Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አገሬን ላገለግል መጥቼ ጥቃት ለደረሰባት ኢትዮጵያዊት ምንም አለማድረጌ ያሳስበኝ ነበር›› ወ/ት ማራኪ ተስፋዬ

ወ/ት ማራኪ ተስፋዬ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን በኢንዲያን ስኩል፣ ቀጣዩን ደግሞ አሜሪካ በሚገኝ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ስኮላርሺፕ አግኝታ መማሯን ትገልጻለች፡፡ በትምህርት ቤቱ ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግም፣ የቴአትር ክለብ አባል ሆና የራሷን ባህል አስተዋውቃለች፡፡ ኮሌጅ ከገባች በኋላ “Homeless but Not Hopeless” የሚል ፕሮጀክቷም አስመስግኗታል፡፡ በምትማርበት ኮሌጅ በሚካሄዱ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ ከሚዘጋጁ ምግቦች የተረፈውን ለተቸገሩ እየወሰዱ መስጠት የ”Homeless but Not Hopeless” ተልዕኮ ነው፡፡ ወ/ት ማራኪ እንግዳ በነበረችበት አሜሪካ በርካቶችን በዚህ መልኩ ረድታለች፡፡ ከትምህርት ውጪ ባሉ እንቅስቃሴዎቿ በአቅሟ አገሯን አስጠርታለች፡፡ ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች በምታደርገው ተሳትፎ ቀላል የማይባሉ ሥራዎች ሠርታለች፡፡ በቅርቡ በጀመረችው ጀግኒት ንቅናቄ ደግሞ ከጀርባ ሆና ለውጦች እንዲታዩ ግፊት ታደርጋለች፡፡ ስለ ጀግኒት ተልዕኮና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡የጀግኒት ንቅናቄ እንዴት ተጀመረ?

ወ/ት ማራኪ፡– ጀግኒት የተጀመረችው የእኔ አስተዳደግ የፈጠረልኝን መልካም አጋጣሚዎች ከመረዳት ነው፡፡ ጎበዝና ጀግኒት እንድሆን በዙሪያዬ ያሉ ሁሉ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ዛሬ እንዳወራ ብዙ ነገሮች ተመቻችቶልኛል፡፡ አንዲት ጎበዝ ሴት ከብዙ መሰናክሎች አልፋ የሆነ ደረጃ ላይ ትደርሳለች፡፡ ነገር ግን ስለዚህ ብዙም አይወራም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሴቶች ስም የሚነሳው ከጥቃት ጋር ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ስኬቷም መነሳት አለበት፡፡ ከአሥር ሴቶች መካከል ስምንቱ ቤት ውስጥ ወይም ሥራ ቦታ ጥቃት ያስተናግዱ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች ግን የሚለኩት ከጥቃት አንፃር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ አንቺ ከቤትሽ ተነስተሽ እዚህ እስክትመጪ ያጋጠመሽን ትንኮሳዎችና እንግልቶች ቆጥሬ በዚያ ልለካሽ አልችልም፡፡ ምክንያቱም ያንቺ ጀግንነት ከዚያ የላቀ ነው፡፡ ያንቺን ብርታት እንዴት ነው ማየት የምችለው? አንዲት ጎበዝ የሆነን ነገር ለማሳካት ቀመር አላት፡፡ እኛ ጀግኒት አለመች፣ አቀደች አሳካች ብለን ተነሳን፡፡ አንዲት ጀግኒት የሆነ ቦታ ላይ መድረስ ማለም፣ ማቀድ ከዚያ ማሳካት አለባት፡፡ የራሴን ነገር ያለምኩት ልጅ እያለሁ ነው፡፡ ህልሜ እንዲሳካ ደግሞ ቤተሰቦቼ አስተዋጽኦ አድርገውልኛል፡፡

ሪፖርተር፡ከአሜሪካ እንደተመለስሽ ምን መሥራት ጀመርሽ?

ወ/ት ማራኪ፡– እንደመጣሁ ወደ ትግራይ ነበር የሄድኩት፡፡ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ባለበት ሽሬ ፆታዊ ጥቃት ላይ እሠራ ነበር፡፡ ፆታዊ ጥቃት ላይ በምሠራበት ጊዜ ብዙ ሴቶች ይመጣሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሴቶች ውጭ ለመውጣት ሲሉ በመጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ኤርትራውያን ጋር ይጋባሉ፡፡ ይህንን የምታደርገው እንግዲህ የፒያሳ ወይም የመርካቶ ልጅ ትሆናለች፡፡ ትግርኛ መናገር ከቻለች ደግሞ አለቀ፡፡ በዚህ መልኩ የተጣመሩ ብዙ ልጆች አውቃለሁ፡፡ እነዚህ መግባባት ሲያቅታቸው ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ተደብድበው ዓይናቸው አብጦ፣ ፊታቸው በልዞ እኔ ጋር ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ወደ እኔ ሲመጡ ምንም ነገር ማድረግ አልችልም ነበር፡፡ ያሉት ማንኛውም ድጋፎች የተዘጋጁት ለኤርትራ ስደተኞች እንጂ ለኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ አገሬን ላገለግል ብዬ እዚህ መጥቼ ጥቃት ደርሶባት ለምትመጣ ኢትዮጵያዊት ምንም ማድረግ አለመቻሌ ያሳስበኝ ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ኮንዶማይዝ በተባለ ፕሮጀክት አማካይነት ሴተኛ አዳሪዎች ላይ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ይህም ከተለያዩ ችግርና ስቃይ ውስጥ ካሉ ሴቶች ጋር እንድተዋወቅ ረዳኝ፡፡

ሪፖርተር፡ያሉትን ፈተናዎች ተቋቁመው መውጣት የሚችሉ ሴቶች አጋጥመውሻል?

ወ/ት ማራኪ፡– አንድ የማውቃት ስትሪፐር (የፖል ላይ ደናሽ) አለች፡፡ ይህች ልጅ አራት ወንድሞች አሏት፡፡ ሁለቱን ጎንደር፣ ሁለቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምራ ለምርቃታቸው ሄጃለሁ፡፡ ሌሎችም ብዙ ጠንካራ ሴቶች አሉ፡፡ ብርታታቸው ከየት እንደሚመጣ ይገርማል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በጣም ብዙ እናቶች አሉ በልጅነታቸው ‹‹ዲቃላ›› የወለዱ፡፡ እናቴም ገና በ15 ዓመቷ ነበር የወለደችው፡፡ ሰፈር ወስጥ ሌሎችም እንደሷ በልጅነታቸው የወለዱ አሉ፡፡ እነዚህ እናቶች ፈልገው ነው ወይስ በግዳቸው ነው የወለዱት የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ስለመደፈር የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ጀግኒቶች ወጥተዋል፡፡ ተጎድተው የቀሩም አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክ ካላቸው ሴቶች ጋር አሥር ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ መጨረሻ ላይ የጀግኒት ሐሳብ መጣልኝ፡፡ ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ‹‹ጀግኒት የእኔ ጎበዝ፣ በርቺ›› እያሉ ማሳደግ ለኋላ ማንነታቸው የሚኖረውን አስተዋጽኦም አጤንኩ፡፡

ሪፖርተር፡በኢትዮጵያ ከሚነሱ ልዩ ልዩ ችግሮች መካከል የልጅ አስተዳደግ ችግር አንዱ ነው፡፡ የልጆችን ፍላጎትና ልዩ ዝንባሌ ወይም ችሎታ ለይቶ ከማበልፀግ ይልቅ በቁጣና ተግሳፅ ወደ አንድ መስመር እንዲገቡ የማስገደድ ካልሆነም ቀጥቅጦ እስከማሳመን የማይሞከር ነገር የለም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙሽና የታዘብሻቸው ነገሮች ካሉ ብታካፍይን?

ወ/ት ማራኪ፡– መቀጥቀጥ ሌላ ነው፡፡ ዲስፕሊን አስይዞ ማሳደግም ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልጆች በዲስፕሊን አይደለም የሚያድጉት፡፡ ልጅን ቆንጥጦ ደግመህ እንዲ አታድርግ ማለት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ አገር ግን ቀጥቅጦ ተነስቶ በርበሬ ነው የሚታጠነው፡፡ ይኼ አረመኔነት ነው፡፡ አቀጣጥ እራሱ አናውቅም፡፡

ሪፖርተር፡ትልቁ ችግር ያለው አባት ወይስ እናት ጋር ነው?

ወ/ት ማራኪ፡– በሰፈሬ ያሉ ዱርዬ የሚባሉትን ልጆች ከጥግ እስከ ጥግ ነው የማውቃቸው፡፡ ዱርዬ ወይም አስቸጋሪ ከሚባሉት አሥሩ መካከል ሁለቱን ይዘሽ ብትጠይቂ እንደዛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው አባታቸው እንደሆነ ይነግሩሻል፡፡ ዓይን ሳይኖረው እየቀጠቀጠ አሳድጓቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ዱርዬ እናቱን ይወዳል፡፡ አባት እንዳይመታው ታሸሸዋለች፣ ጉያዋ ውስጥ ትደብቀዋለች፡፡ በትንሹም በትልቁም እየቀጠቀጡ እየመቱ ማሳደግ ልጅን ያደነዝዛል፡፡ በእኛ አገር አሁንም ልጀ ይመታል፡፡ ወላጅ ባይመታሽ ታላቆችሽ ይቀጠቅጡሻል፡፡ መመታት በሌለብን ነገር ተመትተን ነው ያደግነው፡፡ ጥቃትና አስተዳደግ የሀብታምና የደሃ የለውም፡፡ የደሃ ልጅ ሆኖ በፍቅር አድጎ ለቤተሰቦቹ የሚተርፍ ለጋስ ይሆናል፡፡ ተቀጥቅጦ ያደገ የሀብታም ልጀ ቤተሰቦቹን ዞር ብሎ ማየት የማይፈልግ አረመኔ ይሆናል፡፡ ይኼ የኑሮ ደረጃም ሆነ ገቢ የማይለየው የአስተዳደግ ችግር ነው፡፡ ያለው የአስተዳዳግ ችግር ደግሞ በሴትና በወንድ ልጆች ይለያያል፡፡ እሷ ቃጤ እየተጫወተች እሱ ኳስ እየጠለዘ ሳለ ኑ ግቡ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሰው የሚላችሁን አትሰሙም ብለው አንድ ላይ ከተቆጧቸው በኋላ የእሷ ግን ቀጠል ይላል፡፡ ምንድነው እንደዚህ እግርሽን የምትከፍቺው? ሴት አይደለሽ እንዴ? ዲቃላ እንዳታመጩብኝ የሚሉ ቁጣና ስድቦች ይቀጥላ፡፡ እነዚህ የማናውቃቸው Emotional Abuse (ስሜትን የሚጎዱ) ንግግሮች ናቸው፡፡ እንዲህ ተብለን ስላደግን ይኼንኑ በልጆቻችን እንደግማለን፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሴቶች አትችሉም፣ አታደርጉም የሚባል ነገር አለ፡፡ ፀጉራችንን ብንቆረጥ ሴት አትቆረጥም፣ አካሄዷን አይተው ሴት ልጅ እንደዚህ አትሄድም ወንዲላ ሆንሽ፣ ከማን የበለጥሽ መሰለሽ? ሴት ልጅ ጮክ ብላ አታወራም እንባላለን፡፡ ብዙ ነገሮች ለእኛ የተገደቡ ናቸው፡፡ ሴት እንዲህ ናት እንደዚያ ናት እያሉ ጠባብ ሳጥን ውስጥ ነው የሚከቱን፡፡ ከዚያ ሳጥን ውስጥ ፈንቅሎ መውጣት ነው ዋናው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ነው እንደዚያ ነው ሲሉን የነበሩ ሰዎች በደቂቃዎች ውስጥ ረስተውን ወደየጉዳያቸው ገብተዋል፡፡ ሳጥኑ ውስጥ እንድንገባ ቢያደርጉንም የምንቆየው በፈቃዳችን ነው፡፡ ራሳችንን የምንገድበው በአብዛኛው ራሳችን ነን፡፡ ለዚህም በመጀመርያ ራሴን ነፃ ማውጣትና ቀጥሎ ሌሎቹን ነፃ ለማውጣት ወሰንኩ፡፡ የማይባለውን እያልኩ፣ አደባባይ ላይ የማይወጡ ነገሮችን አደባባይ እያወጣሁ ማውራት ጀመርኩ፡፡

ሪፖርተር፡የጀግኒት ንቅናቄ አሁን ያገኘውን ተቀባይነት ይኖረዋል ብለሽ ገምተሽ ነበር?

ወ/ት ማራኪ፡– ሰው እንዲህ እንደሚወደው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም ከራሴ ቁስል ተነስቼ ነው ሐሳቡን ያመጣሁት፡፡ እኔ እንዴት ጎበዝኩኝ አልሜ አቅጄ እንዳሳካ ያደረገኝ ምንድነው ብዬ አስቤ የነበሩብኝን እንቅፋቶችም አስታውሼ ነው፡፡ የጀግኒት ንቅናቄ የተጀመረው አንዲት ሴት ጎበዝ እንድትሆን እንቅፋቶቿን ለማስወገድ ነው፡፡ ጀግኒት አልማ አቅዳ ታሳካለች ስንል ግን ለማለም ጊዜ ያስፈልጋታል፡፡ መማር አለባት፡፡ መጀመርያ ሴቶችን የሚያበረታቱ ተምሳሌታዊ ሴቶችን እንዲሁም እንደ ድሮ ትምህርታዊ ነገሮች በደብተሮች ጀርባ እንዲታተም አሰብን፡፡ ይኼንን ካሰብን በኋላ ደብተር ለሴቶች ቅንጦት እንደሆነ ተረዳን፡፡ በወርአበባ ምክንያት ከትምህርት ቤት በወር ከአሥር ቀናት በላይ እየቀረች ስለምን ደብተር ነው የምናወራው? አለን፡፡

ሪፖርተር፡የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ሞዴስ አቅርቦት በምን ያህል መጠን ችግር አለበት? ጥናቶችስ ምን ይላሉ?

ወ/ት ማራኪ፡– አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ሞዴስ ከ67 እስከ 123 በመቶ ይቀረጣል፡፡ በወር 35 ሚሊዮን ሴቶች የወር አበባ ያያሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 72 በመቶ የሚሆኑት ሞዴስ አያገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ልጆች ከትምህርት ይቀራሉ፡፡ በወር ከአሥር ቀናት በላይ ይቀራሉ፡፡ ትምህርት ቤት የሚታጠቡበት ውኃ የለም፣ መፀዳጃ ቤት የለም፡፡ በዙሪያቸው የሚገኙ ሱቆችም ሞዴስ አይሸጡም፡፡ ስለዚህ የወር አበባ ሲታያቸው ወይ ወንዝ ዳር ወይ ቤታቸው ነው የሚውሉት፡፡ ስለዚህም በዓመት ከትምህርታቸው 100 ቀናት ያህል ስለሚቀሩ ይደግማሉ፡፡ ሲደግሙ ደግሞ ወላጅ ከዚህ በኋላ ምን ዋጋ አለው ብለው ያለ ዕድሜዋ ለጠየቃት ይድሯታል፡፡ ያለ ዕድሜ አናገባም የሚሉ ከሆነ ደግሞ ዓረብ አገር ይሄዳሉ፡፡ ይህ ሁሉ በወር አበባ ምክንያት ነወ፡፡ ከዚህ ሁሉ ሊታደጋቸው የሚችለው ሞዴስ እንደ ቅንጦት ዕቃ ይቀረጣል፡፡ ሞዴስ እንደ ፋውንዴሽን፣ እንደ ሊፕስቲክ፣ እንደ ኩልና ማስካራ ይቀረጣል፡፡ ለዚህም ሴቶች ጥጥ እያጣፉ፣ አንሶላ እየቀደዱ ይጠቀማሉ፡፡ የሚፈልጉት ፈሳሹን የሚመጥ ነገር መኖሩን ስለሆነ ኩበት እንደ ሞዴስ የሚጠቀሙም አሉ፡፡ እኔና አንቺ እንደ እነዚህ ሴቶች ሞዴስ አጥተን ያደግን ብንሆን እዚህ ጋር ቁጭ ብለን አንነጋርም ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፣ ሕምም ነው፡፡ ነገር ግን እሷ ችግር እንደሆነ እንኳን ላታውቀው ትችላለች፡፡ የወር አበባ ጉዳይ የፆታ ጉዳይ ቢሆንም ይታሳብ የነበረው የዋሽ ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ ሴቶችና ሕፃናት በዚህ ላይ የሚያገባኝ የለም ብሎ ነበር የተቀመጠው፡፡ ከሚመለከታቸው ጋር አውርተን ሞዴስ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ፈቃድ ሊያገኝ ጫፍ ላይ ደርሷል፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሚገቡት ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆን የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን እንዲወስድ ጥረት ማድረግ ጀምረናል፡፡ ምክንያቱም ከደረጃ በታች የሆነ ምርት ገበያውን አጥለቅልቆ በሽታ ላይ እንድንወድቅም አልፈልግም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...