Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጥያቄያችን ግማሹ መልስ ከእኛው ይኖር ይሆን?

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር በርካታ ጥያቄዎች አሉበት፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ታፍነው የቆዩ፣ ጊዜ ሲጠብቁ የነበሩና ሌሎችም አታካች ጥያቄዎች አይጠፉም፡፡ የለውጥ ሒደቱ የጎረበጣቸው ወገኖችም ቢሆኑ ቁጭት ያዘሉ ጥያቄዎቻቸው ተበራክተዋል፡፡

መንግሥት ሊመልስልን ይገባል ተብለው በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚቀርቡ የትየለሌ ጥያቄዎች፣ መንግሥት የሚባለውን አካል ወቅታዊ አቅም ያላገናዘቡ ሆነው እንደሚገኙ ልብ ማለቱ ይገባል፡፡

አንዳንዴ ጥያቄዎቹ ዛሬውኑ ካልተመለሱልን ‹‹ወዮላችሁ›› የሚል የማስፈራሪና የዛቻ ልብስ ያላቸው ሆነውም ይገኛሉ፡፡ ችግሩ ጥያቄው መቅረቡ ሳይሆን፣ ሁሉም ይኼ ሊደረግልን ይገባል የሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ መንጠልጠሉና ከአገራዊ ጠቀሜታና ፋይዳው አኳያ የሚነሳው ኢምንት የመሆኑ ነገር ነው፡፡

እንዲህ ሊደረግልን ይገባል እየተባለ ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የሚቀርቡት ጥያቄዎች ለእኔ ብቻ ወደሚል ዝንባሌ ያጋደሉ መሆናቸው ያስገርማል፡፡ በጨዋና በማመዛዘን አግባብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም አክብሮትን መቸር ያስፈልጋል፡፡ ተገቢ የሚባሉና በፍጥነት ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ምን ነበር? ዛሬስ ምን እየተደረገ ነው? የሚሉትን በማመዛዘን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ አገናዝበው የሚሰነዘሩና የሚቀርቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሊከበሩ በአግባቡ ሊመለሱም ይገባቸዋል፡፡

ነገር ግን ከብዙዎቹ ጥያቄዎች በአዎንታዊ መንገድ እንዲመለሱ የራስንም ድርሻ በማካተት፣ ‹‹እኛም እንዲህ እናደርጋን››፣ ‹‹የእኛንም ድርሻ ተወጥተንና ተጋግዘን እንወጣዋለን›› የሚሉ የመፍትሔ ግማሽ መንገዶችን የሚያቀርብ አካል አይታይም፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ለሁሉ ነገር መፍትሔ ከአንድ ወገን አይጠበቅም፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ተባብሮና ተሳስቦ መጓዝ ካልተቻለ፣ መልካም ውጤት እንዴት ይጠበቃል? አይጠብቅም፡፡ ከሌላ ጠባቂ በሆንበት በቆየ ልምዳችን የቱንም ያህል ቢደረግልን እውነተኛውን ዕርካታ የማግኘታችን ነገር አያሳምንም፡፡ በየትኛውም መንገድ መንግሥት ሊመልስልን ይገባል ተብለው የሚቀርቡ ጥያቄዎች አቅምን ያገናዘቡ፣ ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ከግምት ያስገቡ ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ጠያቂውም ቢሆን የመፍትሔው አካል መሆኑን በመገንዘብ ጥያቄው በአግባቡ እንዲመለስለት አምኖ የድርሻዬን አደርጋሁ በማለት ቢሞግት ውጤቱ ያማረ ይሆናልና በመመካከር ላይ የተመሠረተ ባህል ማዳበሩ ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑ እየታወቀ ብዙ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ፖሊሲዎችና ያረጁ አሠራሮች መነካት የለባቸውም ብሎ ዘራፍ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

ይህ ፖሊሲ ወይም ይህ ሥርዓት ይከተለው የነበረ ፖሊሲ ከተቀየረ አገር ፈራረሰ በማለት በግልጽ በአደባባይ መናገር ለውጥ በሌለው መንገድ መደነባበር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ይህ ከታሰበ ለውጥ ለምን ተባለ? በቀድሞ አሠራር እንጓዝ ማለት ለውጥ አለ ከተባለ አደናቃፊ የነበሩ አሠራሮች በታደሰ በአዲስ መተካትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ጊዜው በሚጠይቀው አመለካከት ተቃኝተው ለተሻለ ጉዞ መለወጣቸው ይጠበቃል፡፡ ይህ ካልሆነ ያስቸግራል፡፡ እንደ መልካም የሚወሰዱ ካሉም ይህንን ይዞ መቀጠል ይገባል፡፡ ግን ብዙዎቹ ችግሮች አሠራሮቻችን ለውጥ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ይህንን መለወጡ አግባብ ይሆናል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከለውጡ ማግሥት ወዲህ የሚቀርብ አንድ ጥያቄ ግን በተለያየ መታየት ያለበት ይሆናል፡፡ ይህም የለውጡ አመራር የአገሪቱ መንግሥታዊ ሥርዓት አቅጣጫ ጥርት ባለ ሁኔታ የወደፊቱ ጉዟችን በዚህ መልክ ይሆናል የሚል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ባይችል እንኳን ሥርዓቱ ሊጓዝ የሚችልበትን ጠቋሚ ነገር ማሳየት አለበት የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ከገለጹት በተግባርም እየታየ እንዳለው አገሪቱ ስትሠራበት የቆየችው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ የመንግሥት ሥሪት መለወጥ ካለበት ተመክሮበት የሚለወጥ መሆኑን ነው፡፡

ስም አልወጣለትም እንጂ ኢሕአዴግ ሲሠራበት ከቆየው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አካሄድ ወጣ ያሉ ሥራዎች እያየን በመሆኑ ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚሆን ይቀረፃል፡፡ በእርግጥ ድርጅቱ በጽሑፍ ሲያስቀምጠው ይህንን አመለካከት አልቀየረም፡፡ የተደለዘ ነገር የለም፡፡ ኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥት አመለካከቱን አልቀየረም የሚለው ነገር የሚናፈሰውም ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ከዚህ ቀደም አላሠራ ያሉ ፖሊሲዎች መቀየር ይኖርባቸዋል የሚል አመለካከት አለውና ይህ መታየት ይኖርበታል፡፡  

ይሁንና አሁን በዚህ ለውጥ ሒደት ግን ይህ አመለካከት በተግባር እየተለወጠ መምጣቱን የሚመለክቱ ተግባራትን እያየን ነው፡፡ በተለይ በኢኮኖሚው ረገድ አገሪቷን ወደፊት የሚያራምደውንና ከቀደመው የታየ ለውጥ መኖሩን የሚያሳየው ፖሊስ ቢያንስ አመላካች መሆን ይኖርበታል፡፡

እውነታው ይህ ቢሆንም አሁንም የብዙዎች ጥያቄ የዶ/ር ዓብይ አሠራር ቁርጥ ያለውን ሥርዓት መግለጽ ይኖርባቸዋል ለሚለው ጥያቄ ለሁሉም ሊገባ በሚችል መልኩ ሊቀርብ ይገባል፡፡

በዚህ ዙሪያ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ቢያንስ አመላካች በሆነ መንገድ መገለጹ በኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን አቅጣጫ ከወዲሁ በማወቅ ፕላን ለማድረግና ለመዘግየት ስለሚያመች ነው፡፡ በተለይ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በግብይቱ ውስጥ ያለውን የተዘበራረቀ አካሄድ መስመር ለማስያዝና የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠርም ቢሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲው አመላካች መሆኑ ይጠበቃል፡፡

ይህ የሸማቾች ጥያቄ ጭምር በመሆኑ የለውጡ መሪዎች በዚህ ጉዳይ ፈጠን ያለ መልስ ሊሰጡ ይገባል፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት