Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበረቂቅ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ላይ የቀረበ ወፍ በረራዊ ቅኝት

በረቂቅ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ላይ የቀረበ ወፍ በረራዊ ቅኝት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

አሁን በሥራ ላይ ያለው የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ይሻሻላል ተብሎ መነገር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ብዙ ክርክሮችም ተደርገዋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንም የተወሰኑ ድንጋጌዎችን በሚመለከት የተለየ አቋም እንዳለው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ረቂቅ አዋጁን ለሕዝብ ይፋ ማድረግም ያልተፈለገም ይመስል ነበር፡፡ ረቂቁን ለማግኘት ጥያቄ ሲቀርብ ለማጋራት እንደማይፈቀድ መግለጽ የተለመደ ነበር፡፡ አሁን ላይ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሷል፡፡ ሕዝባዊ ውይይትም እየተደረገበት ይገኛል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓብይ ትኩረትም ይህንን ረቂቅ አዋጅ በሚመለከት በተደረጉት ማሻሻዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ በረቂቅ ደረጃ ባለው አዋጅ ላይ ስለሆነ በየዕለቱ ለውጥ ሊደረግበት እንደሚችልና የመጨረሻው ሰነድ ጋር ሊለያይ እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ከተሻሻሉት ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ

በክልል የሚቋቋሙ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሚለውን ‹‹አግባብ ያለው ባለሥልጣን›› በማለት ክልሎች በፈለጉት ስያሜ እንዲያቋቁሙት ነፃ አድርጓቸዋል፡፡ የሥራ መሪን በሚመለከት ከቀድሞው ትርጓሜ ላይ ‹‹የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ›› የሚወሰድን ሁሉ የሥራ መሪ ያደርግ ስለነበር ይኼም ወጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹የግል አገልግሎት ቅጥር›› የሚለው የተድበሰበሰ ትርጉም ላይ ማብራሪያ በመስጠት በትርፍ ላይ ያልተመሠረተ ለአሠሪውና ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚውል የቤት ሥራ የሚያከናውን መሆኑን ብያኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ‹‹ወሲባዊ ትንኮሳ›› እና ‹‹ወሲባዊ ጥቃት›› ለሚሉት ሐረጎች ትርጉም ተቀምጦላቸዋል፡፡ ያለ ማስጠንቀቂያ ሥራ ለማቋረጥ ምክንያት እንደሚሆኑ፣ እንዲሁም የሥራ ስንብት ክፍያና ካሳም እንደሚያስገኙ በረቂቁ አንቀጽ 32፣ 39 እና 41 ላይ ተገልጸው እናገኛቸዋለን፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠርን አለመግባባት ለመፍታት ቀድመው ከሚታወቁት አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ለየት ያለና ከኅብረት ድርድር በተጨማሪ ‹‹ማኅበራዊ ምክክር›› (Social Dialogue) የሚባል ሥርዓት ተካቷል፡፡ ለውጭ አገር የሠራተኛ ሥምሪት ብቻ የተለየ አዋጅ ሲወጣ፣ በ2001 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 632/2001 ስለተሻረ በአገር ውስጥ የሚከናወነው የግል ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ጨረቃ ላይ ቀርቶ ነበር፡፡ ይህንን ዘርፍ የሚገዛ ሕግ ስላልነበር በረቂቅ አዋጁ ላይ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡ በመቀጠልም፣ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ለማውጣት የሚያስፈልጋቸውን የሙያ ብቃትና ሌሎች ሁኔታዎች የሚገልጹ አንቀጾች ከ172 ጀምሮ እስከ 182 ድረስ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተሰባጥረው ተካተዋል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ክፍል ሁለት፣ ማለትም ከአንቀጽ 4 እስከ 52 ድረስ ባሉት ላይ አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅና ማሻሻያው ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች አሉ፡፡ በእዚህ ክፍል ሥር ካሉት ማሻሻያዎች በፍጥነት ወደ ዓይን የሚገባው የሙከራ ጊዜ ላይ የተደረገው ለውጥ ነው፡፡ በረቂቁ ላይ ከ45 ቀናት ሊበልጥ እንደማይችል ተደንግጎ የነበረው አሁን ወደ 60 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ 45 ቀናት የሚለው ተከታታይ ቀናትን እንጂ የሥራ አልነበሩም፡፡ ረቂቁ ግን አንድ ሠራተኛ ለሥራው ተስማሚ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሙከራ ወይም የፈተና ጊዜውን ወደ 60 የሥራ ቀናት አቃንቶታል፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ሕጉ ሦስት ወራት ሆኖ፣ እስከ ስድስት ወራት ድረስ ሊራዘም እንደሚችል ይታወቃል፡፡

ሌሎቹ ማሻሻያዎች ከሠራተኛና ከአሠሪ መብትና ግዴታዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ አንቀጽ 12 ላይ የተዘረዘሩት የአሠሪው ግዴታዎች ላይ ሠራተኛው አባል ለሆነበት የሠራተኛ ማኅበር የሚከፍለውን ወርኃዊ መዋጮ አሠሪው ከደመወዙ እየቀነሰ ለማኅበሩ ባንክ ገቢ እንዲያደርግ፣ የሥራ ደንቦችን ለሠራተኞች የማስተዋወቅ፣ እንዲሁም አንቀጽ 14 (1) ላይ ደግሞ አሠሪው እንዳይፈጽም የከለከላቸውን በሚመለከት አሠሪው የሚለው የሥራ መሪውንም ጨምሯል፡፡ ለሠራተኛም ጭምር የተከለከሉት ላይ የተወሰኑ ጭማሬዎች ተደርጓል፡፡

የሥራ ዕገዳ ጊዜ ሲያበቃ የሚኖረውን ውጤት በሚመለከት አንቀጽ 22 መጠነኛ ማብራሪያ የተደረገ ሲሆን፣ ሠራተኛን ያለማስጠንቀቂያ ለማባረር ምክንያት ከነበሩት ውስጥ አንቀጽ 27 (1) (ሀ እና ለ) ‹‹ያለበቂ ምክንያት በመደጋገም ዘግይቶ ወደ ሥራ ቦታ መምጣት›› እንዲሁም ‹‹በተከታታይ ለአምስት ቀናት ከሥራ ከቀረ›› የሚለው ‹‹ያለበቂ ምክንያት›› የሚለው በራሱ ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹በመደጋገም›› የሚለው ለሁለት ቀናት ለሦስት ወይስ ለስንት እንዲሁም በተከታታይ ይሁን ወይም አይሁን አሻሚ ስለሆነ፣ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚለውም በአራተኛው ቀን እየመጡ ከእንደገና እየቀሩ ብዙ ቀናት ከሥራ መቅረት ስለሚኖር፣ በኅብረት ስምምነቱ ወይም በሥራ ደንቡ ውስጥ ማርፈድን በሚመለከት የሚገለጹትን  መሠረት አድርጎ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወራት ውስጥ ለስምንት ጊዜ ካረፈደና መቅረትን በሚመለከት በተከታታይ ቢሆንም ባይሆንም በስድስት ወራት ውስጥ አምስት ቀናት ከቀረ ያለ ማስጠንቀቂያ ለማባረር እንዲቻል ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡

ሌላው በዚህ ክፍል ውስጥ ማሻሻያ የቀረበው አንቀጽ 28 ላይ የሠራተኛው ሥራን የማከናወን ችሎታ ቀንሶ መገኘትን የሚመለከተው ሲሆን፣ አሠሪው በዘፈቀደ ሠራተኛን እንዳያባርር የመሥራት ችሎታ መቀነስ ምንነት በኅብረት ስምምነት መገለጽ እንዳለበት ካልሆነ ግን የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት መሠረት መሆን እንዳለበት በመሥፈርትነት ቀርቧል፡፡ ሠራተኞች በሚቀነሱበት ጊዜ ጥበቃ የሚደረግላቸውን በሚመለከት የሥራ ቅጥር ከመደረጉ በፊትም ቢሆን የአካል ጉዳት ያጋጠመው አካል ጉዳተኛና ለነፍሰጡር ብቻ የነበረው ከወሊድ በኋላ እስከ አራተኛ ወር ድረስ አራስ ሴት መቀነስ እንደሌለባቸው ተጨምሯል፡፡ ቀሪ ማሻሻያዎቹ አንቀጽ 32፣ 39 እና 41 ላይ ሲሆን በዋናነት በወሲብ ትንኮሳ ወይም ጥቃት ምክንያት ያለማስጠንቀቂያ ሥራ ማቋረጥ እንደሚቻል በዚህም ሳቢያ የሚከፈለው የሥራ ስንብት እንደተጠበቀ ሆኖ የካሳ መጠኑ ወደ ሦስት ወር ደመወዝ ከፍ ብሏል፡፡

የረቂቅ አዋጁ ሦስተኛው ክፍል ማለትም ስለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚመለከቱት፣ በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ለሚተዳደሩ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን ስላልነበር የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚወስን ተመልክቷል፡፡ በክፍል አራት ሥር (ከአንቀጽ 61 እስከ 75) ባሉት ላይ አንድ ጉልህ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ይኼውም ከትርፍ ሰዓት ሥራና ክፍያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕግ አንድ ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት ሥራ በቀን ከሁለት ሰዓት ወደ አራት፣ በሳምንት ደግሞ 12 ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ሥራ ለማሠራት ምክንያት የሚሆኑትም ላይ አስቸኳይ የሥራ ትዕዛዝና አቅርቦት ሲኖርም ጭምር ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ዕረፍትን በሚመለከትም እንዲሁ ማሻሻያዎች አሉ፡፡ አንዱ የዓመት ዕረፍት ለመጀመርያው የቅጥር ዓመት 14 መሆኑ ቀርቶ ወደ 16 ከፍ ማለቱ ነው፡፡ ሁለተኛው በየዓመቱ አንድ ቀን የሚጨምረው ቀሪ ሆኖ ለሁለት ዓመት አገልግሎት አንድ ቀን እየጨመረ እንዲሰጥ በሚያደርግ መልኩ ተለውጧል፡፡ አንድ ሠራተኛ የዓመት ዕረፍት እየወሰደ ባለበት ጊዜ ቢታመም የዓመት ዕረፍቱ ተቋርጦ የሕክምና ፈቃድ ያገኝ ስለነበር ይኼንን በሚመለከት የሕክምና ፈቃድ ማምጣት እንዳለበት እንዲሁም አሠሪው የራሱ ክሊኒክ ካለው ከእዚሁ ክሊኒክ፣ ወይም አሠሪው ውል ካደረገበት የሕክምና ተቋም ካለ ከእዚያው እንዲያመጣ በሚያስችል መልኩ ተሻሽሏል፡፡ ዕረፍትን በሚመለከት ሌላው አዲስ ነገር የአንድ ሠራተኛ የትዳር ጓደኛ በምትወልድበት ጊዜ ሦስት ተከታታይ ቀናት የአባትነት ፈቃድ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ይኼ የረቂቁ ክፍል አምስት መሆኑ ነው፡፡

ስለወሊድ ፈቃድም አሁን ባለው ሕግ ቅድመ ወሊድ አንድ ወር፣ ድኅረ ወሊድ ሁለት ወር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ማሻሻያው ግን ቅድመ ወሊድ 30 የሥራ ቀናት፣ ድኅረ ወሊድ 60 የሥራ ቀናት እንዲሆን በረቂቁ ተካቷል፡፡ ከሴት ሠራተኞች ጋር በተያያዘ አንቀጽ 87 (2) ላይ እንደ መንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሰርቫንት) አንድ ወንድና አንዲት ሴት በቅጥር ጊዜ እኩል ነጥብ ካመጡ ቅድሚያ ለሴቷ እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ ተስተካክሏል፡፡

ከአንቀጽ 92 ጀምሮ እስከ 112 የሚዘልቁት፣ የረቂቅ አዋጁ ክፍል ሰባት ሥር፣ አንቀጽ 109 ብቻ ላይ ከዚህ በፊት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የተወሰነውን አካል ጉዳት ካሳ አከፋፈል የሕጉ አካል ሆኗል፡፡ ጉዳት ያጋጠመው ሠራተኛ ኢንሹራንስ የተገባለት ሆኖ የሚገኘው ካሳ ከአምስት ዓመት ደመወዝ ያነሰ ከሆነ፣ ልዩነቱን አሠሪው እንዲሸፍን ይገደዳል፡፡ ቀጣዩ የረቂቅ አዋጅ ክፍል ስለኅብረት ስምምነትና ድርድር የሚመለከት ሲሆን ከ113 እስከ 136 ያሉትን ይሸፍናል፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ለመመዝገብ ጥያቄ አቅርቦ በ15 ቀናት ምላሽ ካልተሰጠው እንደተመዘገበ እንደሚቆጠር የሚደነግገው መዝጋቢው አካል የምስክር ወረቀት ይሰጠዋል በሚል እንዲተካ ሆኗል፡፡ አዲስ ለሚመዘገብ የሠራተኛ ማኅበር የሚከፈለው ብር 350 የቴምብር ቀረጥ ቀሪ ተደርጓል፡፡

በክፍል ዘጠኝ ሥር ያሉት ደግሞ የሥራ ክርክር የመፍቻ ሥርዓት ናቸው፡፡ እስከ አንቀጽ 163 ድረስ ያሉት ማለት ነው፡፡ በእነዚህ አንቀጾች ላይ ሁለት ማሻሻያዎች አሉ፡፡ በነባሩ አዋጅ ላይ አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርዶች እየተወዛገቡ አንዴ በአወንታ ሌላ ጊዜ በአሉታ ውሳኔ ይሰጡባቸው የነበሩት የሠራተኛ ዕድገት፣ ዝውውርና ሥልጠናን የሚመለከቱ ሲሆን፣ በግልጽ ሥልጣን እንዳለው ዕውቅና በመስጠት አንቀጽ 148 (1/ሰ) ላይ ተደንግጓል፡፡ ሌላው ማሻሻያ ግን ቀደም ሲል በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ማሻሻያ (አዋጅ ቁጥር 466/1997) በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለመንግሥት የልማት ድርጀቶች ብቻ  የተለየ  የአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቋሚና ጊዜያዊ ቦርድ እንደሚቋቋም ተደንግጎ ስለነበር በአሁኑ ረቂቅ ለመንግሥት የልማት ድርጅት ገለመሌ ሳይል በወጥነት አዋጁን በአንቀጽ 192 (1) በማሻር የዚሁ አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በረቂቁ ክፍል 12 ውስጥ (ከአንቀጽ 171 እስከ 182) ሁለት ቁም ነገሮች ተጨምረዋል፡፡ አንዱ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን የሚመለከት ነው፡፡ ይኼን ቀደም ብለን ተመልክተነዋል፡፡ ሁለተኛው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመርያዎች በአንድ አንቀጽ ተጠቃለው መቀመጣቸው ነው፡፡ በየአንቀጹ ውስጥ ተሸጉጠው የነበሩትን አንድ ላይ በማድረግ ለሚኒስትሩ ሥራ አቅልሎለታል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ እንደ አዲስ የተካተተው ሌላው ጉዳይ የሥራ ሁኔታን የሚቆጣጠረው አካል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ብቻ መሆኑ ቀርቶ በግል የሚሠራ ሊሆን እንደሚችልና በምን ሁኔታ ፈቃድና ለአገልግሎት ብቁ የሚያደርጉትን ብቃት እንዲሁም የክፍያ ሁኔታ በሚመለከት አዲስ አሠራር አስተዋውቋል፡፡

የመጨረሻው ክፍል ደግሞ በዋናነት አዋጁ ድንጋጌዎች ሲጣሱ የሚያስከትሉት የወንጀል ቅጣት ወደ አስተዳደራዊ መቀየሩና ቅጣቱም በቁርጥ ከማስቀመጥ ይልቅ ቅጣቱን የሚወስነው አካል የነገሩን ሁኔታ ከግምት በማስገባት እንዲወስን ሥልጣን በሚሰጥ ሁኔታ መለወጡ ነው ከነባሩ የሚለየው፡፡

መሻሻል ሲኖርባቸው ያልተሻሻሉ

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ረቂቁ ላይ ያልተካተቱ ነባር ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹ ነባርነታቸውን አስጠብቀው ቀጥለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አምስት ምሳሌዎችን ብቻ እንጥቀስ፡፡ ይህ ማለት ችግሮቹ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ግን በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡

የመጀመርያው የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ አዋጅ በዋናነት ተፈጻሚ የሚሆነው የሥራ ውል ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ምልመላና መረጣን አያካትትም፡፡ በአዋጁ የሚተዳደሩ ድርጅቶች በፈለጉት መንገድ ሠራተኛ እንዲቀጥሩ በር የሚከፍት ብቻ ሳይሆን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አድልኦ መፈጸም (ብሔርን፣ ሃማኖትን፣ ጾታንና አካላዊ ሁኔታን ወዘተ.) መሠረት ያደረገ ልዩነት በምልመላና መረጣ ሒደት ወቅት ለመፈጸም የተመቻቸ ነው፡፡

ሌላው በነባሩ አዋጅም ሆነ በረቂቁ ላይ እንደተገለጸው ከሕጉ ተፈጻሚነት ወሰን ውጪ የተደረጉ የሥራ ግንኙነቶችን በሚመለከት አሁንም ረቂቁ እንደ በፊቱ ችግሮቹን እንደተሸከመ ነው፡፡ የረቂቁም ሆነ የነባሩ ሕግ አንቀጽ 3(2) ላይ ከተዘረዘሩት መካከል የተወሰኑት ትርጉማቸው እንደ ወትሮው እንደተድፈነፈነ ቀጥሏል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ካለው አዋጅ ጀምሮ ሕግ እንደሚወጣላቸው ተገልጾ (ለምሳሌ ስለግል አገልግሎት ቅጥር ሁኔታ) ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ አለመውጣቱ እየታወቀ አሁንም ይኼው ሥልጣን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጥቶታል፡፡ በተለይ የቤት ሠራተኞችን በሚመለከት አሁንም ቢሆን በዚህ መንገድ ማለፉ ችግሩን ማስቀጠል ይሆናል ውጤቱ፡፡ በእርግጥ የቤት ሠራተኞችና አሠሪዎቻቸው የሚኖራቸው የሥራ ግንኙነት ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ላይ ከተደነገጉት ወጣ ሊል እንደሚችል ይታወቃል፡፡

ሦስተኛው ምሳሌ የሥራ ውል የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ አንድ ሠራተኛ ከ30 ቀናት ለማይበልጥ ጊዜ ከታሰረ አሠሪው ያግደዋል፡፡ ማለትም ደመወዝ አይከፍለውም፡፡ ከ30 ቀናት በላይ ከሆነ ግን የሥራ ውሉ ይቋረጣል፡፡ ለፍርድ ቤቶች አስቸጋሪ እየሆነ የመጣስ ከ30 ቀናት በላይ አላግባብ ታስሮ የሚፈታ ሰው ወደ ሥራው የመመለስ ወይም አለመመለስ መብት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም፣ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ቦታ ለአምስት ቀናት በተከታታይም ይሁን በስድስት ወራት ውስጥ መቅረት የሥራ ውልን ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱ በቂ ሆኖ ነገር ግን ከአምስት ቀናት በላይ ቢቀርስ ውጤቱ ምን ይሆናል? አራተኛው ምሳሌ የሠራተኛ ዝውውርን የሚመለከት ነው፡፡ ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ የሥራ ቦታ፣ ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ መደብ እንዲሁም ከአንድ ድርጅት ወደ ሌላ እህት ድርጅት የሚደረጉ ዝውውሮች ጉዳይ በፍርድ ቤት ብዙ ክርክሮችን አስነስተዋል፡፡ አሠሪዎችም ሠራተኛን ለማባረር ሲፈልጉ ወደ ሌላ ቦታ፣ መደብ ወይም ድርጅት ማዘዋወርን እንደ አንድ ሥልት በማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡ አላባረርንም ለማለት አዘዋወርን ይላሉ፤ ነገሩ ግን ‹‹እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሰበር ውሳኔዎችም በርካታ ናቸው፡፡ የሰበር ችሎቱም ትርጓሜ ወደ አሠሪው ያዘነበለ፣ አሠሪው ያሻውን ማድረግ እንደሚችል ዕውቅና የሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ረቂቅ አዋጁም ይህንን እንዳለ አልፎታል፡፡

ምስተኛው ምሳሌ አካል ጉዳት መጠን የሚወሰንበትን አሠራር የሚመለከት ነው፡፡ የአካል ጉዳት መጠንንና የካሳ ክፍያን በሚመለከት ሥራ ላይ ያለው ሕግም የአካል ጉዳት መወሰኛ ሰንጠረዥ እንደሚወጣ ይደነግጋል፡፡ አስካሁን ድረስ ሳይወጣ በሕክምና ተቋማት በሚሰጥ ማስረጃ እየተወሰነ እንዲከፈል መደረጉ ይታወቃል፡፡ በአንድ በኩል የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ከነባራዊው ሁኔታ አንፃር ሲታይ ለረዥም ዘመናት ሳይሻሻል የሚቆይ ዓይነት ስላልሆነ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት የአካል ጉዳት መጠንን የሚወስኑ ሰንጠረዦች አብረው ከአዋጁ ጋር በአባሪነት ቢያያዙም ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ውክልና የተሰጠው ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ይህንን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ሕጉ በአግባቡ ተፈጻሚ አልሆነም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሌላ የመፍትሔ አቅጣጫ መከተል ተመራጭ ነበር፡፡

እንደ ማጠቃለያ

ረቂቅ አዋጁ ነባሩን አዋጅና ማሻሻያዎቹን በአንድነት ጠቅልሎ በአንድ ሰነድ ለመቀየር ታስቦ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ከዚህ የዘለለ፣ ሙሉ አዋጁን ሊያስቀይር የሚችል ለውጥ አለው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የተጨመሩና የተሻሻሉ አንቀጾች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ነገር ግን፣ የተወሰኑት በተለያየ ጊዜያት የተደረጉ ማሻሻያዎችን በአንድ አዋጅ የማካተት፣ የተወሰኑ አንቀጾች ደግሞ በሰበር ትርጓሜ የተሰጠባቸውን ወደ ድንጋጌ የመለወጥ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የተወሰኑ አንቀጾች ደግሞ አሻሚና አወዛጋቢ ትርጓሜ የነበራቸው ግልጽ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ እንደ አዲስ ተጨምረዋል፡፡ የተለወጡ ንዑሳን አንቀጾችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በአብዛኛው በንዑስ አንቀጽ ደረጃ የተካሄዱ ለውጦች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር ሙሉ በሙሉ አዋጁን ከመለወጥ በማሻሻያ መልክ ቢወጣ ከዚያ ቀጣይ በሚደረጉ የወረቀትም ይሁን ዲጂታል ኅትመት ላይ ማሻሻያዎቹን አብሮ ማተም፣ በግርጌ ወይም የጎን ህዳግ ላይ የተለወጡትን ማመልከት ቢቻል ለሕግ ጥናትም አተረጓጎምም አመቺነቱ የጨመረ ይሆን ነበር፡፡ ሌላው ጉዳይ ረቂቅ አዋጁ የሴት ሠራተኞችን የሥራ ግንኙነት በሚመለከት የተደረጉ ማሻሻያዎች እንደተጠበቁ ሆነው በጥቅሉ ሲታይ ቀድሞ ከነበረበት የሥራ ግንኙነት ሚዛን ወደ አሠሪው የማጋደል አካሄድን መርጧል፡፡ ለዚህ ምርጫ በምክንያትነት የተወሰደውን ከረቂቁ ማብራሪያ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይኼውም የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን ሲባል አሠሪዎችን (ኢንቨስተሮችንና ባለሀብቶችን) የማበረታታት ምርጫ መደረጉ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከፖሊሲ (ርዕዮተ ዓለም) አንፃር ካየነውም ወደ ልማታዊ መንግሥት ጠልቆ የገባ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የልማታዊ መንግሥት መለያ ገጽታዎችና በረቂቁ ውስጥ ለአሠሪው የተጨመሩ መብቶችን (የሙከራ ጊዜ፣ የሥራ ስንብት ምክንያቶች፣ የትርፍ ሰዓት ሥራን በአብነት ማንሳት ይቻላል) በዋቢነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...