Thursday, February 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 ብሔራዊ ባንክ በዓይነት ለሚገኝ የውጭ ብድር መመርያ አወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በዓይነት ለሚገኝ የውጭ ብድር መመርያ አወጣ ነው፡፡ በዓይነት የሚገኝ የውጭ ብድር (External Loan in Kind) መመርያ ቁጥር FXD/61/2019 ተግባራዊ እንዲሆን ለሁሉም ባንኮች ተልኳል፡፡

ይህ መመርያ በዋናነት የሚያገለግለው፣ ኤክስፖርት የሚያደርጉና የውጭ ምንዛሪ የሚያመነጩ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አገር በቀልና የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው በዚህ መመርያ አድልኦ አድርጎብናል ያሉ ገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርት የሚተኩ አገር በቀል ባለ ፋብሪካዎች፣ አቤቱታቸውን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

አገር በቀል ባለ ፋብሪካዎች የቅሬታቸው ማጠንጠኛ ቀደም ሲል የወጣው የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ (Suppliers Credit FXD/47/21017) በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተቋቋሙ ፋብሪካዎችን ያገለለ ከመሆኑም በላይ፣ ለከፍተኛ ኢፍትሐዊ የንግድ ውድድር የዳረገ መሆኑን ነው፡፡ መመርያው እንዲሻሻል የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ብሔራዊ ባንክ በድጋሚ በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተመሠረቱ ፋብሪካዎችን ያገለለ መመርያ አውጥቷል ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ መመርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዓይነት በሚገኝ የውጭ ብድርን በሚመለከት ባወጣው አዲስ መመርያም በኢትዮጵያውያን የተመሠረቱ አምራቾችን ሳያካትት መቅረቱ ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡

በመመርያው ብቁ ተወዳዳሪዎችና መሟላት የሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን በሚዘረዝረው አንቀጽ 4 ላይ በወጪ ንግድ የተሰማሩ ላኪዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችና የውጭ ኢንቨስተሮች በዓይነት ወይም በዕቃ ለሚደረግ ግዥ የብድር ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡

ይህንን ብድር ለማግኘት መሟላት ከሚገባቸው መሥፈርቶች መካከል የብድር ስምምነት ረቂቅ ሰነድ፣ የስምምነቱ ዓይነት ዝርዝር፣ ወለድ፣ ተፈጻሚ የሚሆኑ ክፍያዎች፣ የብድር አመላለስ ዘዴ፣ የጊዜ ሰሌዳና የተበዳሪና አበዳሪ ግንኙነት ይገኙበታል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የፋብሪካ ባለቤት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ምርቶችን የመተካት ጥረትን በተገቢው መንገድ ተረድቶ ማስተናገድ ተስኖታል፡፡

‹‹ብሔራዊ ባንክ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርቱ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ጭምር በልዩ ሁኔታ በመደገፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩና ገቢ ምርት የሚተኩ በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የቀረፃቸው መመርያዎች ናቸው፤›› በማለት ባለሀብቱ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

በመስከረም 2005 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769፣ ‹‹ባለሀብት›› ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ያደረገ የአገር ውስጥ  ወይም የውጭ  ባለሀብት  እንደሆነ በአንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ተመልክቷል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ማንኛውም ባለሀብት ከውጭ የተበደረውን የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው  መመርያ መሠረት እንዲያስመዘግብ ከማዘዝ ውጪ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት በማለት የከፈለበት ሁኔታ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በአንቀጽ 36 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይም የሚደነግገው የውጭ ባለሀብት ሥራውን ለማንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ መክፈት እንደሚችል ከመግለጽ ያለፈ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብት ከውጭ መበደርን የሚከለክል ነገር የለውም ሲሉ ባለሀብቱ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው ሁለቱም መመርያዎች የኢንቨስትመንት አዋጅን ይቃረናሉ፤›› በማለት የገለጹት ባለሀብቱ፣ ‹‹የውጭ አቅራቢዎች ብድርም ሆነ በዓይነት የሚገኝ የውጭ ብድር የሚከፍለው አገሪቱ ካፈራችው ሀብት ሆኖ እያለ፣ የአገሪቱ ዜጎች ይህንን ዕድል መነፈጋቸው የዜግነት ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤›› ሲሉ ብለዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መሥሪያ ቤታቸው ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ መመርያን ይቃወማል፡፡

‹‹መመርያውን ለማስቀየር ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየተነጋገርን ነው፤›› በማለት አቶ ተካ ገልጸው ነበር፡፡  አዲሱን መመርያ በተመለከተ አቶ ተካንም ሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች