የዓለም ባንክ ለሶላር ቴክኖሎጂ አቅርቦት ድጋፍ 40 ሚሊዮን ዶላር መድቧል
ተቀማጭነቱ በቻይና ሸንዘን ግዛት የሆነውና ሸንዘን ለሚ ቴክኖሎጂ የተሰኘው ኩባንያ፣ ዘመናዊና የጥራት ደረጃቸውን ያሟሉ የሶላር ቴክኖሎጂ ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማከፋፈል ከአገር ውስጥ የሶላር ኩባንያዎች ጋር መሥራት እንደሚፈልግ ገለጸ፡፡
ሸንዘን ለሚ፣ ሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ምርቶቹን ለአገር ውስጥ የሶላር ምርቶች አከፋፋዮች አስተዋውቋል፡፡ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩና አንፑል የሚያበሩ፣ የሞባይል ስልክ ቻርጅ የሚያደርጉና ሌሎችም የቤት ቁሳቁሶችን የሚያንቀሳቅሱ መሣሪያዎች ለዕይታ አቅርቧል፡፡ ኩባንያው በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የመንገድ መብራቶችን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ምርቶች እንደሚያመርት አስታውቋል፡፡
የሸንዘን ለሚ ቴክኖሎጂ መሥራች ጆይስ ቼን ኩባንያቸው እ.ኤ.አ. 2004 ጀምሮ ጥራት ያላቸው የሶላር ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያመረተ ሲያቀርብ እንደቆየ ገልጸው፣ ጥራት የሌላቸው ምርቶች ገበያ ውስጥ በብዛት ስለሚገቡ የኅብረተሰቡ እምነት እየተሸረሸረ እንደመጣ ጠቁመዋል፡፡ የሸንዘን ለሚ የሶላር ምርቶችን ከዓለም ባንኩ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽ (አይኤፍሲ) ጋር ተባብሮ በመሥራት የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጣላቸውን ምርቶች እንደሚያቀርብ ጆይስ ቼን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን መነሻ በማድረግ ኩባንያው የተመሰከረላቸውን የሶላር ምርቶች ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ በስፋት ማቅረብ እንደሚፈልግም አስታውቋል፡፡
የዓለም ባንክ አይኤፍሲ ተወካይ አስቴር ምሕረት፣ ኮርፖሬሽኑ ‹‹ላይቲንግ ኢትዮጵያ›› በተሰኘው ፕሮግራሙ ለሶላር ምርቶች አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ‹‹75 በመቶ የሚሆነው (75 ሚሊዮን) ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ተጠቃሚ እንዳልሆነ፤›› ገልጸው፣ ይህም የሆነው ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት ኅብረተሰቡን ለማገናኘት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ስለሚጠይቅ እንደሆነና ሊቀርብ የቻለውም ይህንን ያህል ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
አይኤፍሲ ጥራት ያላቸው የሶላር ምርቶች እንዲገቡ፣ የሶላር ምርቶች አከፋፋዮችን አቅም በማጎልበት፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ ምቹ ፖሊሲ እንዲኖር ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጀርመኑ የተራድኦ ድርጅት ጂአይዜድ፣ ከግሉ ዘርፍ ተዋንያንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ጥራታቸውን የጠበቁ የሶላር ምርቶች ወደ አገር ለማስገባት ሲፈለግ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ይህንን ችግር ለመቅረፍ፣ አይኤፍሲ 40 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ገልጸው፣ እስካሁንም 11 ሚሊዮን ዶላር ለተጠቃሚዎች በብድር መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጥራት ያላቸው የሶላር ምርቶች ለኅብረተሰቡ እንዲቀርብ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው፤›› ያሉት አስቴር፣ 8.5 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ የሶላር ምርቶች በተለይ ለገጠሩ ሕዝብ በማዳረስ የነጭ ጋዝና የማገዶ ጭስ ብክለትን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
የሸንዘን ለሚ ኃላፊዎች የሶላር ምርቶቻቸውን ለገጠሩ ነዋሪ በዱቤ ሽያጭ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አርሶ አደሩ በአንድ ጊዜ 4,000 ወይም 5,000 ብር ክፈል ቢባል ላይኖረው ይችላል፡፡ አንደኛው አማራጭ ከማይክሮፋይናንስ ተቋማት ተበድሮ መክፈል ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ ሸንዞን ለሚ በካርድ የሚሠሩ ምርቶችን ቀስ በቀስ በዙር የሚከፍሉበት አሠራር ይዘረጋል፤›› ብለዋል
ደንበኛው ክፍያ ሳይፈጽም ቢቀር፣ ከማዕከል መሣሪያው አገልግሎት እንዲያቋርጥ ይደረጋል ያሉት ኃላፊዎቹ፣ ክፍያውን በፈጸመ ጊዜም በካርዱ አማካይነት ኃይል መልሶ ማግኘት እንዲችል የሚደረግበት አሠራር እንደተዘረጋ ገልጸዋል፡፡
የቻይናው ሸንዘን ለሚ ኩባንያ በበርካታ የእስያና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሲሠራ እንደቆየ የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ወደ አፍሪካ ለመምጣት ግን እንደዘገዩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ከኢትዮጵያውያን የሶላር ምርቶች አስመጪዎች ጋር በመተባበር ጥራት ያላቸውን የሶላር ቴክኖሎጂዎች የኅብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡