Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሙያ ደኅንነት ከአሠሪና ሠራተኞች አንፃር

የሙያ ደኅንነት ከአሠሪና ሠራተኞች አንፃር

ቀን:

የሙያ ደኅንነት ሳይንስ በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓና በአሜሪካ ከተከሰቱ አብዮቶች ጋር ተያይዞ የመጣ ሲሆን፣ ለዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) መመሥረት ምክንያት ሆኗል፡፡

በሙያ ደኅንነትና ጤንነት አመራር ሥርዓት ዙሪያ ለአሠሪዎች በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ቡድን መሪው አቶ ካሳሁን በዛብህ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት አባል ከሆነች በኋላ የሠራተኛ ደኅንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ተቀብላለች፡፡

በስምምነቱም መሠረት የሠራተኛ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት በየድርጅቱና መሥሪያ ቤቱ ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚያስገድድ መመርያ በ1998 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡ ነገር ግን በምርትና በአገልግሎት ዘርፎች ከተሰማሩት የግል ድርጅቶች መካከል መመሪያው የሚያስገድደውን ኮሚቴ የመሠረቱት በጣም ጥቂት እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ሳይንስ ሲነሳ ብዙዎቹ አሠሪዎች ሕጉ ለሠራተኛው ብቻ የወገነ አድርገው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን አመልክተው ጥቅሙ ለአሠሪውና ለሠራተኛው ብሎም ለአገር መሆኑ መገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹የሙያ ደኅንነትና ጤንነት መጠበቅን መሠረት ያደረገ መርህ አለው፤ መርሁም የሥራ ቦታዎች ምቹና ከአደጋ የተጠበቁ እንዲሆኑ የሚያደርግ፣ ጤናማና አምራች ዜጋን የመፍጠር ትልም ያነገበ፣ የሥራ ውጤትን ለማሳደግ የሚያስችል የተደራጀ፣ በሥርዓት የሚመራና በቅንጅት የሚፈጸም እንቅስቃሴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ለሚነሱ ግጭቶች፣ በሥራ ቦታዎች አለመግባባትና አለመረጋጋት እንዳይኖር፣ በሥራ ቦታ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲሰፍን ከሚያደርጉት አጀንዳዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ሳይንስ ነው፡፡ ይህን የአሠራር ሳይንስ ተግባራዊ የሚያደርጉ ድርጅቶች ምርታማ እንደሆኑ፣ ድርጅቱ ሲያተርፍ ሠራተኛውም ከትርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሳይንሱን እንደ ወጪ በመቁጠር ተግባራዊ ያላደረጉ ድርጅቶች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በጭቅጭቅ ስለሚያሳልፉ የድርጅቱ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ እንዲህ ያሉ አሠሪዎች ሠራተኛውን የመቀነስና የማባረር ዕርምጃ ከመውሰድም ወደኋላ አይሉም፡፡

በየትኛውም አካባቢና በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ውስጥ አምስት የጤና ጠንቆች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከፎቶ ኮፒዎችና ከፕሪንተሮች የሚወጡ የወረቀት ብናኞች በቢሮ አካባቢ ከሚከሰቱ የጤና ጠንቆች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ኬሚካል በብዛት በሚጠቀሙ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ለተለያዩ የጤና ጠንቆች እንደሚጋለጡ ጠቁመው የሠራተኛው ደኅንነትና ጤንነት ላይ አደጋ እንዳያስከትሉ መከላከልና መጠበቅ የግድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የሠራተኛውን ደኅንነትና ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ አሠሪው ማዘጋጀት፣ በዝግጅቱም ላይ ሠራተኞቹን በተወካዮች ማሳተፍ ግድ ይላል፡፡ የሠራተኛውን ደኅንነትና ጤንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም አዋጆቹን ደንቦቹንና መመሪያዎቹን ለመፈጸም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመተባበር የአሠሪው ቁርጠኝነት ፖሊሲው ላይ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ከቡድን መሪው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በፖሊስውም ላይ የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ተፈርሞ ማንኛውም ሰው በግልጽ ሊያየው በሚችል መልኩ ቢሮ ውስጥ መቀመጥ እንዳለበት፣ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጀምሮ በተላላኪነትና ፅዳት ሥራ የተሰማሩ ሠራተኛ በሙሉ በሙያ ደኅንነትና ጤንነት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

በቢሮው የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙአየሁ ታደገ ‹‹የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አስፈላጊ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ሁለቱም ወገኖች (ሠራተኛውና አሠሪው) መብቶቻቸው ተከብሮላቸውና ግዴታዎቻቸውንም በመወጣት ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገቶች የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የአሠሪው፣ የሠራተኛውና የመንግሥት ፍላጎቶች ተገቢውን ፍትህ ሊያገኙ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የአሠሪዎች ፍላጎት ሠራተኛን የመቅጠርና የማሰናበት፣ አትራፊ ሆኖ የመወጣት፣ አትርፎ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት መፍጠርና የመሳሰሉት ይሆናሉ፡፡ የሠራተኛው ፍላጎት ደግሞ የተሻለ ሕይወት መምራት፣ ለዚህም ዕውን መሆን የተሻለ ገቢ፣ ደመወዝ፣ የሥራ ማትጊያና ደኅንነቱ በተጠበቀ የሥራ ከባቢ ውስጥ መሥራት ወዘተ ናቸው፡፡

መንግሥትም የተለየ ፍላጎት እንደሌለው፣ ነገር ግን ሁለቱም ዜጎቹ ስለሆኑ መብቶቻቸውን ማስጠበቅ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲከፈትላቸው ማትጋት፣ መጎትጎትና ማንቀሳቀስ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

ይህም ዕውን የሚሆነው ሦስቱም አካላት ማለትም ሠራተኛው፣ አሠሪውና መንግሥት ተቀራርበው ሲወያዩና ሲግባቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ባለመሆኑ በሥራ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል፡፡ በየጊዜውም በተለይ ከሠራተኛው በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ‹‹በነፃ መደራጀት አልቻልንም›› የሚለው ቅሬታም የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን መደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑ አሠሪው የመስጠትና የመከልከል መብት እንደሌለው አቶ ብዙአየሁ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የመደራጀት ጉዳይ ሲነሳ የት ነው የሚሰበሰቡትና የሚደራጁት የሚለው ጥያቄ እንደሚነሳ፣ በድርጅቱ ግቢ ውስጥ ለመሰብሰብና ለመደራጀት የድርጅቱ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ፣ ይህም የሠራተኞቹ የመደራጀት መብት በአሠሪው ፈቃድ ላይ እንዲወሰን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ አሠሪዎች ደግሞ እንዲህ ያሉ ማኅበራት ጫና ይፈጥሩብናል የሚል ሥጋት ስለሚያድርባቸው ማኅበሩ እንዳይቋቋም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

ከአሠሪው ጋር የኅብረት ስምምነት ለማድረግ ያለው ውጣ ውረድ፣ እንዲሁም አሠሪው በቃል የገባውን ውል በጽሑፍ ለመስጠት ጊዜ መፍጀቱና የአለአግባብ የሠራ ውል ማቋረጥም ከተግዳሮቶቹ መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሠራተኛ ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው በሕግ ብቻ ሳይሆን በመነጋገርና በውይይት መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ቀደም ሲል የመንግሥት የነበሩና ከጊዜ  በኋላ ወደ ግሉ ዘርፍ በዞሩ የልማት ድርጅቶች የነበሩ የሠራተኛ ማኅበራት እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዳይንቀሳቀሱ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚፈጠርባቸው አስረድተዋል፡፡

በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ  ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ኃላፊዎች ‹‹ሠራተኞቹ አይሰሙንም፣ የሥራ ፍላጎትም የላቸውም፣ መመርያን አያከብሩም፣ ፈቃድ ያበዛሉ፣ ከሥራ ገበታም ይቀራሉ፣ ድርጅቱ ውስጥ ገብተው ቁጭ ይላሉ እንጂ አይሠሩም›› የሚል እሮሮ እንደሚያሰሙ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ከ100 ዓመት በላይ የቆየ ከመሆኑ አንጻር ችግር ሊኖርበት ይችላል፡፡ አዋጁ ይሻሻላል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጥያቄ በሚያስነሱ ጉዳዮች ዙሪያ የአሠሪና ሠራተኛ ተወካዮች ከመንግሥት ጋር ማኅበራዊ ምክክሮችን ማካሄድ፣ በድርጅቱ ደረጃ አሠሪና ሠራተኛ በየጊዜው እየተገናኙ መወያየት፣ በየሁለት ወይም በየሦስት ዓመት የኅብረት ስምምነት ማድረግ አማራጭ መፍትሔ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር) ‹‹በአገሪቱ የሚታዩ ችግሮች ብዙ ቢሆኑም በማኅበራዊ ውይይት ይፈታል ብሎ ኮንፌዴሬሽኑ ያምናል፡፡ ማኅበራዊ ውይይት መቀራረብ፣ መተጋገዝ፣ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትና የጋራ ማድረግን ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

አሠሪዎች ይህ ዓይነቱን አካሄድ ተከትለው ከሠሩ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና አገራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርሱ እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊም፣ በዚህ ዓመት በኢንዱስትሪዎች አካባቢ እንዲሁም በአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት መካከል እየታዩ ያሉት ወጣ ያሉ ነገሮች የከተማዋን ሰላም እየተፈታተኑ መጥተዋል ብለዋል፡፡ መንስዔውም ሠራተኛው ከሚያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች፣ አሠሪው ከሚያሳየው ፍላጎትና በመንግሥት አካባቢ ከሚታየው ክፍተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪው ሰላም መሸበር ቆይቶ በከተማዋ ያለውን መረጋጋት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል፣ ይህ ዓይነቱንም ሁኔታ መንግሥት በቸልታ ከማለፍ ይልቅ መፍትሔ በመስጠት ለአገር፣ ለከተማዋና ለዜጎቹ ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ጳውሎስም፣ በአዲስ አበባ ከተማ  የሥራ ዕድል የመፍጠርና ድህነትን የመቀነስ ሸክምና ኃላፊነትን በብዛት የያዙት የግል ድርጅቶች ቢሆኑም፣ ከመካከላቸው አንዳንዶቹ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት የተሳለጠ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታቸውን የመዘንጋትና የሠራተኛውን በማኅበር መደራጀት ያለመፈለግ አዝማሚያ ይስተዋልባቸዋል ብለዋል፡፡

ለአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ምቹ ሁኔታ ካልፈጠሩት መካከል አንዱ የሠራተኛው ደኅንነትና ጤንነት ጥበቃ የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች ያለመሟላትና ያሉትንም ግብዓቶች በአግባቡ ያለመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሠራተኛው በኩል ግብዓቶችን ማውደምና እንደራስ ንብረት አድርጎ አለማየት የመሳሰሉ ሁኔታዎች እንደሚታዩ ነው ያመለከቱት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን የቀጠሩ 47,000 ድርጅቶች አሉ፡፡ 120,000 የሚሆኑ ሠራተኞች በመንግሥት ድርጅቶች የተቀጠሩ ናቸው፡፡ በግሉ ዘርፍ ከተሰማሩ ሠራተኞች መካከል በማኅበር የተደራጁት ከ80,000 እንደማይበልጡና የሠራተኛውም ማኅበራት 500 ብቻ እንደሆኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ባለፉት አሥር ወራት ውስጥ በ40 የግል ድርጅቶች በጥቃቅን ጉዳዮች ሥራ የማቆም፣ በሠራተኛውም ያልሆነ የአመጽ ምልክቶችን የማሳየት ነገር ታይቷል፡፡ አሠሪዎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን መቀነሳቸው ታይቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በግሎባል ሆቴል በተካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ አራት የሠራተኛ ማኅበራትና የአሠሪ ተወካዮች ታድመው ነበር፡፡ በየትኛውም ሴክተር የሥራ ጥራትና የሙያ ብቃት ክፍተት በስፋት እንደሚታይ፣ የሠራተኛ ፍልሰት፣ ከሥራ በተደጋጋሚ የመቅረት፣ ደካማ የሥራ ባህል መኖሩን  የሚያሳዩ አስተያየቶች ከመድረኩ ተሰንዝረዋል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ቢኖርም፣ ሕጉ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉት፣ ነባራዊውን ሁኔታን ያላገናዘበ፣ ከዘመኑም ጋር አብሮ እንደማይሄድና ሊሻሻል እንደሚገባም ተጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...