በንጉሥ ወዳጅነው
በአገራችን የዘውጌ ፖለቲካ መካራርና ፈር መልቀቅ እያደረሰብን ያለው ቀውስ፣ ከእለት ወደ እለት እየከበደና እያስፈራ ነው፡፡ በተለይ በብዙኃኑ ሕዝብ የጋራ ሕይወት፣ የአብሮነት ተስፋና የዕለት ከዕለት ጉዞ ላይ የከፋ ደንቃራ እየሆነ ለመምጣቱ ያለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እርግጥ የአገራችን የብሔርተኝነት ጥግ አሳፋሪ የሚሆነው መተዛዘን የሌለበት፣ ሁሉም ለራሴ በሚል ብሒል የራሱን ጥቅም ለማስቀደም የሚጣደፍበት መሆኑና ዛሬም በለውጥ ማግሥት ነን በምንልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ችግሩ ተንሰራፍቶ መገኘቱ ነው፡፡
በመሠረቱ የትኛውም የአገራችን ክፍል ቢሆን ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ታሪካችን መሠረት የተዋለደና የተዋሃደ እንደ መሆኑ፣ ኅብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ ብሎም ታሪኩም የሁሉም አሻራ ያረፈበት ነው፡፡ ምንም እንኳን የዘውግ ፖለቲካ ስለመነጣጣል እየሰበከ አብሮነታችንን ቢሽረሽረውም፣ ለብቻ የተሠራ ወይም በአንድ ዘውግ ብቻ ተገነባ የሚባል አካባቢም አልነበረንም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ አሁን አሁን ግን በየአጥቢያውና አካባቢው የምንታዘበው አሳዛኝና አሳፋሪ እየሆነ መምጣቱን፣ በአንዳንድ መገለጫዎች መጠቃቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥ ድኅረ ተሃድሶው ኢሕዴግና የለውጥ ኃይሉም ቢሆን አደጋውን በሚገባ እየተረዳው የመጣ ይመስል ነበር፡፡ መንግሥት ቢያንስ በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ዘረኝነት ነውርና ፀያፍ መሆኑን በግልጽ ማውገዝ በጀመረበት ወቅት፣ ብዙዎች ይለወጣል የሚል ተስፋ ሰንቀውም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል ‹‹በማስ›› ስፖርት ውድድሮች፣ በጋራ የፅዳት ዘመቻዎችና መሰል መድረኮች ላይም ድርጊቱን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች ሲያወግዙት እየተደመጠ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎችም ቢሆኑ ስለአብሮነትና አንድነት ደጋግመው ማውሳታቸው፣ ለውጡን ሊያፋጥነው እንደሚችል ይታመናል፡፡ እስካሁን እንደ አገር የተከመረው ችግር ግን ጉዳቱ ቀላል አልሆነምና አሁንም ከቀውሱ ለመውጣት ገመናዎቻችንን መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡
የሐዋሳ ነበራዊ ሁኔታ እንደ ማሳያ
‹‹ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ፣
የሲዳሞ ቆንጆ እንዴት ነሽ፤›› ሲባልላት የኖረችው የደቡቧ ፈረጥ ሐዋሳ ባለፉት 27 ዓመታትም እጅግ በፍጥነት ካደጉት የአገራችን ከተሞች ተርታ የምትመደብ ነበረች፡፡ አይ ጉድ ‹‹ነበረ/ች›› ቀልድ እየመሰለ መጣ መሰለኝ፡፡ አሁን ግን የዘር ፖለቲካ፣ የባለቤትነት ውዝግብና ስግብግብነት ክፉኛ ይፈትናት ይዟል፡፡ ያን ሁሉ ኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪና መሠረተ ልማት በአጭር ጊዜ የሰበሰበች መዲና በመንደርና ዘውጌያዊነት ልክፍት ተተብትባ ለመውደቅ የተቃረበች መስላለች፡፡ በዚህ ከቀጠለችም ያለ ጥርጥር የውድቀት ማሳያ መሆኗ አይቀሬ ነው፡፡ እንዲያውም ከሰሞኑ በጨንበለላ ባህላዊ የአካባቢው በዓል ብዙዎች ያደረባቸው ሥጋት ቀላል አልነበረም፡፡
እዚህ ላይ የምጽፈው የሰማሁትን ሳይሆን ያየሁትንና የታዘብኩትን ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን በደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሐዋሳ የመገኘት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ከዘመድ ቤተሰቦቼ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ለዓመታት በከተማዋ ከኖሩና በተለያየ የሕይወት መስክ ከተሰማሩ ዜጎች ጋርም ለመገናኘት ሞክሬያለሁ፡፡ እጅግ በሚያሳዝን ደረጃ ከተማዋ ሥጋት፣ ቀላል የማይባል ዘረኝነትና መገፋፋት ብሎም የወንጀል ድርጊት፣ ሥራ አጥነትና ኑሮ ውድነት ነግሦባት ነው ያገኘኋት፡፡
በእውነቱ በአገሪቱ ለሦስት አሥርት ዓመታት የተንሰራፋው የጎሳ ፌደራሊዝምና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የቀፈቀፈው ስሜታዊ ትውልድ በኤጀቶ፣ በቄሮ፣ በፋኖና በመሳሰሉት ተደራጅቶ ለለውጡ (የሕወሓት/ኢሕአዴግን ኢፍትሐዊ አገዛዝ ለማረም) ቢያግዝም፣ ግብታዊና የማያመዛዝን ኃይል መሆኑን የተረዳሁበት ወቅት ነበር፡፡ ከተማዋን ኤጀቶ የተባለው የወጣቶች ስብስብ ሥርዓት አልባ አድርጎት መክረሙ ለአባባሉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
እንዲያውም አሁን ጋብ ብሎ እንጂ ሁኔታው እየከፋ ሄዶ ነበር ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡ ሰሞኑን ፌዴራል ፖሊስና መከላከያ ሐዋሳ በመግባታቸው የቀነሰ ቢመስልም፣ ከተማው በሕገወጥ ወጣቶችና ዘራፊዎች ብሎም ዓይቶ እንዳላየ በሚያልፈው የከተማዋ ፖሊስና አስተዳዳር ብልሽትሽቷ ወጥቶ እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ በተለይ ለበርካታ ዓመታት የኖሩና አንዳንዶቹም ምናልባትም ከተማዋን የቆረቆሩ የአማራ፣ የወላይታና የጉራጌ ማኅበረሰብ አባላት እየደረሰባቸው ያለው ጫናና መገፋት በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚያስከፋ ሆኖ ይገኛል፡፡
እሱ ብቻ ሳይሆን በመዲናዋ አንዱ ብሔር ከሌላው ተዋልዶና ተጋብቶ (በተለይ ዘርና ጎሳ ሳይቆጥር በኢትዮጵያዊነት ተዋህዶ) የፈጠረውን ኅብረት ለመገዝገዝ የተጀመረው ጥረት ያለ ጥርጥር የሚያስከትለው ተያይዞ መውደቅን ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት በከተማዋ ‹‹ክልል እንሁን›› በሚል በተከታታይ የሚጠራውን ሠልፍ ማበረታቻ ሴቶችና ወጣቶች ሠልፍ እንዲወጡ በማድረግ እያሞቁት ነው፡፡ አስከፊው ነገር ደግሞ በሠልፉና በየኳስ ሜዳዎች በሚካሄዱ ትዕይንተ ሕዝብ ከመድረኩ ዓላማዎች ውጪ ዜጎች ወደ ግጭትና ብሔር ተኮር ጥቃት እያማተሩ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡
በተጨባጭ እኔም እንዳየሁት ማንም ቢሆን በከተማዋ በባጃጅ በተለይ በምሽት በነፃነት መሄድ አይችልም፡፡ በሞተር ብስክሌት የታገዘ የቦርሳ ንጥቂያና ዝርፊያም ተባብሷል፡፡ ማምሸት ወይም ማለዳ በእነዚያ የሚያማምሩ (የፍቅር ሐይቅና የፍቅር ጎዳናዎች) መንቀሳቀስ አስፈሪ ሆኗል፡፡ ያለ ጥርጥር ይህን ወደ ኋላ የመመለስ የውድቀት መንገድ የፈጠረው ደግሞ፣ ከዘር ፖለቲካ ለመውጣት ያለ መጠንከር አባዜያችን ነው፡፡
በአላሙራ፣ በአዲሱ ገበያ፣ በአቶቴና በአዲሱ መናኃሪያና በመሳሰሉ አካባቢዎች ደግሞ ዘረፋና ንጥቂያው ከቦርሳም አልፎ በመኖሪያ ቤትና በንግድ ድርጅቶች ላይ ጭምር ነው፡፡ በዚህ መዘዝ ያልተዘረፉት አብዛኞቹ የንግድ ድርጅቶችም ተዘግተዋል፡፡ በግለሰቦች አጥር በር ላይ ሳይቀር ከወራት በፊት ማንነትን የሚገልጽ በቀለም ጽፈው ነዋሪዎች ከመሸበራቸው ባሻገር፣ አሁንም ድረስ ያለምንም ለውጥ ጽሑፉ መታየቱ እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡
ይህ አስከፊ ድርጊት ደግሞ ፖለቲካዊ መልክም እየተሰጠው ለወራት የተካሄደ ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ በማንነታቸው ብቻ የተዘረፉ ቤቶች፣ የተበረገዱ በርና መስኮቶች፣ ብሎም የተገነጣጣለ ጣሪያ ማየት አስገራሚ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም ከሌላ አካባቢ የመጡ አንዳንድ ነጋዴዎች ውሎ አዳራቸውን በመጠራጠርና በተጠንቀቅ መሆኑን ነው የገለጹልኝ፡፡ በመሠረቱ የሲዳማ የክልል ጥያቄስ ቢፈቀድ ሌላውን ሕዝብ የማያቅፍ ክልል የመፍጠር ግብ ነው እንዴ የተቀመጠው? ሐዋሳስ ብትሆን ከክልሉም በላይ የመላው አገሪቱ ሕዝቦች አሻራ ያረፈባት አልፎም የዓለም ባለሀብቶችን ለመሳብ የተዘጋጀች ሆና ስታበቃ በመንደር ሥሌት ማሰብ የት ሊያደርስን ነው? ያስብላል፡፡
ጉድ እኮ ነው! እጅግም የሚያስገርም ርካሽ ተግባር ሰው በአገሩ (ኢትዮጵያዊያን በየትም ዓለም ተንደላቀው በሚኖሩበት ዘመን)፣ ለዓመታት ተወልዶ በኖረበት፣ ብሎም ሠርቶ በሚኖርበትና በሚቀየርበት ምድር እንዴት ባዕድ ሆኖ ለከፋ ችግር ይጋለጣል? ያውም ትንሿ ኢትዮጵያ ስንላት በኖርነው ክልል መዲና ሐዋሳ!! ሐዋሳ!!
በነገራችን ላይ በዚህ መዘዝ ከተማዋ እንደ በረዶ ቀዝቅዛ፣ ከፈጣን ዕድገቷ ታቅባ፣ ዓለም አቀፍ አይደለም አገራዊ ካባዋንም አውልቃ ነው ያገኘኋት፡፡ ዛሬ ባጃጅ አሽከርካሪዎች እንኳን ሥራ ሞቶባቸዋል፡፡ የመዝናኛ ሥፍራዎችም እምብዛም ቱሪስትና እንግዳ ሲያስተናግዱ አይታዩም፡፡ በየቦታው በብዛት የተለቀቁ ቤቶች ‹‹የተከራይ ያለህ›› እያሉ ነው፡፡
በአሁኑ ሁኔታ በሐዋሳ አይደለም መሬት ቤት የሚገዛ የለም፡፡ ባንክ ያጫረታቸው የሽያጭ ቤቶችም በእጥፍ እየቀነሱ እንዳሉ እዚያው ያገኘሁት ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ኢንቨስትመንቱም ይስፋፋል እንዳይባል ባለሀብቱ ሁሉ ቆም ብሎ እንዲያስብ ነው የተገደደው፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የኋላቀሩ የዘር ፖለቲካ ውድቀት አንድ ማሳያ ይሏል ይኼንን ነው፡፡
በመለያየት ያጣነውን መርሳት አይገባም!
ባለፉት 28 ዓመታት የአገራችን ሕዝቦች ዋነኛ መገለጫ በብሔር፣ በሃይማኖትና አለፍ ሲልም በመንደር መፈላለግና መሰባሰብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን እውነታ በፖለቲካ አደረጃጃት፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ (አክሲዮን፣ የሥራና ቤት ማኅበር..) ወይም በማኅበራዊ ጉዳዮች (የሰንበቴ ማኅበርና ዕቁብ ሳይቀር) ውስጥ ወለል ብሎ እናየዋለን፣ እየኖርነውም ነው፡፡
በተቃርኖ ፖለቲካዊ አካሄድም አንዱ ብሔር ሌላውን እንዲያጠቃ ተሰብኳል፡፡ ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ የብሔር ፍረጃ (ትምክህትና ጠባብነት) ነበር፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና መዳኘት አንድ መልካም ነገር ቢሆንም፣ ቢያንስ አንድና ሁለት የፌደራሉ የጋራ የሥራ ቋንቋ ተጠናክሮ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ዜጎች በአንድ የጋራ ሰንደቅ ሥር እንዲሰባሰቡ ከማድረግ ይልቅ፣ ቀለማቸው እንኳን በውል በማይታወቁ ወፈ ሰማይ የክልል ሰንደቆች አገር ምድሩን መሙላት እንደ ትጥቅ ማስፈቻ ሥልት ሆኖ ቆይቷል፡፡
የትምህርት ፖሊሲ አፈጻጸምም በክልል የታጠረ ነበር፡፡ የተሽከርካሪ ሰሌዳና የግል መታወቂያም መገለጫቸው ማንነት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድ በየትም አገር እንደሌለ ብቻ ሳይሆን፣ የዘር ፍጅት ምልክት እንደሆነ ብዙዎች ሲጮሁ ቢኖሩም ሰሚ አለማግኘታቸውም ሊዘነጋ አይችልም፡፡
ከመነሻው በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት እንደሚፈጥር ተስፋ የተጣለበት ነበር፡፡ ይሁንና ገና ከአስተዳዳር ክልል አወሳሰኑ ጀምሮ በዋናነት ብሔር ላይ ብቻ በመንጠልጠሉ፣ የሁሉም ክልሎች አከፋፋል ወጥ የሆነ መሥፈርትን የተከተለ ባለመሆኑ፣ አወዛጋቢ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ተድበስብሰው በይደር በመቆየታቸው ለአሁኑ ትውልድ ጭቅጭቅ አውርሶታል፡፡
በእርግጥ ዛሬ በአንድነት መንፈስ ቆም ብሎ የሚነጋጋር ልሂቅም ሆነ ሽማግሌ እየጠፋ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ተከባብሮ፣ ተዋልዶና ተሳስሮ የኖረው የየአካባቢው ሕዝብ በማንነቱ ብቻ አሳዳጅና ተሳዳጅ ሆኖ ሲታይ (ሐዋሳን በመሰሉ ትልልቅ የብዝኃነት ከተሞች ጭምር) የፈተናውን መክበድ ያሳያል፡፡
ሁሉም በራሱ አጥርና ጎሬ ተደብቆ እንዴት ያለ አገርና ዕድገት ማረጋጋጥ እንደሚቻልም ግራ አጋቢ ነው፡፡ ወጣቱ ኃይል ደግሞ ‹‹የእኔ የእኔ›› ባይነትን ዋነኛ ጠባይ አደርጎ፣ በወሰንና በመንደር አጀንዳ ብሎም በጎጥ አስተሳሰብ ማዶና ማዶ ሆኖ መተጋተጉን ገፍቶበታል፡፡ ባሳለፍናቸው ቀናት በዩኒቨርሲቲዎች በማንነታቸው የሚሳደዱ ብቻ ሳይሆኑ የሚገደሉ ዜጎች መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡
ሌላው ቢቀር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር በዘርና በመንደር እየተቧደነ ተማሪ የሚገዳደልባት ብቸኛ አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥርተን ያረፍነው፣ በመለያያት ጉዟችን ምክንያት ነበር፡፡ በመጪው ጊዜም በየመንደሩ የወሰን፣ የማንነት፣ የክልልና የልዩ ዞን ልሁን ጥያቄዎች መቼ ተፈትተው እንደሚያልቁ ግራ አጋቢ እንደሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህን ወልጋዳ አካሄድ መቀየር ካልተቻለ፣ አዲሱ ሥርዓት ምን ሊስተካካል ይችላል ብሎ ወደ ውስጥ ማየት ይገባል፡፡
በመሠረቱ መለያየታችንና አንድነት ማጣታችን ያተረፈልን በአገሪቱ ቀስ በቀስ እየፈረጠመ በመጣው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይል እየተነጠሉ መቀጥቀጥ፣ መታፈንና መበደል ነበር፡፡ እንዲሁም ዜጎች ከአገራዊ ሀብቱ (ኬኩ) በፍትሐዊነት እንዳይጠቀሙ መደረግ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙኃኑ ሕዝብ በሕጋዊ መንገድ የብዛቱንና ተሳትፎውን ያህል ሳይጠቀም፣ ጥቂት የተቧደኑ ዘራፊዎች ሥርዓቱን ተገን አድርገው በተፈላቀቀው ሕዝብ ውስጥ እንደፈለጉ እየገቡ እንዲመዘብሩና እንዲፋንኑበት ተደርገዋል፡፡ የዜጎች የግል መብትም ተጨፍልቆ ነበር የቆየው፡፡
ማጠቃለያ
እንግዲህ ከዚህ አብነታዊ ማሳያ ተነስተን በአገር ደረጃ በተለይ በከተማ ነዋሪዎችና በተማረው ወገን ረገድ የተደቀነውን ጠባብ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለነገሩ የጠባብ ብሔርተኝነት የተዛባ ፖለቲካ የስበት ማዕከል አርሶ አደሩንም ቢሆን ከቀን ወደ ቀን እየጎተተው ነው፡፡ ስለሆነም በዘር ፖለቲካ መዘዝ አገርና ሕዝብ እያረፈባቸው ያለውን የጭካኔ በትርም መመርመር የግድ ይላል፡፡
በመሠረቱ አገራችን ከነበረችበት ጥልቅ የጭቆናና የአሀዳዊነት ታሪኳ ተላቃ እነሆ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መራመድ ከጀመረች ሦስት አሥርት ዓመታት ተቃርቧል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን የልማት ተስፋዎች ቢታዩም ዴሞክራሲው ባለመዳበሩ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል በመጥፋቱ፣ ብሎም የአገር አንድነቱ ይበልጥ በመሸርሸሩ፣ አገራችን ከማንም የላቀ ሀብት ኖሯት ከብዙዎች በታች ሆና የኖረች፣ ከማንም ያላነሰ ታታሪና አገር ወዳድ ሕዝብ እያላት በድህነት ስትማቅቅ የዘለቀች ለመሆን እንደተገደደች የሚታወቅ ነው፡፡
እውነት ለመነጋገር ዘረኝነት፣ ጠባብነትም ይባል ስግብግብነት ይወገድ እንጂ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ በቂና ከበቂ በላይ ነች፡፡ ሀብቷም እልፍ ነው፡፡ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ያለውን የተፈጥሮ ሀብት እንኳን ወደ ጎን ብለን፣ በሕዝቦቿ መካከል ያለውንና ዓለምን የሚያስደምመውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርስ ወይም የብዝኃነት ሀብት ብንመለከት እንደ ኢትዮጵያ የታደለ አገር ማግኘት ሲበዛ ብርቅ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሀብቷ ለዘመናት ውበቷና ጌጧ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ብልጭ ያለውን ተስፋ በሚያጨለም ደረጃ፣ አሁንም እርስ በእርስ ሲያባላንም እየታየ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መታረም በነበረበት ጊዜ ባለመታረሙ፣ መስተካከል በነበረበት አጋጣሚም ሳይስተካከል በመቅረቱ የአገራችን ዕድገትም ታውኮ ቆይቶል፡፡
እስካሁንም በሚፈበረክልን የውዥንብር ትርክት አንዳችን ለሌላችን እኩል ማስፈለጋችን ሳይገለጥልን፣ ወይም እንዲገለጥልን ሳንፈልግ ለዘመናት በመኖራችን መድረስ በነበረብን ሥፍራ ላይ ሳንደርስ ቆይተናል፡፡ ይኼ ደግሞ እንደ ትውልድና እንደ አገር ሊቆጨን ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን የደረስንበትን ሁሉን አቀፍ የዕድገት ጅምርና ለውጥ ስናስብ ምነው ቀደም ብለን ጀምረነው በነበር ያስብላል፡፡
በመሠረቱ በደግም ሆነ በክፉ የታሪክ ምዕራፍ ኢትዮጵያዊያን አብረን ከመጣነው ገና የምንጓዘው እንደሚበልጥ ማስተዋልም ከሁሉ መቅደም ያለበት ነው፡፡ ለአብነት በጠቀስናት ከተማም ሆነ በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች ይህ ግንዛቤ ፈር መሳቱንም ፈጥነን ልንነቃበት የሚገባ ነው፡፡ ስለሆነም ከዘር ፖለቲካ ስካር በመላቀቅ እንደ አገር ወደ ጠንካራ አንድነትና የሕዝቦች አብሮነት ግንባታ መሸጋገር ያስፈልጋል እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡