዴራል መንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የተመለከቱ ጥያቄዎችን፣ እንዲሁም የፕሮጀክቶች አፈጻጸም አዝጋሚ መሆን ለፋይናንስ ብክነት እየዳረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በቀጣዮቹ ሳምንታት ረቂቅ በጀቱ በፓርላማው የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰፊ ግምገማ ከተካሄደበት በኋላ፣ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ ወር መጨረሻ በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽ ከሰጡበት በኋላ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።