Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኒያላ ስፖርት ክለብ ህልውና በሰኔ ያበቃል ተባለ

የኒያላ ስፖርት ክለብ ህልውና በሰኔ ያበቃል ተባለ

ቀን:

የክለቡ ሜዳ የዳቦ ማምረቻ እንዲገነባበት ተሰጥቷል

ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው የእግር ኳስ ተሳትፎው ብሎም በቦክስ ስፖርት መስክ ያፈራቸው አትሌቶች ለአገሪቱ አይረሴ ባለውለታዎች ነበሩ፡፡ ይህ ክለብ ‹‹ኒያላ ስፖርት ክለብ›› ይሰኛል፡፡

ይህ ክለብ በአሁኑ ወቅት ወደ መፍረሱና በነበር ወደ መቅረቱ ተቃርቧል፡፡ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አጠገብ የሚገኘው የክለቡ የስፖርት ሜዳ በከተማ አስተዳደሩ ለዳቦ ማምረቻነት እንዲውልና የፋብሪካ ግንባታ እንዲካሄድበት በመሰጠቱ መታረስ ጀምሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲፈርሱ ከተፈረደባቸው ክለቦች ተርታ ለመመደብ የቀናት ዕድሜ እንደቀረው የሚነገርለት ኒያላ ስፖርት ክለብ፣ ለህልውናው ማክተም ሰበብ የሆነው ክለቡን የሚያስተዳድረው ኩባንያ ለውጭ ባለሀብቶች በመሸጡ ነው፡፡ የቀድሞ ትንባሆ ሞኖፖል የአሁኑ ብሔራዊ ትንባሆ ድርጅት፣ ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በአንድ ቢሊዮን ዶላር መሸጡ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ውስጥ ውስጡን የኒያላ ስፖርት ክለብ ህልውና ማብቃቱ ሲውጠነጠን ቆይቶ በመጨረሻው ግን እስከ ሰኔ መጨረሻ ብቻ ህልውናው እንደሚቆይ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡

የክለቡ ህልውና ብቻም ሳይሆን፣ የክለቡ ስፖርት ማዘውተሪያና የልምምድ ሜዳም ከወዲሁ አብቅቶለታል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አጠገብ ይገኝ የነበረው ይህ ሜዳ፣ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዳቦና ለዱቄት ፋብሪካ ግንባታ ይካሄድበታል ተብሏል፡፡

በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የተመራ ልዑክ ባለፈው ሳምንት በስፖርት ማዘውተሪያው ሜዳ ላይ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ከሰሞኑ የሜዳው የግብ ብረትና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች በምሽት ተነቅለዋል፡፡

 ይህ ዕርምጃ ያሳዘናቸው የክለቡ አባላትና አመራሮች በሜዳው አቅራቢያ ስንት ክፍት ቦታ ባለበት የክለቡ ነባር ይዞታ እንዳልበረ ፈራርሶ በማየታቸው ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሆነ የክለቡ ህልውና በዚህ አኳኋን ማብቃቱ፣ የስፖርት ማዘውተሪያውንም ማጣቱ በሌላ ወገን፣ የከተማ አስተዳደሩን አድራጎት ጥያቄ ላይ ይጥለዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲስፋፉ፣ ስፖርት መሥራት እንዲበረታታ የሚወተውተው መንግሥት፣ በሌላ ገጽታው ግን ለዘመናት የቆዩ የስፖርት ሜዳዎችን እየማሰ መገኘቱ፣ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ፤›› እንደሚያሰኘው በመግለጽ ቅሬታቸውን ያሰሙት የኒያላ ስፖርት ክለብ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የሌሎች ስፖርት ክለቦች አመራሮች በሜዳው ላይ ተግኘተው የመሠረት ድንጋይ ሲያስቀምጡና እንዲፈርስ ሲደረግም መሳተፋቸውን በመመልከታቸው እጅግ እንዳዘኑ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይለ ሰማያት መርሐ ጥበብ ስለጉዳዩ ከሪፖርተር ተጠይቀው መረጃው እንደሌላቸው፣ ይልቁንም ማዘወተሪያው የሚገኝበትን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን እንድናነጋገር ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደስታ ለማ በበኩላቸው፣ ‹‹ሜዳው የድርጅቱ የራሱ ነው፡፡ የክፍለ ከተማችን ቡድን ውድድር የሚያደርግበት ብቻም ሳይሆን፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመወዳደሪያነት ያስመዘገበው ሜዳ ነው፡፡ የሜዳው ባለቤት ኒያላ ስፖርት ክለብ ለከተማ አስተዳደሩ እንደሰጠው መረጃው ባይኖረንም፣ በወሬ ወሬ እንደሰማነው ከሆነ፣ ድርጅቱ ‹ተለዋጭ መሬት ይሰጠኝና ቦታውን እሰጣለሁ› በማለቱ ሜዳው እንደተሰጠ ሰምተናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ደስታ አያይዘው እንደገለጹት፣ ክፍለ ከተማው ቀደም ብሎ መረጃው ቢኖረው ኖሮ ሜዳውን በብሔራዊ ሊግ በመወዳደር ላይ ለሚገኘው ቡድኑና ለክፍለ ከተማው ወጣቶች ማዘውተሪያነት ለማዋል ሌላ ተለዋጭ ቦታ የሚሰጥበትን አማራጭ ለማቅረብ ፍላጎት ነበረው፡፡ ይሁንና ክፍለ ከተማው ጉዳዩን በዝርዝር ሳያውቀው በድርጅቱና በከተማ አስተዳደሩ ስምምነት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከአቃቂ ቃሊቲ ቡድን በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቡናና የጤና ቡድኖችን ጨምሮ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማዘውተሪያነት የሚጠቀሙበት ሜዳ እንደነበርም ኃላፊው አክለዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ስፖርት ቡድንም በሜዳው አገልግሎት ያገኝ የነበረው በአንድ ጨዋታ እስከ ሁለት ሺሕ ብር እየከፈለ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...