Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት እሑድ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ነበር፡፡ የሄድኩትም አንድ የማውቃቸው ሰው የተጣሉ ጓደኛሞችን ለማስታረቅ ስለጠሩኝ ነበር፡፡ በገንዘብ ምክንያት የተጣሉ ጓደኛሞችን አግባብተን ካስታረቅን በኋላ ወደሚቀጥለው ጉዳዬ ላመራ ስል ድንገት ዓይኖቼ ከአንድ ሐውልት ጋር ተገጣጠሙ፡፡ በሐውልቱ ላይ የሚታየው ጉልህ ፎቶግራፍ ከዚህ በፊት የማውቃቸውን አንድ ሰው አስታወሰኝ፡፡ ፎቶግራፉ ምንም እንኳን በጎልማሳነት ዘመን የተነሳ ቢሆንም፣ በስተርጅና ዘመናቸው የማውቃቸው ሰው እንደሆኑ ግን አልተጠራጠርኩም፡፡ በዚህም ምክንያት ፍጥነቴን ጨምሬ ወደ ሐውልቱ ተጠጋሁ፡፡

በእርግጥም የማውቃቸው ሰው ናቸው፡፡ ስማቸውን አነበብኩት፡፡ ወይ ጉድ? መቼ ይሆን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት? አዎን ከ1918 – 2010 ዓ.ም. የሚል ተጽፏል፡፡ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም. ማረፋቸውን አወቅኩኝ፡፡ እኔ ደግሞ መሞታቸውን አልሰማሁም፡፡ ሐውልቱን ደገፍ ብዬ ስለእሳቸው ማሰብ ጀመርኩ፡፡ መጀመርያ የተዋወቅኳቸው በ2005 ዓ.ም. ነበር፡፡ የተገናኘነውም በአጋጣሚ ለቅሶ ላይ ነበር፡፡ የሟች ቤተሰቦችን ሲያፅናኑና የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ ሲያጫውቱን ለዛቸው ደስ ይል ነበር፡፡ ጨዋታ ከጀመሩ አይጠገቡም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት እያገኘሁዋቸው ሐሳብ ለሐሳብ እንለዋወጥ ነበር፡፡

መጨረሻ ያገኘኋቸው ግን ከአንድ ዓመት በፊት አራት ኪሎ ነው፡፡ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ፊት ለፊት ከሚገኙት ካፌዎች አንደኛው በራፍ ላይ ሆኜ ጋዜጣ እያነበብኩ ማኪያቶ ሳጣጥም፣ እኚህ አዛውንት የሕንፃውን ምሰሶ ደገፍ ብለው አየኋቸው፡፡ ትኩር ብዬ ሳያቸው ላብ በላብ ሆነውና ድክም ብሏቸው ምሰሶውን የሙጥኝ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ደንገጥ ብዬ ተነሳሁና ወደሳቸው ቀርቤ ሰላምታ ካቀረብኩላቸው በኋላ ደገፍ በማድረግ ተቀምጬበት የነበረው ሥፍራ አምጥቼ አስቀመጥኳቸው፡፡ ባርኔጣቸውን አውልቀው ላባቸውን በመሃረባቸው ከጠራረጉ በኋላ በረዥሙ ተነፈሱ፡፡ የፀሐዩ ንዳድና መንገድ እንዳደከማቸው ነገሩኝ፡፡

እኔም፣ ‹‹ምነው ምሰሶውን ከሚደገፉ መቀመጫ ላይ አረፍ ብለው ሻይ ቡና አይሉም ነበር ወይ?›› በማለት እንደ ዘበት አስተያየቴን ጣል አደረግኩ፡፡ በዚህ መሀል አስተናጋጇ መጥታ ትዕዛዝ ስትጠይቃቸው አንዴ እኔን ሌላ ጊዜ እሷን አዩ፡፡ ነገሩ ገብቶኝ ለስላሳ፣ ቡና፣ ማኪያቶ ወይም ምን ይፈልጉ እንደሆነ ምርጫ አቀረብኩላቸው፡፡ ወፍራም ቡና እንዲመጣላቸው አዘው፣ ‹‹ሰማህ?›› አሉኝ፡፡ ጠጋ ብዬ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ምሰሶውን እኮ የተደገፍኩት መቀመጡን ጠልቼ አይደለም፤›› አሉኝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹የጡረታ አበል ሆድ መሙላት እያቃታት ቡና ሻይ ማለት እንዴት ይቻላል?›› ብለው ሲተክዙ ገባኝ፡፡ እኚህ ከወጣትነታቸው ጀምረው ጣሊያንን የተዋጉ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ኮሪያና ኮንጎ የዘመተው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል ባልደረባ የሚያገኙት ጡረታ ለምግብም አይበቃም፡፡ የእሳቸው ትካዜ እኔ ላይ ተጋብቶ ለረዥም ጊዜ ፀጥ ተባብለን ቆየን፡፡

እኚህ ጀግና ሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ አገራችን አዛውንቶቿን አትጦርም፤›› አሉኝ፡፡ ብዙዎቹ እሳቸውን መሰል አዛውንቶች ከቤታቸው ወጥተው እግራቸውን ለማፍታታትና ለመንቀሳቀስ እንደማይመቻቸው፣ ብዙዎቹ የሕዝብ መናፈሻዎች መዘጋታቸውን፣ ከተማዋ ሕንፃ በሕንፃና መንገድ በመንገድ ስትሆን እንኳ ተዘዋውሮ ለመመልከት እንደማይመቻቸው፣ በየቦታው አረፍ የሚባልበት አለመኖሩን፣ ካፌ ጎራ ለማለት አቅም መጥፋቱን፣ አዛውንቶች መንቀሳቀስ ሲገባቸው በዚህ ችግር ምክንያት ተሳስረው መቀመጣቸውን በሐዘን አወጉኝ፡፡ አዎን የኑሮ ውድነቱ እንደ ወላፈን በሚጋረፍበት በዚህ ዘመን ስንቶች ከረሃብ ጋር እንደሚተናነቁ ወለል ብሎ ታየኝ፡፡ ይኼንን ሁሉ ስናወራ የራሳቸውን ችግር ሳይሆን የብዙዎችን አዛውንቶች ነበር ማዕከላዊ ነጥብ አድርገው የነገሩኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር ከእኝህ አዛውንት ጋር የተለያየነው፡፡

ሐውልቱን ተደግፌ በመጠኑ ስለሳቸው የተጻፈውን እያነበብኩ ሳለ አንዲት ወጣት ሴት አጠገቤ መጥታ ቆመች፡፡ ዞር ብዬ ሳያት፣ ‹‹ታውቀዋለህ እንዴ?›› አለችኝ፡፡ ፊቴን በሐዘን አጨማድጄ፣ ‹‹አዎን፤›› አልኳት፡፡ ወጣቷ፣ ‹‹አያቴ ነው፡፡ ኩሩ ሰው ነበር፡፡ በኮሪያ ጦርነት ጊዜ የጀግንነት ሜዳሊያ ከአሜሪካ ጄኔራልና ከጃንሆይ እጅ ተቀብሏል፡፡ እሱ ግን ይህ እንዲወራለት አይፈልግም ነበር፡፡ የፈለገ ቢከፋው ዝም ይላል እንጂ አገሬ በደለችኝ አይልም ነበር፡፡ ይልቁንም አገራችን አልፎላት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ትልቅ ደረጃ በደረሱ እያለ ነበር የሚናገረው…›› እያለች ስትነግረኝ ዓይኖቼ በዕንባ ተሞሉ፡፡ በጀግንነት አገራቸውን ያገለገሉ ሰው በስተርጅና ዘመናቸው በችግር ውስጥ ሆነው ቢያልፉም በኩራት መኖራቸው አስደሰተኝ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ችግሮችን ተጋፍጠን አገራችንን ሳናማርር የምንኖር? ስንቶቻችን እንሆን ከአገር በፊት ራሳችንን እያስቀደምን በኃፍረት እንደተሸማቀቅን የምናልፍ?

ልጅቷ እንደነገረችኝ ከሆነ ሐውልቱን ያሠሩላቸው የሚያውቋቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሐውልቱ ላይ በዚህ ጊዜ ተወልደው በዚህ ጊዜ ሞቱ ከሚባለው በስተቀር ምንም አልተጻፈም፡፡ ስለጀግንነታቸው ለምን እንዳልተጻፈ ጠየቅኳት፡፡ ልጅቷ፣ ‹‹አያቴ ሁሌም የሚያሳስበኝ በፍፁም ምንም ዓይነት ነገር እንዲህ አደረገ ተብሎ እንዳይጻፍ ወይም እንዳይነገር ነው፡፡ እሱ ለአገሩ በፍፁም ፈቃዱ ያከናወነውን ተግባር ዝና ፍለጋ እንደማይጠቀምበት አስጠንቅቆኛል፤›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ ርካሽ ተወዳጅነትና ዝና ፍለጋ ስንትና ስንት ኃጢያት በሚያሠራበት በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት የተባረኩ ሰዎችን ማጣት አሳዘነኝ፡፡ እዚህ ግባ የማይባል የጡረታ አበል እየሰጠችና የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን እየዘጋች አዛውንቶቿን የዘነጋች አገር እንዲህ ዓይነት ኩሩ ሰዎችን እያጣች፣ በዝርፊያና በክፋት የደለቡ ከንቱዎችን ስትንከባከብ ማን ይሆን ማፈር ያለበት? በቅርቡ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ደቡብ ኮሪያ ሄዶ ነበር፡፡ አውሮፕላኑ አርፎ የኮሪያን ምድር ሲረግጥ ኮሪያውያኑ ያደረጉለት አቀባበል አስገራሚ እንደነበር ሲነግረኝ ገረመኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የመጣ መሆኑን በማወቃቸው የዚያች ባለውለታ አገር ሰው ብለው ነበር ለእሱ በተለይ ደማቅ አቀባበል ያደረጉለት፡፡ ቃኘው ሻለቃ በመባል ስለሚታወቀው ዝነኛ ሰላም አስከባሪ ጦር ጀግንነት የነገሩትን ታሪክ ሰምቶት ስለማያውቅ እንደ ጉድ ነበር የተገረመው፡፡ በኮሪያ ምድር ሐውልት የቆመላቸው እነዚያ ብርቅዬ ጀግኖች በገዛ አገራቸው እየተራቡ ማለፋቸውን ለሚሰማ ሰው ያሰቅቃል፡፡ አገር የምታምሱ አክቲቪስት ተብዬዎች እስቲ ሌላውን የጥፋት እንቶ ፈንቶ ተውና ታሪክን እየዘከራችሁ ታላላቅ ሰዎች እንዲከበሩ ሥሩ፡፡ እነሱ ያቆሙዋትን አገር ለመጣል ከምትንሰፈሰፉ መጀመርያ የሚያስከብር ተግባር ፈጽሙ፡፡

  (ቶማስ ዘርጋው፣ ከጃልሜዳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...