Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የተደረገው ማስተካካያ የተፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የብር የውጭ ምንዛሪ የመግዛት አቅም በ2010 ዓ.ም. በ15 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የተፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘ የፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የዘንድሮ በጀት ዓመት የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው።

የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ ፍጹም አሰፋ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኮሚሽኑ ከሌሎች የመንግሥት አስፈጻሚ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ ግምገማ ማካሄዱን፣ በዚህም በዕቅድ ዘመኑ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከያ የተፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ መገምገሙን አስረድተዋል።

ከዓመት በፊት የብር የውጭ ምንዛሪ የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ የተደረገበት መሠረታዊ ምክንያት፣ የኤክስፖርት ዘርፉን ለመደገፍ እንደነበረ ይታወሳል። ባለፈው ሳምንት የ2012 በጀት ዓመትን ረቂቅ በጀት ለፓርላማው ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት መከሰቱንና የዚህ መዛባት መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ የኤክስፖርት ዘርፉ አፈጻጸም ከማደግ ይልቅ በማሽቆልቆል ሒደት ውስጥ መሆኑን አመልክተው ነበር።

 አቶ አህመድ ያቀረቡት ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2011 ዓ.ም. አሥር ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ከኤክስፖርት ዘርፉ የተገኘ ገቢ ከ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ (2.3 ቢሊዮን ዶላር) ጋር ሲወዳደር፣ በ187.1 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑን መግለጻቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

በዚህም የተነሳ የውጭ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ አምራቾችን ፍላጎት በሚጠበቀው ደረጃ ማሟላት አለመቻሉን፣ በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሠረታዊ ዕቃዎች አቅርቦትንም ቢሆን ማቅረብ አለመቻሉን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ይህንንም ተከትሎ የአንዳንድ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ በማሳየት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 በተጨማሪም የአገሪቱ የኤክስፖርት ንግድ መዳከም የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ፣ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ሥጋት ደረጃ እንዲጨምርና ይህም ተጨማሪ የልማት ብድር እንዳይገኝና መንግሥት በጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ጫና ማሳደሩን አስታውቀዋል።

የፕላንና ልማት ኮሚሽነሯ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈጻጸም ግምገማ ዋና ዋና ግኝቶችን አስመልክቶ ያቀረቡት መረጃ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሥራ ፈጠራ ረገድ የተገኘው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን፣ የገቢ ንግድ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተከናወነው ሥራ ደካማ መሆኑን ያመለክታል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወነው ሥራም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመገኘቱ የዳቦ ስንዴ፣ የቢራ ገብስና ጥጥ ከውጭ አገር ለማስገባት አገሪቱ መገደዷን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ልማትን በተመለከተ በተለይም በማንፋክቸሪንግ ዘርፉ የተቀመጡ ግቦች ያልተሳኩበትን ምክንያት ጥልቀትና ስፋት ባለው ትንተና ችግሮቹ እስካሁን ተለይተው አለመቀመጣቸውንም እንደ ክፍተት አውስተዋል። ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት አገራዊ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።

ፓርላማው የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም በአዎንታ የገመገመ ሲሆን፣ እየተዘጋጁ ያሉ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መሪ የልማት ዕቅዶች ከጊዜ አንፃር ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስቧል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች