የአሜሪካ አክሪዲቴሽን ድርጅት ከሆነው አናብ አክሪዲቴሽን የፊዚኮ ኬሚካልና ኮንዶም ጥራት ምርመራ፣ በ2011 በጀት ዓመት በ16 የመድኃኒትና ኮንዶም ጥራት ምርመራ ዓይነቶች አይሶ/ISO 17027 ዕውቅና ማግኘቱን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ከሚናወኑ የቁጥጥር ሥራዎች መካከል የጥራት ምርመራ ማከናወን ወሳኝ ሲሆን፣ በ2011 በጀት ዓመት ከአናብ አክሪዲቴሽን ተቋም በ11 የፊዚኮ ኬሚካልና በአምስት የኮንዶም ጥራት ምርመራ ዓይነቶች ዕውቅና ማግኘት ተችሏል፡፡
በአዋጅ 1112/11 ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነት መካከል በመድኃኒቶች ላይ አስፈላጊውን የጥራት ምርመራ በማከናወን ጥራቱን፣ ደኅንነቱን፣ ፈዋሽነቱንና አስተማማኝነቱን በማረጋገጥ የኅብረተሰቡን ጤና የመጠበቅና የማበልፀግ ኃላፊነት የተጣለበት መሥሪያ ቤቱ፣ በ16 ምርመራ ዓይነቶች ዕውቅና ማግኘቱ በ18 መግቢያና መውጭያ ኬላዎች ላይ የሚሠራውን የመድኃኒትና ኮንዶም ድኅረ ገበያ ጥራት ምርመራ አስተማማኝ ያደርገዋል ተብሏል፡፡