Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርእንደ አህያ ጥላ በማይረባው ስንጣላ አገር እንዳናጣ!

እንደ አህያ ጥላ በማይረባው ስንጣላ አገር እንዳናጣ!

ቀን:

በድሮ ዘመን ሁለት ጎረቤታሞች አብረው ይኖሩ ነበር። አንደኛው የእህል ነጋዴ ሲሆን፣ ሌላኛው ጎረቤት ደግሞ ገበሬ ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን እነዚህ ሁለት ጎረቤታሞች ገበያ ይሄዳሉ። ነጋዴው እህል ሊሸጥ አህያውን ጭኖ፣ ገበሬው ደግሞ ለዘር የሚሆን እህል ሊሸምት። ረዥም በረሃና አስቸጋሪ መንገድ ከተጓዙ በኋላ ነጋዴው እህሉን ሸጦ፣ ገበሬውም ለዘር የሚሆነውን እህል ገዝቶ ወደ ቤት ሲመለሱ ገበሬው የገዛውን ዘር ለመጫን የነጋዴውን አህያ ተከራይቶ ጉዞ ቀጠሉ።

መንገዱ በረሃማ ስለነበር ተጓዦች ፀሐይ ይበረታባቸውና ለማረፍ የሚያደርጉት አንድ ልማድ ነበራቸው። ይኼውም በአህያው ጥላ ሥር ተቀምጠው ከፀሐይ መጠለል ነበር። ይሁን እንጂ ጎረቤታማቾቹ ሁለት ስለሆኑና የአህያው ጥላም ሁለቱን በአንድ ጊዜ ማስጠለል ስላልቻለ በመካከላቸው አለመግባባት ይነሳል። ነጋዴው አህያው የእኔ ስለሆነ ጥላውም የእኔ ነው፡፡ ስለዚህ የጥላው ተጠቃሚ እኔ ነኝ ይላል፡፡ የገበሬው መከራከሪያ ደግሞ አህያውን ስለተከራየሁት ጥላውም የእኔ ነው የሚል ሐሳብ ነበር። የቃላት ክርክሩ ወደ ፀብ ይቀየረና መደባደብ ይጀምራሉ፡፡

 ከብዙ ድብድብ በኋላ ሰው ደርሶ ፀቡን ካበረደ በኋላ ለመሆኑ ምን ነክቷችሁ ነው እናንተን የመሰለ ወዳጅ እንዲህ የምትደባደቡት ተብለው ሲጠየቁ፣ በአህያ ጥላ ይገባኛል ሰበብ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ይናገራሉ። ገላጋዮቹም ግራ ተጋብተው በየትኛው አህያ ጥላ ብለው ሲጠይቁ፣ ጎረቤታማቾቹ አህያውን ለማሳየት ወዳቆሙበት ቢመለከቱ አህያው ጭነቱን ይዞ ጠፍቷል፡፡ ተፈልጎም ሊገኝ አልተቻለም። እንግዲህ ለጥላ መጣላት ነጋዴውን አህያ ሲያሳጣው ገበሬውን ደግሞ ያለ ዘር አስቀረው።

ልብ አድርጉ፡፡ የነጋዴው ህልውና በአህያው ላይ የገበሬው ህልውናም በሚዘራው ዘር ላይ ነው የተመሠረተ ነው። ኢትዮጵያውያን ያለንበትን ወቅት ይህ ተረት በሚገባ ይገልጸዋል። አገር ሊያሳጣን በሚችል ሁኔታ ውስጥ ሆነን የምንከራከረው ግን የአህያውን ጥላ በሚመስል ጉዳይ ላይ ነው። ወቅቱ የሚጠይቀው መንግሥትም ሆነ ሕዝብ አገርን በሚያድን አጀንዳ ላይ ማተኮራቸው ላይ ሆኖ ሳለ፣ በተግባር የሚታየው ግን የአህያው ጥላ የማነው በሚል አክሳሪ አምባጓሮ ላይ ነው።

ጎረቤታሞቹን ያጣላቸው የአህያው ጥላ ከአህያውና ከተጫነው ጭነት በላይ ገዝፎ ስለታያቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እኔነት ጫፍ የረገጠ ብሔርተኝነት፣ መንደርተኝነት፣ የእኔ ለውጥ ነው ባይነት ፣ ግላዊ ፍላጎት፣ ልወደድና ተረሳሁ ባይነት ከአገር አጀንዳ በላይ እየጮሁ ያስቸገሩ የአህያ ጥላዎች ናቸው። ዛሬ በሶሻል ሚዲያው ትኩረት እያገኙ ያሉት ጩኸቶች እነዚህ ናቸው። ካስተዋልን ግን እነዚህ ጩኸቶች ሊደመጡ የሚችሉት ኢትዮጵያ ስትኖር ነው። አህያው እስካለ ድረስ ጥላውም እንደሚኖረው ሁሉ አገርም  ስትኖር ነው እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አንገብጋቢነታቸው መጠን በአግባቡ መልስ የሚያገኙት፡፡

 ኢትዮጵያውያን በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉን ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ከአገር በላይ የገዘፈ አጀንዳ አለን ብዬ አላምንም። የአህያ ጥላ በሚመስል አጀንዳ ላይ መጣላት አገርን ያሳጣል፡፡ የህልውና አደጋ ነው፡፡ አክሳሪ ነው፡፡ መጨረሻውም ተሸናፊነትና እርስ በርስ መጠፋፋት ነው። በዚህ ውስጥ ከሳሪ እንጂ አትራፊ አይኖርም። ስለዚህ ምን እናድርግ? ብንል እነዚህን እናድርግ እላለሁ፡፡

መንግሥት አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ቁርጠኝነቱን ለማሳየት፣ ሕግ ማስከበር ላይ፣ ፍትሐዊነትና የዜጎችን ሰላም ማስከበር ላይ ፈጣን ዕርምጃ ይውሰድ። ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አማካይነት የሚፈጸሙ ተግባራትን በመከታተል አፋጣኝ ማስተካከያ ያድርግ። ሕዝቡም በዚህ ሒደት ውስጥ ተሳታፊ ይሁን።

የአገርን ገጽታ በሚያበላሽና የዜጎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሚያውኩ የዘረፋ ወንጀሎች ላይ መንግሥት የማያዳግም ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ። የለውጡ ባለቤት ማነው ከሚል ጠባብ አጀንዳ ወጥተን ለውጡ እንዴት ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደሚጠቅም አቅጣጫ እንምራው በሚለው ላይ እናተኩር። በየሚዲያ የሚካዱት የውይይት መድረኮች በአክቲቪስቶችና በፖለቲከኞች ከሚጣበቡ ይልቅ የውይይቱ ርዕስ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ቢሳተፉበት።

የመንግሥትና የግል ጋዜጠኞች የማኅበረሰቡን ችግሮች ከአክቲቪስቶች ሳይሆን፣ ታች ወርደው ከማኅበረሰቡ መሰብሰብና ወደ መንግሥት አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት ማድረግ ቢችሉ ለለውጥ ይበጃል።

አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ነጋዴዎች ከሚሰጡን ጥቃቅን አጀንዳዎች ወጥተን የጋራ ህልውና መሠረት በሆኑ ትላልቅ አጀንዳዎች ላይ እናተኩር። የራስንና የመንደርን ፍላጎት ለማሳካት አገርን ከሚጎዱ ድርጊቶች እንቆጠብ።

(ሮቤል ዋቢ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...