Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ500 በላይ ሰዎች በኮሌራ ተጠቅተዋል

ከ500 በላይ ሰዎች በኮሌራ ተጠቅተዋል

ቀን:

በአዲስ አበባ በስምንት ክፍለ ከተሞች ተስፋፍቷል

በአገር አቀፍ ደረጃ 525 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ሲጠቁ 16 ሰዎች ደግሞ በበሽታው መሞታቸውን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በቀጣይ ቀናት እንደሚካሄድና ክትባቱ ሙሉ ለሙሉ ወረርሽኙን መከላከል እንደማያስችል ተገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደገለጹት፣ በወረርሽኙ ከሞቱት መካከል 14 በአማራ ክልል ሁለቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ስምንት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈው ኅብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ይህም ማለት ወደ ሕክምና ተቋማት ሳይመጡ የሕክምና ባለሙያዎች ሳያዩአቸውና ተገቢው ምርመራ ሳይደረግላቸው ነው፡፡ በበሽታው መሞታቸው ሊረጋገጥ የቻለውም ከኅብረተሰቡ የተገኘው መረጃ ከወረርሽኙ ጋር ተቀራራቢነት ስላለው ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሌሎቹ ስድስት ሰዎች የሞቱት ግን ወደ ጤና ተቋማት መጥተውና የጤና ባለሙያ አግኝቷቸው ምርመራ ካደረጉላቸው በኋላ መሆኑን ዶ/ር በየነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀደም ሲል አዲስ አበባ ውስጥ በሦስት ክፍለ ከተሞች ማለትም በአቃቂ ቃሊቲ 12፣ በአዲስ ከተማ 12፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ሦስት ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘው እንደነበር፣ በተጨማሪ በአምስት ክፍለ ከተሞች ማለትም በልደታ ሦስት፣ በቂርቆስ አንድ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አራት፣ በጉለሌ አንድ፣ በአራዳ አራት በድምሩ በስምንት ክፍለ ከተሞች 40 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በጭሮ ወረዳ 58፣ በኦዳ ቡልቱም ወረዳ 125፣ በሚኤሶ 20፣ በቦዴሶ ከተማ 34 በአጠቃላይ 236 ሰዎች፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል በምሥራቃዊ ዞን ክልተአውላዕሎ ወረዳና አዲግራት ከተማ፣ በደቡብ ምሥራቅ ዞን ደጋአ ተንቤን ወረዳ፣ በመቐለ ዙሪያ ሰሜን ክፍለ ከተማ በድምሩ 13 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

የበሽታውን መንስዔ ለማረጋገጥ ከታካሚዎች በተወሰዱ ናሙናዎች ላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በአማራ ክልል ሁለት፣ በትግራይ ክልል ሁለት፣ በኦሮሚያ አምስት፣ በአዲስ አበባ 10 በድምሩ 19 ናሙናዎች ወረርሽኙን ያስከተለው ቪብሮ ኮሌራ የተሰኘ ባክቴሪያ መሆኑን ተረጋጋጧል፡፡ በዚህም መሠረት ወረርሽኙ በተከሰቱባቸው ክልሎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ለማከም የሚያስችሉ በአጠቃላይ 13 ለይቶ የማከሚያ ማዕከላት ተቋቁመዋል፡፡

ከማዕከላቱም መካከል በኦሮሚያ ስድስት (በአዳቡልቱም አንድ፣ በጨሮ ሦስት፣ በሜኦሶ 2)፣ ሲሆኑ በአዲስ አበባ ሁለት (ድል ፍሬ አንድ እና አዲስ ከተማ አንድ)፣ በመቐለ አንድ (አደሃቂ)፣ እንዲሁም በአማራ ክልል አራት (በዋግህምራ ዞን ሁለትና በጠለምት ወረዳ ሁለት) ናቸው፡፡

ወረርሽኙ በተከሰቱባቸው ክልሎች ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የመለየት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ተቋማት መካከል የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከላት፣ የጎዳና ሕፃናት ማገገሚያ ማዕከላትና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እንደተለዩ፣ ክትባቱን ለመስጠትም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በቀጣይ ቀናት  ይከናወናሉ ተብሏል፡፡

‹‹ክትባቱ በተሰጠበት ዕለት ወዲያውኑ መከላከል አይችልም፡፡ የተወሰኑ ቀናት ወይም ሳምንታት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የተከተበው ማኅበረሰብ ከእንግዲህ ወረርሽኙ አይዘኝም ብሎ ራሱን ከቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ማራቅ የለበትም፡፡ የክትባት ባሕርይ ደግሞ  ወረርሽኙን መቶ በመቶ አይከላከልም፤›› ብለዋል፡፡

አንዳንድ ክትባቶች ወረርሽኙን 80 በመቶ ወይም 90 በመቶ መከላከል እንደሚችሉ የኮሌራ ወረርሽኝ ክትባት ግን መከላከል የሚችለው ከ60 እስከ70 በመቶ ብቻ እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የኮሌራ ወረርሽኝ ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ፣ ውኃን እያከሙና እያፈሉ ለምግብ ማብሰያና ለመጠጥ መገልገያ ማዋል፡፡ መፀዳጃ ቤትን በንጽሕና መጠቀም፣ ከተገለገሉ ወይም ከተፀዳዱ በኋላ እጅን በሳሙናና በውኃ በሚገባ መታጠብ  እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ክትባት የሚሰጥበት ቁርጥ ያለ ቀን አልተቀመጠም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የወረርሽኙን ሁኔታ እንዲያጠና ወደ ተለያዩ ክልሎች የተንቀሳቀሰው ቡድን ጥናቱን አጥንቶ መጨረስና የቀረበውም ጥናት መገምገምና በሚገባ መታየት ስላለበት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመጨረስ ደግሞ ትንሽ ጊዜ ያስፈልገል፤›› ብለዋል፡፡

ለኮሌራ ወረርሽኝና ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና ምላሽ ለመስጠት 206 ያህል የጤና ባለሙያዎች ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 72 የጤና ባለሙያዎች ለኮሌራ ወረርሽኝ ምላሽ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከመጋቢት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ 847 ባለሙያዎችን መመደብ ተችሏል፡፡

በሽታውን በቶሎ ለመቆጣጠር የበሽታዎችን መንስዔ በጥናት በመለየትና ናሙናዎችን በላቦራቶሪ በማረጋገጥ ለሁሉም ክልሎች መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች ወደ ሕክምና ጣቢያዎች እንዲከማቹ ተደርጓል፡፡ በዚህም በዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ ለኮሌራና ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና ምላሽ ለመስጠት 134.2 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል፡፡

ከመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦት በተጨማሪ ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ለአአብነትም ለ50 የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ 68 የቅድስት ሥላሴና የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ መምህራን እንዲሁም 20 የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪዎች በድምሩ 138 የቤተ ክርስቲያኒቷ መምህራንና አስተዳዳሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሂዷል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀደም ሲል በአፋር ክልል ተከስቶ የነበረው የትኩሳት ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል ቀብሪ ዳሃር ከተማ መቀስቀሱን የክልሉ ጤና ቢሮ ያሳወቀ ሲሆን፣ ከቦታውም ከተሰበሰቡ አምስት ናሙናዎች በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በሦስቱ ናሙናዎች ላይ ወረርሽኙን ያስከተለው ችኩንጉኒያ ቫይረስ መሆኑ ተረጋጋጧል፡፡ ማኅበረሰቡ ራሱን ከበሽታው ለመከላከል አጎበር እንዲጠቀም እንዲሁም ለትንኞች መራቢያ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን እንዲያስወግድ ኢንስቲትዩቱ ያሳስባል፡፡

ትንኞቹ በቀላሉ ሊራቡ የሚችሉት የወባ ትንኝ መራቢያ በሆነው ውኃ ያቆሩ ቦታዎች፣ ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ በሚኖሩበት ቦታ ላይ መሆኑን ገልጸው ማኅበረሰቡ ውኃ ያቆሩና ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ያሉባቸውን ቦታዎች ማፅዳት፣ ትንኞቹ የሚናከሱት ቀን ላይ ስለሆነ ማኅበረሰቡ ቀን ላይ ሸለብ ሲያደርገው ወይም ሲተኛ አጎበር እንዲጠቀም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...