በውኃ ሳምንት ፕሮግራም 85 ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹የውኃ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተስፋ›› በሚል ርዕስ ሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ማክበር በጀመረው የውኃ ሳምንት፣ በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይቶች መካሄድ ጀመሩ፡፡ በውይይቱ ትኩረት ይደረግባቸዋል ከተባሉት መካከል ከዚህ ዓመት ጀምሮ በሰፊው ስለሚገባበት የመስኖ ግድቦችና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ በተለይም የታላቁ የህዳሴ ግድብና የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርብ እንደተናገሩት፣ በ2012 በጀት ዓመት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሚመደበው ለመስኖ ፕሮግራሞች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞችና የከርሰ ምድር ውኃ ባለቤት፣ ከ74 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሊታረስ የሚችል መሬት ባለቤት ሆና እያለ፣ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ስንዴና ዘይት የምታስገባ አገር መሆኗ ዘግይቶም ቢሆን ቁጭት እየፈጠረ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በመጠኑ፣ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በጥልቀት ወደ መስኖ ልማት የመግባት ዕቅድ የነደፈች ሲሆን፣ ቆላማ ቦታዎችን ያካተተ ሰፋፊ የእርሻ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ ተብሏል፡፡
የህዳሴንም ሆነ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከችግር በማውጣት ረገድ አስፈላጊ ግብዓቶች ከውይይቱ ይገኛል ተብሎም ታቅዷል፡፡
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የውኃ ሳምንት ፕሮግራምን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹በመስኖና በኃይል ማመንጫ ሥራዎች ላይ የገጠሙን ችግሮች ለውይይት ቀርበው፣ ከመሰል ችግሮች የወጡ አገሮች ልምድ የሚቀሰምበት ፕሮግራም ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በቀጣይ የምንከተለው አቅጣጫ በመንግሥትና በግል አጋርነት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ነው፡፡ በውይይቱ ጥሩ ልምድ ካላቸው አገሮች ልምድ እንቀስማለን፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በይፋ የተከፈተው የውኃ ሳምንት ፕሮግራም እስከ ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ይቆያል፡፡ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ፕሮግራም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በመጡ የዘርፉ ምሁራን 85 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከዚህ በኋላ አገሪቱ ትኩረት በምታደርግበት የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮግራም የገቡና የሚገቡ ባለሀብቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ግንባታ የሚደግፉ አካላት፣ ታዋቂ ግለሰቦች የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማትና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ይሳተፋሉ፡፡
በውኃ ሳምንት ፕሮግራም ውይይቶች፣ ዓውደ ርዕይና የተለያዩ ትዕይንቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምትከተላቸው ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ግብዓት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡