Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሞጆ ደረቅ ወደብን የማስፋፋት ፕሮጀክት መዘግየቱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በዘጠኝ ወራት 1.4 ቢሊዮን ብር አትርፏል

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሞጆ ደረቅ ወደብን ለማስፋፋት የዘረጋው ፕሮጀክት በትግበራ ሒደት ላይ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ከታቀደው አኳያ መዘግየቱን ገለጸ፡፡

ከሦስት ዓመታት በላይ የዘገየውና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክት፣ የሞጆ ደረቅ ወደብና የኮንቴይነር ተርሚናልን ለማስፋፋት የተወጠነ ቢሆንም፣ ከታቀደለት ጊዜ እንደዘገየ የገለጹት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ናቸው፡፡ ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት ከሆኑት መካከል፣ የመሬት ወሰን ማስከበር ችግር አንዱ እንደነበር በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ግን በተወሰነ መልኩ የማሽነሪ ግዥ እንደተካሄደና አገልግሎቱም እንደተስፋፋ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የሞጆ ደረቅ ወደብ አሁን ባለበት ሁኔታ 62 ሔክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ143 ሔክታር ይዞታ ይኖረዋል፡፡ ወደፊትም እስከ 200 ሔክታር ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የደረቅ ወደቡን የማስፋፊያና የማዘመኛ ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ በተገኘ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ወደቡን አማካይ አካባቢ ላይ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ ዋና መንገዶችን እንዲሁም የባቡር መንገዶችን ከወደቡ ጋር በማገናኘት ትልቅ የአስመጪና ላኪ ሥራ የሚሠራበት የወደብ ማዕከል ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ማሽነሪዎችን በማስገባት ምርቶችን የማቀነባበር ሥራም ዕዛው በወደቡ እንዲካሄድ በማድረግ የምርት ሒደትንና ሰንሰለትን ማቅለል የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚመቻች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሸብር ኖታ ገልጸዋል፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከዓለም አቀፍ ወኪሎቹ ጋር ባደረገው ዓመታዊ ጉባዔ ወቅት ነው፡፡ በጉባዔው 27 አገሮች የተውጣጡ 46 ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ወክለው የመጡትም የኢትዮጵያ መርከቦች መዳረሻ የሆኑ 320 በላይ ወደቦችን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መርኮች አፍሪካን ከእስያ ከማገናኘት ባሻገር በአውሮፓም መቅዘፍ እንደጀመሩ ይታወቃል፡፡

የዘንድሮውን ዓመታዊ ጉባዔ ከሌላው ጊዜ የሚለየው፣ ከሥራ አፈጻጸም ግምገማ ባሻገር ወኪሎቹ በአሁኑ ወቅት በተቋሙም ሆነ በአገሪቱ እየታየ ባለው ለውጥ ተጠቅመው በመረጡት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከወኪልነት ባሻገር የወደፊት ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር መስማማት ላይ መድረስ የሚቻልበት ዕድል መፈጠሩን አቶ ሮባ አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ወደ ግል እንዲዛወሩ ከወሰነባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሲሆን፣ መንግሥት በሎጂስቲክስ መስክ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ አጋሮቻቸው ጋር በሽርክና መሥራት የሚችሉበትን የኢንቨስትመንት ፈቃድም ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጭነት በባህር የማጓጓዝ አቅሙ በዓመት አራት ሚሊዮን ቶን በላይ እንደደረሰ የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡ ተያዘው በጀት ዓመት፣ የድርጅቱ ጠቅላላ ጭነት 3,855,248 ቶን ሲሆን፣ በራሱ መርከቦች ያስተናገዳቸው ጭነቶችም 796,955 ቶን እንዲሁም በስሎት ወይም በኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች አማካይነት 3,058,293 ቶን አጓጉዟል፡፡

 ድርጅቱ 11 መርከቦች ያሉት ሲሆን፣ ሁለቱ የነዳጅ ጫኝ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በጠቅላላው በአንድ ጊዜ 400 ሺሕ ቶን ጭነት የማጓጓዝ አቅም ያላቸው እነዚህ መርከቦች፣ ወደ አገሪቱ ከተጓጓዘው ጠቅላላ ጭነት ውስጥ በመቶኛ ሲሰላ 21 በመቶ ድርሻ እንደያዙ የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ የዘጠኝ ወራት የድርጅቱ አፈጻጸም መሠረትም፣ ተቋሙ ከታክስ በፊት 1.384 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች