Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአገረ ብሔር ግንባታ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች በብዝኃነት ማዕቀፍ

የአገረ ብሔር ግንባታ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች በብዝኃነት ማዕቀፍ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በሙሉጌታ ይልማ (ዶ/ር)

በክፍል አንድ የነበረውን ውይይት ስቋጭ በኢትዮጵያ የአገረ ብሔር ግንባታን ዕውን ለማድረግ ከዴሞክራሲ ግንባታና ከኢኮኖሚ ብልፅግናው ባሻገር በተጨማሪ ብሔር ዘለል የሆነ የሕዝቦችን ትስስር የማጠናከሩ ጉዳይ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በሚል ማጠቃለያ ነበር፡፡ በቀጣዩም የሚዝናናው ይኼው ሐሳብ ይሆናል። የነበረው ትስስር ድሮም የላላ ነበር ቢባልም በዘመነ ኢሕአዴግ ግን የባሰ እንዲላላ ተደርጓል፡፡ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ልሂቃንም ከዜግነት ፖለቲካ በላይ አጉልተው የሚያራምዱት የብሔርተኝነት ፖለቲካን በመሆኑ ሁኔታውን የተባባሰ እንዲሆን አድርጎታል። ብሔር ዘለል የሆነው ትስስር አስፈላጊነት ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር ያለውን ግንኙነት፣ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች የተገኙትን ተሞክሮች በቀጣይ የምንዳስሳቸው ይሆናል። በተለይ ስዊስ ብሔር ተሻጋሪ የሆነ የሕዝቦችን ትስስር ያዳበረች፣ በብዝኃነት ማቀፍ ውስጥም የአገረ ብሔር ግንባታ ሽግግርን ያሳካች በመሆኗ፣ ለሌሎችም አገሮች እንደ ተምሳሌት (Role Model) ሆና የምትታይ አገር ሆናለች፡፡ በመሆኑም ተሞክሮዋን ሰፋ አድርገን የምንዳስሰው ይሆናል።       

የተለያዩ ብሔሮች በሚኖሩባቸው አንዳንድ አገሮች አንድነታቸውን ጠብቀው ሲኖሩ ተመሳሳይ የብሔር ስብጥር ያላቸው፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ የመበታተን/የመገነጣጠል አደጋ ሲያጋጥማቸው ይታያል፡፡ ለምን የብሔራዊ አንድነት ግንባታ በአንዳንድ አገሮች ላይ ሲሳካ በሌሎች አገሮች ላይ አይሳካም? የመገነጣጠሉ አደጋ ባላደጉና የዴሞክራሲ ሥርዓታቸውንም ባላዳበሩ አገሮች ብቻ ሳይሆን ባደጉና የዴሞክራሲ ሥርዓታቸውን አዳብረዋል በሚባሉ አገሮችም ሳይቀር የሚታይ ችግር ሆኗል፡፡ በስፔይን፣ በቤልጂግና በእንግሊዝ እንደሚታየው።በአንፃሩ ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓታቸው ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው በዝቅተኛ ደረጃ ይገኛል የሚባሉት በደቡብ ቻይና የካንቶን ቋንቋ ተናጋሪዎችና በህንድ ውስጥም በሚኖሩ የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች መሀል የመገንጠሉ ጥያቄ አይታይም፡፡ ስዊስና ቡኪና ፋሶም የተለያዩ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው አገሮች እንደ መሆናቸው ሁሉ ብሔራዊ አንድነታቸው ምንም ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም በማለት የሶሲዮሎጂና የፖለቲካ ፍልስፍና ተመራማሪ የሆነው ምሁር ዊመር (Wimmer) ይናገራል፡፡ ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበው የመከራከሪያ ነጥብም በሕዝቦች መሀል የተፈጠረ ትስስር መኖሩን ነው (Nation Building: Why Some Countries Come Together While Others Fall Apart Andreas Wimmer Forthcoming in Survival. The International Institute for Strategic Studies Quarterly 60, 2018).

ከዚህ መረዳት የሚቻለው የዴሞክራሲ መዳበርና የኢኮኖሚ ዕድገት ለብቻቸው ለብሔራዊ አንድነት ግንባታ መሳካት ዋስትና እንደማይሆኑ ነው። ብሔር/ብሔረሰቦች (Ethnicgroups) በሚኖሩባቸው አገሮች ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓቱም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ብሔር ዘለል በሆነና ሁሉን አሳታፊ/አቃፊ ሆኖ በሚፈጠር መንግሥታዊ አስተዳደር መታጀብ እንዳለበት ነው፡፡ ሰዎች የብሔሮቻቸው አባላት በላይኛው የሥርዓቱ አስተዳደር ላይ ተሳታፊ ሆነው በሚገኙባቸው አገሮች የመገለል ብሎም የመገንጠሉ ስሜታቸው የመነመነ እንደሚሆን ነው። የተለያዩ ብሔሮች በሚኖሩባት ስዊዘርላንድ የአገሪቱ አንድነት ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ እንደ አንድ አገር በፌዴራል አስተዳደር መተዳደር ከጀመረችበት ከ1848 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለመቀጠል ችላለች፡፡ ለዚህ ያበቃትም ከዳበረው የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገቷ በተጨማሪም ሁሉን አቃፊ የሆነ መንግሥታዊ አስተዳደር በመዘርጋቷ ነው።  

ዴሞክራሲና አሳታፊነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የቡድኑን መብት በተደራጀ መልክ የማስከበር ችሎታ ይኖረዋል። የግል መብትና የቡድን መብት የተለያየ ነው የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም፣ የቡድኑም መብት በግለሰብ መብት ሥር ይከበራል፡፡ ሎጂኩም በዴሞክራሲ ሥርዓት ብሔር/ብሔረሰቦች የሚጨቆኑበት ሁኔታ በጣም ዝቅተኛ ስለሚሆን ነው፡፡ አናሳ የሆኑ ብሔረሰቦች እንኳን በዴሞክራሲ ሥርዓት ሥር የመደራጀት ነፃነት ስላላቸው ማንም በቀላሉ ሊጫናቸው አይችልም፡፡ በአስተዳደሩም ውስጥ የመታቀፋቸው ዕድል ሰፊ ነው። ይህ ማለት ግን የዴሞክራሲ ሥርዓት መኖሩ ብቻውን በራሱ አሳታፊ የሆነ ሥርዓት ለመፍጠር ዋስትና ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዴም ዴሞክራሲ የቂም በቀል መወጣጫም ሲሆን ይታያል፡፡ ለምሳሌ ኢራቅ ከአምባገነን ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ እየጣረች ነው ቢባልም ሥርዓቱ አናሳ የሆኑትን የዓረብ ሱኒዎችን (15 እስከ 20 በመቶ) በማግለሉ  ለብዙ ጊዜ ኢራቅን በትርምስ ላይ የምትገኝ አገር አድርጓታል። በሥልጣን ላይ ያለው የፖላንድ ገዥ ፓርቲም በፓርላማ ያገኘውን አብላጫ ድምፅ በመጠቀም የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ (December 2017) ሙስናን እዋጋለሁ በሚል ሽፋን አርባ ከመቶ (40 በመቶ) የሚሆኑትን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች ጡረታ የመውጪያቸው ዘመን ከመድረሱ በፊት (ከ70 ወደ 65 ዓመት ዝቅ በማድረግ) ሊያሰናብታቸው ሞክሮ ነበር፡፡ የተፈለገውም ተቃዋሚ የሚባሉትን ዳኞች አግልሎ ለፓርቲው ታማኝ በሆኑ አገልጋዮች ለመተካት ነበር፡፡ ነገር ግን የአውሮፓ ማኅበር (EU) ባሳደረው ተፅዕኖ ሙከራውን ለማስቆም ተችሏል፡፡ ሙከራው እስከሚቆም ድረስ ግን ለአንድ ዓመት ያህል ፖላንድ ከፍተኛ ተቃውሞ በውስጧ አስተናግዳለች። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደሯና በኢኮኖሚ ብልፅግናዋ የምትታወቀዋ አሜሪካንም 70 ዓመት ባርያነትን ሳታስወግድ እስከ 1865 ዓ.ም. ድረስ ቆይታለች፡፡ ከዚያም በኋላ ለሌላ መቶ ዓመት ጥቁሮችን ትርጉም ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሳታሳትፍ እስከ 1965 ዓ.ም. (The Voting Right Sact of 1965) ድረስ ኖራለች።

ኢትዮጵያም ወደ ዴሞክራሲ በመሸጋገር ላይ ያለች አገር በመሆኗ ብዙ ችግር ይጠብቃታል፡፡ በፖለቲካ ታሪኳም የዴሞክራሲ አየር ነፍሶባት የማታውቅ አገር በመሆኗ ችግሩ እጥፍ ድርብ እንደሚሆንባትም መገመት አያዳግትም። ለምሳሌ አንደኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ሌብነትን ወደ ሕግ ፊት ለማቅረብ በምታደርገው ትግል ውስጥ እያጋጠማት ያለው ችግር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ናቸው። ግጭቶች በማንኛውም አገር የሥርዓት ለውጥ በሚደረግበት ጊዜ በሽግግር ወቅት የሚፈጠሩ ክስተቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በፈረንሣይ አብዮቱን ተከትሎ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ወደ ዘጠና ዓመት ያህል (1789-1875) ዘልቋል፡፡ ሊቢያም ከጋዳፊው ድቀት በኋላ እስካሁን ድረስ በትናንሽ ‹‹ንጉሦች›› በመታመስ ላይ ትገኛለች።

ወደ ፊትም በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ሽግግሩ ‹‹አስተማማኝ›› ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የተለያዩ ግጭቶችንና ችግሮችን መጋፈጡ አይቀሬ ነው፡፡ ግጭቶቹና ችግሮቹም በዚህ ዓመትና ወር ይቆማሉ ብሎ ለመገመት ያዳግታል፡፡ በተለይ በታችኛው የሥልጣን መዋቅር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣኖች አብዛኞቹ ሽግግሩን የማይደግፉ መሆናቸውም ችግሮቹን የባሰ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ በሽግግር ጊዜ የሚያጋጥሙን ችግሮች ለመቅረፍና የሽግግሩንም ጊዜ ለማሳጠር ግን የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ቅድሚያ ማግኘት ይኖርበታል ብሎ መናገር ይቻላል። ለምሳሌ ገለልተኛ ሚዲያዎች፣ ነፃ ፍርድ ቤቶች፣ ነፃ የሲቪል ማኅበሮች፣ የፖሊቲካ ፓርቲዎችን ለማጠናከር የተጀመረው ሥራ በይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የጦር ኃይሉን፣ ደኅንነቱንና የምርጫ ቦርዱን ከፖለቲካና ከወገናዊነት ነፃ አድርጎ የማደራጀቱም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።ብሔር ዘለል እየሆነና ሁሉን አቃፊ እየሆነ ለመሄድ የሚሞክረው የጠቅላይ ሚኒስትር የዓብይ ካቢኔም በአገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው ስለሚችል መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የፆታ ተዋጽኦውም እንደዚሁ፡፡ ዜጎች በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ታቅፌአለሁ አገሪቱ የእኔም ናት የሚል ስሜት በመጠኑም ቢሆን እንዲያድርባቸው ያደርጋል። በእርግጥ ሁሉን አቃፊ የሆነ ሥርዓት የመገንባቱ ጉዳይ በቅድሚያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን (Civil Society Organizations) መገንባትና ማጠናከርን፣ የፖለቲካ ማኅደሩን ማስፋትንና እንዲሁም ግንባታው ሥርዓታዊ (Systemic) በሆነ መንገድ ሊተገብር የሚችል አስተዳደርን ይጠይቃል። ይኼ ሁሉ ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ጉዞው ለኢትዮጵያ አገረ ብሔር ግንባታ አስፈላጊ በመሆኑ ዕርምጃውን መጀመር ግድ ይሏል። በ123 አገሮች በተካሄደ አንድ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው ዜጎች የብሔራቸው/ብሔረሰባቸው አባል የሆኑ ሰዎች በላይኛው የሥልጣን ዕርከን በሚሳተፉበት አገሮች ላይ በዜግነታቸው ኩራት እንደሚሰማቸው፣ በአንፃሩ ደግሞ የብሔራቸው/ብሔረሰባቸው አባል በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ባልታቀፉበት አገሮች የዜግነት ኩራት እንዳማይሰማቸው ነው (Wimmer, A. (2017). “Power and Pride National Identity and Ethno Political Inequality Around the World.” World Politics 69(4): 1-35)

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ካቢኔ ብሔር ዘለልና ሁሉን አቀፍ እየሆነ መምጣቱ የሚደገፍ ነው ቢባልም በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአካባቢያቸው ባሉ ሰዎች አነሳሽነት የሚተገበር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፣ አተገባበሩ ሥርዓታዊ (Systemic) ሆኖ ወደ ታች አልወረደም፡፡ ሥርዓታዊ እስካልሆነ ድረስ ደግሞ ፈቃደኛ ያልሆኑ መሪዎች ሥልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ሁኔታው በቀላሉ ሊለወጥ ይችላል፡፡ ብሔር ዘለልና ሁሉን አቃፊ የሆነው አስተዳደር ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በአገራዊ አንድነት ግንባታም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል።

አስተዳደሩ ዘላቂነትና ለአገራዊ አንድነት ግንባታም አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በበጎ ፈቃድ የተደራጁ ድርጅቶች በነፃ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት መንገድም መመቻቸትም ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ የሚያደራጁ ፓርቲዎችና ድርጅቶች መሠረታቸው ዘር ተሻጋሪ በመሆኑ ለማንኛውም የሥልጣን ዕርከን ሁሉን አሳታፊ የሚሆን መሠረት ይጥላሉ። ዘርን ብቻ መሠረት አድርጎ የሚደራጅ ድርጀት ግን በተቃራኒው ከራሱ ብሔር ውጪ ከሌሎች ጋር ድርጅታዊ ትስስር ኖሮት የማይነቃነቅ ስለሚሆን ዘር ተሻጋሪና ሁሉን አቃፊ ሊሆን አይችልም፡፡ አገራዊ አንድነት ግንባታ ላይም የሚኖረው አስተዋጽኦ አሉታዊ ነው የሚሆነው።

ዘር ተሻጋሪ የሆኑትስ ሥር አንዱ ገጽታው በተዋቀረ መንገድ በመንግሥትና በዜጎች መሀል የሚኖረውን ትስስር/ትብብር ታሳቢ አድርጎ የሚነሳ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ጠንካራ ፓርቲዎች በሚኖሩበት አገሮች እንደሚታየው በመንግሥታትና በዜጎች መሀል የሚኖረውን የተዋቀረ ግንኙነትን መመልከት ይቻላል። በአሜሪካ ዜጎች የዴሞክራትን ወይም የሪፐብሊክን ፓርቲ ከመምረጣቸው በፊት የትኛው ፓርቲ ነው ከእኔ ፍላጎት ጋር የሚስማማ ዓላማ/ፕሮግራም ያለው ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሻሉ፡፡ ፓርቲዎችም የተሻለ ነው የሚሉትን ሐሳብ ይዘው ከመራጭ ፊት ይቀርባሉ፡፡ ለመራጮች የሚስማማ ሐሳብ ይዞ የቀረበው ፓርቲ አሸናፊ ከሆነ መንግሥታዊ አስተዳደር ይመሠርታል፡፡ ሁሉም መራጮች ማለት ጥቁሩ፣ ነጩ፣ ላቲኑ፣ አይሪሹ፣ ፖሊሹ፣ ኢትዮጵያዊው፣ ሶማሌው፣ ወዘተ በጋራ የመረጡት ፓርቲ መንግሥታዊ አስተዳደር ይመሠርታል ማለት ነው። አስተዳደሩም ዘርን፣  የቆዳ ቀለምን፣ ፆታን፣ ወዘተ ሳይሆን ሐሳብን ብቻ (ምክንያታዊነትን) መሠረት አድርጎ የተመሠረተ በመሆኑ ሕዝቦችን በጋራ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡ ምርጫውን ሲያሸንፉ አብረው ይደሰታሉ፣ ሲሸነፉም አብረው ያዝናሉ። በአሸናፊም በተሸናፊም ወገን የሚገኘው የሕዝቦች ስብጥር ተመሳሳይ በመሆኑ በማንነቴ ተበድያለሁ ብሎ እሮሮ የሚያሰማ አይኖርም፡፡ ለምሳሌ አይሪሽ በመሆንህ ነው የዴሞክራት ፓርቲን የመረጥከው ብሎ ኢትዮጵያዊው በአይሪሹ ላይ ጣት አይቀስርበትም፡፡ የዴሞክራቲክ ፓርቲን የመረጡ ኢትዮጵያውያንም ስለሚኖሩ።

ሁለተኛው ገጽታ ደግሞ በሕዝቦች መሀል ሊፈጠር የሚችለውን ትስስር የሚያመላክት ነው። የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የአካባቢን ጥያቄ ይዘው ቢነሱም አንዳንድ ጊዜም ደግሞ አገር አቀፍ ሊሆን የሚችል ጥያቄ ይዘው ሊነሱ ይችላሉ። ሙያን መሠረት ባደረገ ፍላጎት የተመሠረቱን (አስተማሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ ወዘተ) የጋራ ጥቅሞችን በሚነኩ (የደን፣ የአየር መከላከልን፣ ወዘተ)፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲ መብት መከበር፣ ለፃታ እኩልነት፣ ጎጂ ባህልን ለማጥፋት፣ ወዘተ ላይ ተመሥርተው በሚነቃነቁበት ጊዜ ክልልና ዘር ተሻጋሪ የሆነ የጎንዮሽ ትስስርን ሊፈጥሩ ይችላሉ ብሎም አገር አቀፍ የሆነ ድርጅት የመመሥረት ችሎታም ይኖራቸዋል። የዚህ ዓይነት አደረጃጀቶችም የሚያራምዷቸው ጥያቄዎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ይዘት ስላላቸው በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመንግሥት ላይ ጫና መፍጠራቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለሆነም ድርጅቶቹ በመንግሥትና በሕዝብ መሀል ድልድይ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ ጥያቄዎቹ በአግባቡ ከተስተናገዱ ደግሞ ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በሥልጣን ዙሪያ ተወክያለሁ ወይም ታቅፌአለሁ የሚል ስሜትም ያሳድርባቸዋል፡፡ ይኼ ስሜታቸው ደግሞ የሚደግፉት ፓርቲ ሥልጣን ላይ በማይኖርበትም ጊዜ ቋሚ ሆኖ የሚኖር ይሆናል፡፡በአገሪቱ ምሁራንም ሆኑ በዜጎች መሀል መንግሥት የጋራችን ነው የሚል አመለካከት ይፈጥራል፣ ታማኝነታቸውም ከሁሉ በላይ ለአገሪቱ ይሆናል ማለት ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ እንደሆነ ነው የሚነገረው ያሉትም ዘርና ክልል ተሻጋሪ የሆነ ትብብር ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም፣ የአማራ ምሁራን ማኅበር፣ የኦሮሞ ምሁራን ማኅበር፣ የትግሬ ምሁራን ማኅበር፣ ወዘተ በሚል በክልልና በብሔር ተወስነው የተደራጁ መሆናቸውን ነው። እነዚህ ድርጅቶች ለክልላቸውና ለብሔራቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያደርጉት ንቅናቄ ባለመኖሩ አገር አቀፋዊ ድርጅቶች ሆነው ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ዘር ተሻጋሪ የሆነ የሕዝቦችንም ትስስር አላጠናከሩም፡፡ በመሆኑም በአገረ ብሔር ግንባታ ላይ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ይሆናል።

ተመራማሪው ምሁር ዊመር (Wimmer) የአገረ ብሔር ግንባታ ተሳክቶላቸዋል የሚላቸው አገሮችን ሲዘረዝር ዘር ተሻጋሪ የሆኑና ጠንካራ የፖለቲካ ትስስር/ትብብር ያለው አስተዳደር የገነቡትን ነው፡፡ ለመሳካቱ ደግሞ እንደ ዋና ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበውም ረዥም ጊዜ በሚወስድ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ መገንባት ያለባቸውን ሦስት ሁኔታዎች አሟልቶ መገኘት ነው፡፡ አንደኛ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚነቃነቁ ጠንካራ የማኅበረሰብ ድርጅቶች መኖር፣ ሁለተኛ የመንግሥት ግልጋሎትን ለሕዝብ የማቅረብ አቅም ግንባታና ሦስተኛ የጋራ የሆነ የመግባቢያ ቋንቋ ተሟልተው መገኘታቸውን ነው። የሦስቱም አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ በመቀጠል የሚደረገው ውይይት ዘር ተሻጋሪ የሆነ የሕዝቦች ትስስር በአገር ግንባታ ላይ የሚያስከትለውን አዎንታዊ ተፅዕኖ በተጨባጭ ማየት ይሆናል፡፡ ስለሆነም የስዊስን ተሞክሮ ወደ መዳሰሱ እንሻገራለን።

ስዊዘርላንድ

ዛሬ ለሚታየው የስዊስ ፌዴራል አስተዳደር መሠረቱ ከሰባት መቶ ዓመት በፊት  (1,301) በሦስት ካንቶኖች (ግዛቶች) መሀል በተደረሰ ስምምነት የተገነባ ኅብረት (Alliance) ነበር፡፡ ዓላማውም የንግድ መንገዶችን እየዘጉ ያስቸግሯቸው የነበሩና አምባገነን የሚሏቸው የሮማ መንግሥትና የሃቡስበርግ መሳፍንቶችን በጋራ ለመከላከል ነበር። ከጊዜ በኋላ ኅብረቱ ያስገኘውን ጥቅም የተመለከቱ ሌሎች ካንቶኖች (ግዛቶች) ኅብረቱን መቀላቀል ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ኅብረቱ ስዊስን ማዕከል ያደረገ አልነበረም፡፡ በየካንቶኖቹ የሚገኙ ሕዝቦች ራሳቸውን የሚመለከቱት እንደ የካንቶናቸው አባል ብቻ እንጂ እንደ ስዊሳዊ አልነበረም፡፡ ካንቶን ተሻጋሪ የሆነ የሕዝቦች ትስስር ነበር ለማለትም አይቻልም። በእንደ እነዚህ ዓይነት የላላ ኮንፌዴሬሽን ሥር ሆና ስዊስ እስከ ፈረንሣይ ወረራ ድረስ ቆየች፡፡ ፈረንሣዮቹም ስዊስን ለማስተዳደር የሪፐብሊክ መንግሥት መሠረቱ፣ የወረራው ዘመንም አጭር ነበር። ወረራው በአገረ  ብሔር ግንባታ ላይ የስዊስን ልሂቃን/ኤሊት ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ይዘው እንዲነሱ መንገድ ከፍቶላቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ በካንቶኖች መሀል የነበረውን የላላ ኅብረት ወደ አንድ የብሔራዊ ማንነት (Swiss Nationness) ለመለወጥ ቁርጠኛ ሆነው እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል።

ከ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከ  19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ብሔር ዘለል የሆኑ የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች በመላው ስዊዘርላንድ በስፋት ይገኙ ነበር፡፡የተኩስ ክበቦች (Shooting Clubs)፣ የንባብ ክበቦች (Reading Cicles)የሙዚቀኞች ማኅበረሰብ (Choral Societies)፣ የምርምር ቡድኖች፣ ከብዙዎቹ መሀል የሚጠቀሱ ናቸው። ከጦርነቱ በአሸናፊነት የወጡትና በአገሪቱም ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ችሎታ የነበራቸው የአገሪቱ ኢሊቶቹ (Elite) ቅድሚያ የሰጡት በአገሪቱ ላይ ተስፋፍተው የሚገኙትን አገር አቀፍና ብሔር ዘለል የሆኑትን የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶችን በማቀፍ ተከታዮችና መሪዎችን ከመካከላቸው መልምሎ የመንግሥት ሥልጣንን ማዋቀር ነበር። በመላው ስዊዘርላንድ በዚህ ዓይነት መንገድ የተፈጠረው የሥልጣን አወቃቀርም አገር አቀፍ ባህርይ ሊያገኝ ቻለ፡፡የእያንዳንዱ ቋንቋም ተናጋሪ በከፍተኛው የፌዴራል አስተዳደር ውስጥ እንደ ብዛቱ መጠን ውክልና እንዲኖረው ተደረገ፣ ሁሉም ቋንቋዎች /አራቱም/ ኦፊሺያል ሆኑ፣ እስከ ዛሬም የቋንቋ ጥያቄ ችግር ሳይሆን ሊቀጥል ቻለ።

በተጨማሪም ኤሊቱ የጥንት ታሪክን ወደ ፊት በማምጣትና የተለያዩ ተምሳሌቶችን (Symbols) በመጠቀም በሕዝቡ ውስጥ የስዊሳዊነት/የዜግነት ስሜት እንዲዳብር ብዙ አነቃቂና ስሜትን የሚኮረኩሩ ሥራዎች ሠርቷል። የተለያዩ የሃይማኖት መዝሙሮችን በመጻፍ፣ ስዊስ የአልፕ አገር በመሆኗ ሕዝቡ ኩራት እንዲሰማው በማድረግ ከሰባት መቶ ዓመት በፊት ስለነበረው የካንቶኖች ኅብረት አመሠራረት ታሪክ በኅብረተሰቡ ውስጥ በሰፊው እንዲነገር በማድረግ፣ በኅብረት በውጪ ኃይሎች ላይ በጦርነት የተቀዳጇቸውን ድሎች ወደ ፊት በማምጣት፣ የጦር ጀግኖቻቸውንም እንዲወደሱ በማድረግ የስዊስን ብሔራዊ አንድነት ለማጠንከር ተጠቅሞበታል ስዊሳዊነት እንዲጠናከር አድርጓል።

ልሂቃኑ ኮንፌደሬሽኑን የላላውን ኅብረት ወደ ተሻለ ኅብረት እንዲሻገር አድርገው በካንቶኖቹ መሀል ያለው ትስስር እንዲጠነክር ካደረጉ በኋላ በሁሉም ካንቶኖች መሀል ተቀባይነት ያለው የስዊስ ማንነትን ለመገንባት ችለዋል። ግንባታው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ሒደቱን የሚቃወም የካቶሊኮች ጥምረት ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የእርስ በርስ ጦርነት (Sonder Bund War) ተከስቷል። ተቃዋሚዎቹ ተሸንፈው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ አዲስ የፌዴራል ሕገ መንግሥት ተረቀቀ፡፡ የስዊስ የፌዴራል አስተዳደርም ተመሠረተ። ካንቶኖችም ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ረገድ ከጦርነቱ በፊት የነበራቸውን አስተዳደር ይዘው እንዲቀጥሉ፣ ባህላቸው እንዲከበር፣ በቋንቋቸውም ተገልጋይ እንዲሆኑ ተደረገ። ተቃዋሚዎች የነበሩትም ካንቶኖች እንደፈሩት ሳይሆን መብታቸውና ጥቅማቸው እንደተጠበቀ ሲረዱ አዲስ የተዘረጋውን የስዊስ ፌዴራል ሥርዓትን መደገፍ ጀመሩ።

የስዊስ አገረ ብሔር ግንባታ ስኬታማነት ሲወሳ የቤልጂግ አለመሳካት አብሮ ይነገራል፡፡ ሁለቱም አገሮች ተመጣጣኝ የቆዳ ስፋት፣ ተመሳሳይ የብሔር ስብጥር፣ ተመጣጣኝ የታሪክ ዕድሜና፣ ተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያላቸው ናቸው። የአገረ  ብሔር ግንባታን በተመለከተ ግን ልዩነታቸው የሰፋ ነው፡፡ የስዊስ የተሳካ ሲባል የቤልጂግ ‹‹የከሽፈ›› የሚባል ነው፡፡ ለዚህ ልዩነት እንደ ዋና ምክንያት ሆኖ የሚቀርበውም በስዊስ የተዘረጋው ብሔር ዘለል የሆነው የሕዝቦች ትስስር ቤልጂግ ላይ ባለመዘርጋቱ ነው።

ቤልጂግ በመጀመርያ ናፖሊዮን፣ በኋላም ናፖሊዮንን በተካው በደች ንጉሣዊ አገዛዝ ሥር ወድቃ በነበረችበት ጊዜ ስዊዘርላንድ የነበሯትን ዓይነት የሲቪል ሶሳይቲ ማኅበራት እንዳይኖሯት ተደርጓል፡፡ ነበሩ የሚባሉትም አነስተኛ ማኅበራዊ ድርጅቶች በሀብትና በዕውቀት የበላይነት በነበራቸው የፈረንሣይኛ ተናጋሪዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎችና በፈረንሣይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የተወሰኑ ነበሩ ፍሌሚሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎችና በፍለሚሾች መሀል ግን ፈጽሞ ያልተለመደ/ያልነበረ ነገር ነበር። በመሆኑም ቤልጂግ ከኒዘርላንድ ነፃ በወጣችበት (1831) ጊዜ የገዥዎቹ ትስስር ፈረንሣይኛ ተናጋሪ ከሆኑ ማኅበራት ጋር ብቻ የተወሰነ ሆነ፡፡ እንደ ስዊዘርላንድ አገር አቀፍና ብሔር ዘለል የሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብሎም የሕዝቦች ትስስር ባለመኖሩ ሁሉም ዓይነት ሕዝቦች የሚወከሉበት አቀፋዊ የሆነ አስተዳደር ለመመሥረት ሳይቻል ቀረ፡፡ መንግሥታዊ አስተዳደሩም በፈረንሣይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የበላይነት ተዋቀረ፡፡ ባልተጠናም ሁኔታ ፈርንሣይኛ የአስተዳደሩ፣ ወታደሩ፣ የፍርድ ቤቱ መገልገያ ቋንቋ ሆኖ እንዲታወጅ ተደረገ፣ የቋንቋም ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ እየሆነ መምጣት ጀመረ። በቤልጂግ ሳያቋርጥ እየተንከባለለ ዛሬ የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሶ የሚታየው የመከፋፈል አደጋ ምክንያቱ ይኼው ነው፡፡ የአገረ ብሔር ግንባታውንም ከጅምሩ ‹‹እንዲቀጭ›› የሆነበትም ምክንያት።

የሕዝቦች ትስስር በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በፖለቲካ ድርጅቶችም መሀል መኖር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕዝቦችና በመንግሥት መሀል ያለውን ግንኙነት በተዋቀረ መንገድ ለማስኬድ ስለሚያስችል (ከላይ እንዳየ ነው የአሜሪካን ምርጫ)፣ ሌላው ደግሞ የተለያዩ ሕዝቦችን ከማንነታቸው ባሻገር በፖለቲካ አመለካከታቸው በጋራ አብሮ እንዲቆሙ ስለሚያደርጋቸው ነው። አንዳንዶቹ የአገሮችን ልሂቃን ግን ሊከተሉ የሚፈልጉት መንገድ ከዚህ ለየት ያለ ይመስላል፡፡ በብሔረሰብ ማንነት ላይ ብቻ ያተኮረ እንጂ በፖለቲካ አመለካከት (Ideology) ላይ ቆሞ ኅብረ ብሔራዊ የሆነ የሕዝቦች ትስስር የማጠናከሩን ሥራ የተቀበሉት አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያዊነትንም በመገንባት ላይ የሚያሳዩት ፍላጎት እምብዛም ነው አብራራለሁ። ለምሳሌ ይህን ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ እያለሁ አንድ ታዋቂ አክቲቪስት ታማኝነቴ ለሦስት ነገር ነው ‹‹አንድ ለብሔሬ፣ የብሔሩን ስም ጠርቶ፣ ሁለት ለሃይማኖቴና ሦስት ለህሊናዬ ነው›› ብሎ ሲናገር ሰማሁት፡፡ ይኼን ስሰማ ያሳሰበኝ ለኢትዮጵያስ ያለው ታማኝነት ምን ያህል ነው? የሚለው ነበር፡፡ እንደ ምሳሌ አነሳሁት እንጂ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ልሂቃን ጥቂት አይደሉም፡፡ እንደ አሸን እየፈሉ በመሄድ ላይ ናቸው፡፡ የብሔርን ጥያቄ ከኢትዮጵያዊነት በላይ በማውለብለብ በአገራችን እየተገበረ ያለውን የዘር ፌዴራሊዝምን ለማስቀጠል የሚታገሉትንም ሁሉ ግምት ውስጥ ሳስገባ ማለት ነው።  

ብሔር ዘለል የሆነ የሕዝቦች ትስስርና ጠንካራ የሆኑ የኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ሊፈጠር ያልተቻለውም አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያዊነትን የማስቀደም ፍላጎት ዝቅተኛ ቦታ በመያዙ ነው እላለሁ። በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ በየክልሉ ለሚኖሩ የብሔረሰቦቹ አባል ላልሆኑ ዜጎች ሙሉ መብት የማይሰጥ መሆኑና ክልሎችን በቋንቋ መለኪያ ብቻ ማዋቀሩ የሕዝቦች ትስስርን ካላሉት መሀል እንደ አንድ ትልቅ ምክንያት ሊቆጠር ይችላል፡፡ የየብሔሮቹ ልሂቃን ባለመታከት (Proactive) ያካሄዱትም የፕሮፖጋንዳ ሥራ ሌላው ምክንያት እንደሆነ ነው የምረዳው፡፡ ዛሬ በልሂቃኑ መሀል ብቻ ሳይሆን በብሔረሰቦችም መሀል ደፍርሶ ለሚታየው ግንኙነት ምክንያቶችም እነዚሁ ይመስሉኛል። ይሁን እንጂ አሁንም አልመሸም፡፡ የተረጋጋችና ሰላሟ የሰፈነባትን ጠንካራ አገር ለመገንባት ከተፈለገ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ዜጋ የመፍጠሩ ሥራ የልሂቃኑም ሆነ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት፡፡ የጋራ ዓላማና የጋራ ዕጣ ፈንታ አለኝ የሚል የአንድነት አስተሳሰብ ስሜት የሚያድርበት ዜጋ መፍጠሩ ግድ ይሏል፡፡ አለበለዚያ እንደ አገር መቀጠል አይቻልም።

በክፍል አንድና እንዲሁም በክፍል ሁለት ልሂቃኑ በተለያዩ አገሮች ውስጥ በአገረ ብሔር ግንባታ ላይ ያደርጉትን አዎንታዊ አስተዋጾኦ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ የአንድ ቋንቋና አንድ ባህል ባላቸው አገሮችና የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎችና የተለያየ ባህል ያላቸውን ሕዝብ ባቀፈች ስዊዘርላንድ የተደረጉ ተሞክሮዎችንም ለመዳሰስ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ በሁሉም አገሮች ላይ የተሄደበት መንገድ ይለያይ እንጂ መድረሻቸው አንድ እንደሆነ ነው፡፡ ጠንካራ ዜጋ መፍጠር ነው፡፡ መልዕክቱ እኛም በአገራችን ‹‹እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ›› የሚል ዜጋ ቀርፀን ማውጣት እንዳለብን ነው። በእርግጥ ይኼ የሚባለው ኢትዮጵያዊነት ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት በስምምነት የሚሆን ነገር ይሆናል፡፡ ይህ ሲባል ግን የጋራ የሆኑ ታሪኮቻችንና ተምሳሌዎቻችንን (Symbols) በዜሮ እያባዛን እንሄዳለን ማለት አይሆንም፡፡ ሊተገበሩ የማይችሉ ነገሮችን ወደ ፊት ማምጣት የሚበጅም አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሁሉንም ብሔረሰቦች ቋንቋ የሥራ ቋንቋ ማድረግ አይቻልም፡፡ የባቢሎን ግንብ ገንቢዎች ሊያደርገን ስለሚችል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...