በየትኛው የካቢኔ ውሳኔ እንደተላለፈ እንደማይታወቅ ተጠቁሟል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት በክፍለ ከተማ ደረጃ ለተሾሙ ኃላፊዎች፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለጤና ቢሮ ሐኪሞች፣ ለከተማው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ለፍርድ ቤት ዳኞች በኪራይ ተሰጥተው የነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግዥ እንዲዘዋወርላቸው መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ፡፡
አስተዳደሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለተሿሚዎች የተሰጡት በአነስተኛ ኪራይ በመሆኑና ቤቶቹ ደግሞ የተገነቡት በቦንድ ብድር በተገኘ የቤት ፋይናንስ ከመሆኑ አንፃር፣ በየወሩ መከፈል ያለበት የብድር ዕዳ ሊከፈል ባለመቻሉ ለከፍተኛ የቦንድ ብድር ወለድ ወጪ በመጋለጡ፣ በካቢኔው ውሳኔ ሊተላለፍ መቻሉን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
የሥልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት ሲቀራቸው አቶ ድሪባ ኩማ መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በካቢኔያቸው ያስተላለፉት ውሳኔ እንደሚያስረዳው፣ የአስተዳደሩ የተለያዩ ክፍሎች አመራሮች በጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ቋት ውስጥ የሚገኙ ከሆነ፣ ዕጣ ሲወጣላቸው በኪራይ የተሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤት በስማቸው ይተላለፍላቸዋል፡፡
በነባር የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ቋት ውስጥ ያልተካተቱ አመራሮች ተመዝግበው በቁጠባ ሥርዓቱ እንዲያልፉ ተደርጎ ቤቱ ሲደርሳቸው ወይም ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ እየኖሩበት ያለው የጋራ መኖሪያ ቤት በስማቸው እንዲዛወርላቸው ካቢኔው ውሳኔ ማስተላለፉን ሰነዶቹ ያረጋግጣሉ፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ አስተዳደሩ ውስጥ ካሉ ወይም በውሳኔው ከተጠቀሱት 797 አመራሮች ውስጥ 290 ግለሰቦች የቁጠባ ሒሳብ እንዲከፍቱ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ዝርዝራቸው ተልኮለት ተግባራዊ ማድረጉን፣ በባንኩ የደንበኛና የመኖሪያ ቤቶች ብድር ዳይሬክተር አቶ መዝገበ ይፍሩ ፊርማ ወጪ በተደረገ ደብዳቤ ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
የቀድሞ ካቢኔ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የሚመለከታቸው የአስተዳደሩ ተቋማት ውሳኔውን ተግባራዊ አድርገው የነበሩ ቢሆንም፣ የምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ካቢኔ ውሳኔውን በውሳኔ መሻሩ ወይም ሌላ መመርያ ማውጣት አለማውጣቱ ይፋ ባልተደረገበት ሁኔታ፣ ቤቶቹ እየተላለፉ መሆኑን ሰነዶች ያሳያሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ለአምስት ክፍላተ ከተሞች አስቸኳይ መልዕክትና ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ በኤጀንሲው ወጪ የተደረገ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ካቢኔው በወሰነው መሠረት (የትኛው ካቢኔ እንደሆነ አይገልጽም) በኪራይ የተሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወለድ መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ እያስወጡ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ በቤቶቹ ላይ ድጎማ አይደረግም፡፡
በመሆኑም በኪራይ የተላለፈላቸው አመራሮችና ተቋማት በግዥ እንዲተላለፍላቸው መወሰኑንና በክፍላተ ከተሞቹ ሥር የሚገኙ የወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ ለአመራሮቹና በልዩ ሁኔታ ቤት ለተሰጣቸው ግለሰቦች በቅፅ መረጃ ሞልተው እንዲልኩ ታዘዋል፡፡
ኤጀንሲው ደብዳቤውን ወጪ ሲያደርግ የትኛው የከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማለትም የቀድሞ የአቶ ድሪባ ኩማ ወይም የምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንደሆነ ካለመገለጹም በተጨማሪ፣ ለሚመለከታቸው አካላት በተዋረድ ያስተላለፈበት ቀንና ቁጥር አለመገለጹ ታውቋል፡፡ በአቶ ድሪባ ካቢኔ የተወሰነው ውሳኔና ቃለ ጉባዔ፣ ቤቶቹ የሚዘዋወሩት በ1997 ዓ.ም. በጋራ ቤቶች ምዝገባ ቋት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አመራሮች ዕጣ ሲወጣላቸው በማለቱ ከሆነ፣ በግልጽ ተነግሮና በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ በአስተዳደሩ ለሚመለከታቸው ተቋማት አሳውቆ መሆን እንደነበረበት፣ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ኃላፊዎች አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአቶ ድሪባ ካቢኔ ውሳኔ ተሽሮም ከሆነ ምክንያቱ ተገልጾ ቃለ ጉባዔ ጭምር መያያዝ እንደነበረበትም አክለዋል፡፡ በተጨማሪም ካቢኔው አዲስ ውሳኔ አስተላልፎ ከሆነም በአጠቃላይ ማለትም ለመምህራን፣ ለመንግሥት ሠራተኞችና ለችግረኞች (የደሃ ደሃ) ተከራዮችም በተመሳሳይ ሊተላለፍላቸው ይገባል እንጂ፣ ከተማው መክፈል አቅቶታል በሚል ለተሿሚዎች ብቻ በግዥ እንዲተላለፍላቸው ተወስኗል ማለት ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ለከተማው አመራሮች በግዥ እንዲተላለፍላቸው ያደረገው የአቶ ድሪባ ኩማ ካቢኔን ውሳኔ ተከትሎ ስለመሆኑ፣ ወይም የምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ካቢኔ አዲስ ውሳኔ አስተላልፎ ስለመሆኑ፣ ማብራሪያ እንዲሰጡ የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ዳምጠውን፣ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ተረፈንም ሆነ የኤጀንሲው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ ሌሊሳን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡