የንግድ ሥራ ለመጀመር ጋሬጣ የነበሩ የሕግ መሥፈርቶች ላይ ማሻሻያ የያዘው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ፀደቀ፡፡
በሥራ ላይ የሚገኘው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ የያዛቸውን አስገዳጅ የሆኑ፣ ነገር ግን እምብዛም ፋይዳ የሌላቸውን መሥፈርቶች የሚያስቀረውን ማሻሻያ አዋጅ ፓርላማው ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. አፅድቋል።
ፓርላማው አዋጁን ባፀደቀበት ወቅት በይዘት ላይ የተነሳ ክርክር ባይኖርም፣ ማሻሻያ አዋጁ የፀደቀው ግን በሦስት የታቅቦ ድምፅ ነበር፡፡ የማሻሻያ አዋጁ የንግድ ሥራ ለመጀመር ይጠየቁ የነበሩ አገልግሎት ፈላጊዎችን ለምልልስ ይዳርጉ የነበሩ መሥፈርቶችን የሚያስቀር በመሆኑና ኢትዮጵያ የምትተችበትን መሰናክል የበዛበት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ሒደት የሚያስቀር መሆኑን እንዳመነበት፣ የማሻሻያ አዋጁን መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረበው የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ አስታውቋል።
በፀደቀው አዋጅ ከተካተቱ የማሻሻያ ይዘቶች መካከል የንግድ ምዝገባን በጋዜጣ ስለማሳወጅ የነበረው አሠራር እንዲቀርና በምትኩ መዝጋቢው አካል ራሱ ተደራሽ የሆነ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚያሳውቅበትን አሠራር እንዲተገብር፣ የመተዳደሪያና የመመሥረቻ ጽሑፎች ሰነድን ለማረጋገጥ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል እንዲረጋገጥ ይጠየቅ የነበረው አሠራር ተገልጋዮችን ከአንድ ቢሮ በላይ እንዲሄዱ የሚያደርግና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ ሰነዶቹን የማረጋገጥ ተግባር በመዝጋቢው አካል እንዲከናወን የሚያስችል ድንጋጌን አካቷል።
የንግድ ምዝገባ አገልግሎትን ለማግኘት ተገልጋዮች በአካል ወደ መዝጋቢው አካል መምጣት ሳይጠበቅባቸው፣ መዝጋቢው አካል የኢንፎርሜሽን መገናኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተገልጋዮች በአካል ሳይቀርቡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራሮችና ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲዘረጋና እንዲያስፈጽም በማሻሻያው ተካቷል።
በሌላ በኩል የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ቅጣት ከማሳደሻ ጊዜ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነጋዴው አሥር ሺሕ ብር በመክፈልና አግባብ ባለው ባለሥልጣን ይሁንታን በማግኘት ያጠፋ የነበረውን ጊዜና እንግልት በማስቀረት እጥፍ በመክፈል ብቻ (20 ሺሕ ብር)፣ የመዝጋቢውና የፈቃድ አዳሹ አካል የበላይ ኃላፊ ይሁንታ ሳያስፈልገውና ሌላ ምንም ዓይነት መሥፈርት ሳይኖረው በቀጥታ ፈቃዱን ማደስ እንዲችል ተደርጎ ተሻሽሏል።
የንግድ ፈቃድ ለማግኘት ይጠየቅ የነበረው የንግድ አድራሻና ይህንን ለማረጋገጥ ይጠይቁ የነበሩ የቢሮ ኪራይ ስምምነቶችና ማረጋገጫዎች፣ ከሕጉ እንዲወጡ በማሻሻያው ተደርጓል።
የንግድ ተቋማት ካሽ ሬጅስተር ማሽንን ብቻ እንዲጠቀሙ የሚደነግገው አንቀጽ ተሽሮ የግብይት መረጃን የሚይዝ በኮምፒዩተር ሶፍትዌር የታገዘ ደረሰኝ ኅትመትን መጠቀም እንዲችሉም፣ በማሻሻያው ከተካተቱት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።Top of FBottom of Form