Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየብሔር ማንነት ከሌሎች ማንነቶች በተለየ የግጭቶች መንስዔና ሥጋት እንደሆነ ተገለጸ

የብሔር ማንነት ከሌሎች ማንነቶች በተለየ የግጭቶች መንስዔና ሥጋት እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ሥጋት ከሆኑትና የአገሪቱን አንድነት እየተፈታተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ የብሔር ማንነት እንደሆነ ተገለጸ፡፡ ይኼን ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ‹‹አዲስ ወግ›› በተሰኘው ተከታታይነት ያለው የውይይት መድረክ ‹‹ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ዓርብ ሰኔ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ንጉሡ፣ ‹‹ለአገራችን ሥጋት ከሆኑትና አንድነታችን ሊፈታተኑ ከሚችሉ ነገሮች አንዱ ምንድነው ብለን ብንነሳ በየቦታው ዜጎችን የሚያፈናቅል፣ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊን የሚያፈናቅልበት፣ ግጭቶች የሚፈጠሩበት፣ አልፎ ተርፎም ሞትም ጭምር የሚከሰትበት ዋነኛ አጀንዳ ምንድነው ብንል ከማንነቶች ሁሉ የብሔር ማንነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የሚያመንና የሚበላን ቦታ በመሆኑና የሚበላን ቦታ ላይ ብናክክ ልንግባባ እንችለለን፤›› ተብሎ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጊያ መድረክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በውይይት መድረኩ ላይ የመነሻ ሐሳብ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዳይሬክተርና የሥነ አዕምሮ ባለሙያና ሐኪም ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ፣ የፌዴራሊዝምና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) እና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሙሳ አደም ቀርቧል፡፡ የማንነት አፈጣጠር፣ ታሪካዊ የማንነት ዓምዶችና እንደ አገር የታለፈባቸው አዎንታዊ ጉዳዮች አለመጉላላታቸውን ያንፀባረቁ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡

የግልና የጥቅል የሚባሉ ማንነቶች መኖራቸውን በንግግራቸው የጠቀሱት ዶ/ር ዳዊት፣ አንድን ሰው ከሌሎች ጋር የሚያመሳስሉት የጋራ የሆኑ ማንነቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህ ማንነቶች ከውልደት ጀምሮ ስለሚታወቅ ስሜት በተጨማሪ፣ በቆይታ ከውጭው ዓለም ወደ ውስጥ ማስገባት ሲጀመር ‹‹የእኔ›› ያልሆነ ስሜት እየፈጠሩ እንደሚሄዱ ተናግረዋል፡፡

የሰዎች ማንነት በሚፈጥሩት ግንኙነት እንደሚሠራም በማውሳት የቦታና የጊዜ፣ የአካባቢ ብሎም የአጋጣሚዎች ቁርኝት የዚህ ግንኙነት አፈጣጠር መንገዶች ናቸው ሲሉም አውስተዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ማንነት የሚወረሰው በደም ነው የሚለው አመለካከት በየትኛውም ጥናት ያልተረጋገጠና ልክ ያልሆነ ነው፤›› በማለት አስምረውበታል፡፡ ሆኖም በተቃራኒው ያለው ማንነት ፈጠራ ነው እንጂ የለም የሚለው ጽንፍ ስህተት እንደሆነና ከተፈጠረ ወዲያ ማንነት እንዳለና እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡

በእኔና ሌላው በሚለው የማንነት አመለካከት ውስጥ ስድስት የማንነት ደረጃዎች መኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር ዳዊት እነርሱም አጥፊ ማንነት (እኔ ከሁሉ እበልጣለሁ፣ ሌላውን አጥፍቼ የእኔ ዓይነት አደርጋለሁ የሚለው)፣ አላዋቂ ማንነት (እኔ ስለማውቅ ሌሎችን የተሻሉ እንዲሆኑ ላድርግ የሚለው)፣ የታወረ ማንነት (ልዩነት በሰው መካከል የለም የሚለው አመለካከት)፣ ግድ የለሽ ማንነት (ሁሉም እንደፈቀደ ይሁን የሚለው)፣ መሠረታዊ ማንነት (ልዩነት አለ፣ የሌላውንም ፍላጎት ለማወቅና ለመረዳት እንፈልጋለን) የሚለውና ከፍ ያለ ማንነት (ልዩነትን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ሆን ብለው ለማወቅና ሌሎች አዳዲስ ማንነቶችን ለማወቅ መጣር) ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የውይይቱ መሪ የነበሩት ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ከዚህ በመንደርደር የማንነት ጥያቄ ከፖለቲካዊ ድንበር መውጣት አለበት በማለት፣ መጀመርያውኑ ማንነት ምንድነው ወደሚለው ሄዶ መነጋገርና መወያየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ብሔርተኝነትን በአጀንዳነት አንስቶ ለመወያየት ምክንያት የሆነው በዙሪያው ላሉ ሥጋቶች ምክንያት መሆኑን የተናገሩት አብዲ (ዶ/ር) ደግሞ፣ የኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ ችግሮች ከአገር ግንባታ ጋር ተያይዘው እንደሚታዩ በማመላከት፣ የኢትዮጵያ ችግር ግን የብሔርና የብሔርተኝነት ነው ማለት ልክ አይደለም ብለዋል፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ የብሔርተኝነት ስሜት ከፋፋይ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ ትልቁ ብሔራዊ/አገራዊ ማንነት እኔን አላካተተኝም፣ አላቀፈኝም የሚል ነው በማለት፣ ያኔም የፉክክሩ ደረጃ ከፍ እንደሚልና ይኼም በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ደጋፊዎች በመኖራቸው እንደሚጦዝ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ወገኖች ላሉት የሚስማማ ሥርዓት መገንባት የአገር ግንባታ ብልኃት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ በፖለቲካ ለውጥ ላይ እንደሆነችም ያስታወሱት አብዲ (ዶ/ር)፣ ለውጥ ሒደት በመሆኑና ብዙ ሐሳቦችን ይዞ ስለሚመጣ፣ በዚህ ሒደት የሚንፀባረቁ ሐሳቦች መለጠጥ እንደሌለባቸው አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ‹‹ሁሉም ብሔሮች እኩል ናቸው ነገር ግን አንዳንድ ብሔሮች የበለጠ እኩል ናቸው›› የሚል አመለካከት እንዳለ ያመላከቱት አቶ ሙሳ በበኩላቸው፣ ከ‹ነገር ግን› በፊትና በኋላ ባሉ መካከል ክፍተት አለ ሲሉም አመላክተዋል፡፡

‹‹የብሔር ማንነት እንደ አንድ የሽንኩርት ልጣጭ አንዱ የተደራራቢ ማንነታችን መገለጫ ነው፤›› ያሉት አቶ ሙሳ፣ ‹‹ያለን ምናባዊ ትርክት ግን አመለካከታችንን አዛብቶታል፤›› በማለት ተችተዋል፡፡

‹‹የማንነት እንቅፋቶች፣ በተለይም የብሔር ማንነት እንቅፋትነት ተመዝዞ በገበያ ተሸጧል፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ተመልሶ እንደሚነጥቀን አልገባንም፤›› ሲሉም የተሠራውን ስህተት ነቅሰዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ዕውቁ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው ብሔርተኝነት የመንግሥት መዋቅር ሆኖ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና አግኝቶ ሳለ ብሔርተኛ የሆነው መንግሥት ብሔርተኝነት አስቸገረኝ ብሎ እንዲህ ዓይነት የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ምንን ያመለክታል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ንጉሡ በበኩላቸው እስካሁን በብሔርና በአገራዊ ማንነት መካከል ሚዛን የጠበቀ ሥራ ባለመከናወኑና ሕዝቦችን አንድ ላይ ሊያስተሳስር በሚችል ሳይሆን በሚበጥስ መንገድ በመሠራቱ፣ አሁን አገሪቱ የደረሰችበት ደረጃ ላይ መድረሷን ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት  ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን በሐሳብ አለመሟገታችን ነው፤›› ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

‹‹መጀመርያ ለራሳችን ዋጋ እንሰጠዋለን ወይ? ሃይማኖታችንን እናከብራለን ወይ?›› ሲሉ በመጠየቅ፣ የማክበር ምልክት የሆነው ለታላቅ ወንበር መልቀቅ እየቀረ፣ ለመምህር ተነስቶ እጅ የሚነሳ ተማሪ አለመኖሩ ከታች ጀምሮ ያለ ችግር ማመለከቻ ነው በማለት፣ በትምህርት ቤቶች ላይ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በዘለለም በ1960ዎቹ የነበረውና የብሔር ጥያቄ ነው ሲባል የቆየው፣ ‹‹ዕውን የብሔር ነው የመደብ ጥያቄ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ኃላፊ ጌታቸው ካሳ (ዶ/ር)፣ ‹‹ትንንሽ ነገር ላይ እያተኮርንና አኅጉራዊ አስተሳሰብ መገንባት ሲገባን ችላ ብለን የቅኝ ገዥዎችን አጀንዳ በማቀንቀናችን ዛሬ ላይ ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡

ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በስብሰባው የተገኙ አንድ ተናጋሪ በበኩላቸው፣ በርካታ የማንነት ጥያቄዎች ለምክር ቤቱ እንደሚቀርቡ በመጠቆም፣ ከእነዚህ ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ የሀብት ጥያቄ ስላለ ዋነኛ ጥያቄው የማንነት ነው ወይስ የኢኮኖሚ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ሙኒክ አብዱል መናን የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው፣ ‹‹ጉዳዮችን ከመሠረታዊ ትርጉማቸው አንስተን ማየት አለብን፤›› በማለት፣ ‹‹ትልቅ ጉዳይ ለሰጠናቸው ጉዳዮች መጠየቅ አለብን፤› ብለዋል፡፡ ‹‹አዳዲስ ነገሮችን መማር ብቻ ሳይሆን፣ የተማርነውን ስህተት ዳግም አለመማር ይጠበቅብናል፤›› ሲሉም አስምረዋል፡፡

አሁን ሄዶ ሄዶ የተለየ ብሔር ያለውን ማጥቃት ላይ በመደረሱ፣ ይኼንን መቀየር የሚቻለው ሁሉም ዕውቅና አግኝተው ኢትዮጵያዊ ማንነትን ደግሞ በማይጋጭ ሁኔታ መገንባት ሲቻል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...