Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጤናን የሚዘርፉ ዘይቶች

ጤናን የሚዘርፉ ዘይቶች

ቀን:

የምግብ ዘይት አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዚህም የሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የምግብ ዘይትን ለተለያዩ ምግቦች የመጠቀሙ ዝንባሌ በከተሞች መዘውተሩ እንደምክንያት ይነሳሉ፡፡ የማኅበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እየተለወጠ መምጣትም ለምግብ ዘይት አጠቃቀም ከፍ ማለት ተጠቃሽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ 16 ዓይነት ዘይቶች በአገር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ቢያንስ ሰባቱ በየሰፈሩ በአገር ደረጃ የሚመረቱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ዘጠኙ ደግሞ የተለያየ ብራንድ (መለያ) ያላቸውና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ተከፍሎባቸው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡

ሁሉም ዘይቶች ከጥራትና ከጤና  አንጻር በተለያየ ሁኔታ አስፈላጊው ክትትል ካልተደረገባቸው በስተቀር አንዳንድ ጎጂ የሆኑ ባህሪያት አሏቸው፡፡

በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ በገበያ ላይ በሚገኙና በ16ቱ የምግብ ዘይቶች ላይ ያተኮረ የዳሰሳ ጥናት እና የላቦራቶሪ ፍተሻ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ያተኮረው አጠቃላይ ይዞታቸው እንዴት ነው? በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠላቸውን መስፈርት ከማሟላት አንጻር የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ተሟልቶላቸዋል ወይ? ከምግብ ይዘታቸው አንጻር ያላቸው ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለው ላይ ነው፡፡

ለጤና ጎጂ ከሆኑ አንዳንድ ሁኔታዎች አንጻርም፣ በላቦራቶሪ እንስሳት/አይጦች ላይ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ዘይቶች ላይ እንደ ዋና ክፍተት የታየው የአመራረት ጥራቱ በጣም ደካማ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ኤባ በውስጣቸው የሚኖረው የጥራት መጠን ሊኖር ከሚገኘው ዝቅ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ሊይዙት የሚገባው የአሲድ መጠንም ካለው ደረጃ ከፍ ብሎ [ከፍ ማለቱ የሚጎዳ ነው] ተገኝቷል፡፡

በተለይ የአመራረት ሒደቱ በጣም ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑን፣ የምርቱ አጠቃላይ መግለጫ ላይ ያለውና መሟላት የሚገባቸው መረጃዎች ተሟልተው አለመገኘታቸውም በጥናቱ ታይቷል፡፡ ዘይቶቹ መቼ እንደተመረቱና መቼ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆኑ የሚገልጽ ነገር እንደሌለ የምግብ ይዘታቸውም ሆነ የቅመማ ቅማሞች መጠንም ተፅፎ እንደማይታይ ጠቁመዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረቱ የምግብ ዘይቶች ከጤና አንጻር በበጎ ጎን የሚወሰደው የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም የምግብ ድርጅት ጤናን ሊጎዱ ይችላሉ ብለው ካስቀመጧቸው የተለየዩ ንጥረ ነገሮች አንጻር ብዙም ችግር ስለሌለባቸው ነው፡፡ በተለይ በረዥም ጊዜ አጠቃቀም ሊመጡ ከሚችሉ በሽታዎች አንጻር ሲታዩ፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ፈሳሽ ዘይቶች በጥሩ ሁኔታ እንዳሉና ብዙም ችግር እንደሌለባቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡

የተለያየ ባህርያት ያላቸውና ከውጭ የሚገቡ ዘጠኝ የዘይት ዓይነቶችም በጥናቱ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የተለያዩ መለያዎች ያሉትና በተለምዶ ፓልም ኦይል ወይም በሩም ቴምፕሬቸር የሚረጋው ዘይት አንዱ ሲሆን፣ ሌሎችም ከውጭ የሚገቡት ፈሳሽ ዘይቶች የአኩሪ አተር፣ የወይራ፣ የሱፍ ዘይቶችም በጥናቱ ከተካተቱ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ዘይቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠላቸውን ደረጃ ያሟላሉ ወይ? የሚለውን ለመፈተሽ እንደተቻለ፣ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገቡ የውጭ ዘይቶች የተጠቀሰውን ስታንዳርድ በማሟላት ምንም ክፍተት እንደሌለባቸው ታይቷል፡፡ ከዚህም ሌላ አንዳንድ ፊዚካል ዳሰሳዎች እንዳሉ፣ እነርሱም ስፔስፊክ ግራቪቲ፣ የአዮዲንና የአሲድ ይዘቶች እንደሆኑና እነዚህም የተቀመጠላቸውን ደረጃ ያሟላሉ ወይ? በሚለውም ዙሪያ ፍተሻ ተደርጎ ከአዮዲን ይዘት ውጪ ሌሎቹ የተቀመጠው ደረጃ ላይ የሚያርፉ እንደሆነና በዚህም ዙሪያ የታየ ክፍተት እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

ከተመጣጠነ ምግብ አንጻር ምን ያሟላሉ? የሚለውን ለማየት በተሞከረበት ፍተሻ፣ የዓለም ጤናና ምግብ ድርጅት በ1995 ዓ.ም. በተለይ ሳቹሬትና ፋቲ አሲድ ለብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚወሰድ ከሆነ ከልብ ጋር የተያያዙና የተለያዩ ዓይነት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከማምጣት አንፃር ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳለው አረጋግጧል፡፡

16ቱም የምግብ ዘይት ዓይነቶች ንጥረ ነገሮችን በመያዝ ረገድ ያላቸው ይዘት ምንድነው? የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት እንደተደረገ፣ የተደረገውም ጥናት ፈሳሽ ዘይቶች ብዙም ችግር እንደሌለባቸው፣ ምክንያቱም የፋቲ አሲድ ይዘታቸው በጣም አነስተኛ እንደሆነ፣ ነገር ግን የሚረጉ ዘይቶች ወይም ፓልም ኦይል  የሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ ይዘታቸው ከፍተኛ ማለትም 50 በመቶ  ገደማ የሚሆነው ይዘታቸው ይህንኑ ዓይነት ፋቲ አሲድ እንደያዘ አሳይቷል፡፡

የፋቲ አሲድ መጠን ከፍተኛ መሆን ከጤና አንጻር ሊያስከትል የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት ለማየት ለየት ያለ ዝርያ ባላቸው 94 አይጦች ላይ ለአራት ወራት ያህል ተከታታይ ጥናት ተደርጓል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ፣ የተለያዩ የፈሳሽና የሚረጉ ዘይቶችንና ለማመሳከርያ የሚሆኑ ኮሌስትሮሎችን በመጠቀም በተጠቀሱት አይጦች ላይ በተካሄደው በዚሁ ጥናት የተገኘው ውጤት፣ ሳቹሬትድ ፋቲ አሲድ ያለበትን ዘይት የተጠቀሙ አይጦች ላይ የኮሌስትሮል መጠናቸው ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንጻር የረጋ ዘይት የኮሌስትሮል መጠን በመጨመር ጤናን ለማቃወስ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱት ፈሳሽ የምግብ ዘይቶች ከጤና አንጻር ምንም ችግር እንደሌለባቸው ቢታይም፣ የአመራረት ይዘታቸው ግን ክፍተት አለበት፡፡ የፓልም ኦይል ወይም የረጋ ዘይትም ትልቅ አደጋ አለው፡፡

የሰው ልጅ ፓልም ኦይልን መጠቀም የጀመረው ከ5000 ዓመት በፊት ነው ያሉት ዶ/ር ኤባ፣ ፓልም ኦይል ከሌላው የሚለየው ሙቀትን ተቋቁሞ ምግብን የማብሰል ጥንካሬ ስላለው አብዛኞቹ ምግብ አብሳዮችና የምዕራብ አገሮች የሚጠቀሙት ፓልም ኦይልን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም አጠቃቀማቸው ግን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ፣ ዛሬም፣ ነገም ወይም ሁልጊዜ ፓልም ኦይል እንደማይጠቀሙና የተለያዩ የዘይት ዓይነቶችን ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶች እንደሚጠቀሙ አመልክተዋል፡፡

ይህ ዓይነቱን አጠቃቀም በሚከተሉና በሚያዘወትሩ አገሮች የሚከሰተው የጤና ጉዳት ያነሰ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቱና ምንም አማራጭ የሌላቸው ማኅበረሰቦች ሁልጊዜ ስለሚጠቀሙበት ለጤና ጠንቅ ተጋላጭነታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በኢትዮጵያም 81 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ዘይት ፍጆታ የሚይዘው ይኸው ፓልም ዘይት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተለያየ ዓይነት የጥራት ደረጃ ያላቸው የፓልም ዘይቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን እያስገባች ያለችው በዋጋ ረገድ በጣም አነስተኛ፣ በጥራት ረገድም ክፍተት ያለበትን ፓልም ዘይት ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ዋጋ ተጨምሮ ጥራት ያለውን ፓልም ዘይት መግዛት የተሻለ አማራጭ መሆኑንና ለዚህም ዕውን መሆን ጉዳዩ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው አጠቃላይ የዘይት ፍጆታ ዛሬ ካለው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ በ2004 ዓ.ም. 270,000 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ የዘይት ዓይነቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. ያለው አሃዝ ደግሞ እስከ 450,000 ሜትሪክ ቶን ደርሷል፡፡ ይህም የዘይት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በአገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ በሚገቡ በእነዚሁ ዘይቶች ላይ ተገቢውን የላቦራቶሪ ምርመራ ያደረገው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ የጥናቱን ውጤቱ ለጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ማድረጉን፣ ሚኒስቴሩ ደግሞ የምርምሩን ውጤት በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በጽሑፍ ማቅረቡን ዶ/ር ኤባ ገልጸዋል፡፡

የዘይት ግዥውን በተመለከተ ንግድ ሚኒስቴር አማራጮችን ፈትሾ እንዲያቀርብ ከወራት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደብዳቤ ቢላክለትም፣ እስካሁን የታየ ለውጥ ግን የለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...