የኬንያ ኬንጄን ኩባንያ የቁፋሮ ሥራውን ጨረታ አሸንፏል
በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን ኢተያ ከተማ አካባቢ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው 520 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ረቂቅ ስምምነት ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው፡፡
የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ልማት ስምምነት በመጀመርያ የተፈረመው እ.ኤ.አ. በ2015 ሲሆን፣ ረዥም ጊዜ የፈጀ ድርድር ተካሂዶ የኃይል ግዥ ስምምነት በ2017 መፈረሙ ይታወሳል፡፡ ሬይካቪክ ጂኦተርማል የተሰኘው የአይስላንድ ኩባንያ ሜሪዲየም ከተባለ የፈረንሣይ ኢንቨስትመንት ቡድን ጋር በመጣመር፣ ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥርተዋል፡፡
ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል በምሥራቅ አርሲ ዞን ኢተያ ከተማ አቅራቢያ ቱሉና ሞዬ በተሰኙ ሥፍራዎች የሚገኘውን ዕምቅ የእንፋሎት ኃይል በመጠቀም የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ይሸጣል፡፡
ከተራዘመ ድርድር በኋላ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አንድ ኪሎ ዋት አወር ኤሌክትሪክ በአሜሪካ ሰባት ሳንቲም ለመግዛት ተስማምቷል፡፡
የኃይል ግዥና ትግበራ ስምምነቶች የተፈረሙ ቢሆንም የመጨረሻው ስምምነት፣ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስምምነቱን ካፀደቀው ሰነዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚቀርብ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የጂኦተርማል ልማት ፕሮጀክቱ ስምምነት የሚቀርበው አገሪቱ የኃይል ቀውስ በገጠማት ወቅት በመሆኑ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰነዱን በአፋጣኝ መርምረው ያፀድቁታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሬል ቦይድ ኩባንያቸው የተለያዩ የሲቪል ሥራዎች በማካሄድ ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በአዲስ አበባና በኢተያ ከተሞች ጽሕፈት ቤት በመክፈት፣ በፕሮጀክት ሳይት ላይ የጉድጓድ ውኃ ቁፋሮና የመንገድ ግንባታ ሥራ ማካሄዱን አስረድተዋል፡፡
የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የገለጹት ቦይድ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማትና ገንዘብ ተቋማት ፕሮጀክቱን በገንዘብ ለመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳሳዩ ጠቁመዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋነኛ ባለአክሲዮን ሜሪዲየም ኩባንያ 40 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል ያዋጣ ሲሆን፣ የአሜሪካ የንግድ ልማት ኤጀንሲ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለግሷል፡፡
በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በአውሮፓ ኅብረት የሚደገፈው ጂኦተርማል ሪስክ ሚትጌሽን ፈንድ አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደመደበ የገለጹት ቦይድ የአሜሪካ፣ የፈረንሣይና የጀርመን የልማት ተቋማት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ለፕሮጀክቱ የሚውል ብድር ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
520 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው የቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ፕሮጀክት በአራት ምዕራፍ ተከፍሎ ይከናወናል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመገንባት 250 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ለሁለተኛው ምዕራፍ 100 ሜጋ ዋት፣ ለሦስተኛው ምዕራፍ 100 ሜጋ ዋት፣ እንዲሁም ለአራተኛው ምዕራፍ 270 ሜጋ ዋት ማመንጫዎች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ በ2022 መጀመርያ ማመንጨት እንደሚጀምር ዳሬል ገልጸዋል፡፡
ቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ጉድጓዶች ቁፋሮ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ኩባንያው ያወጣውን የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ጨረታ ኬንጄን የተሰኘው የኬንያ ኩባንያ አሸንፏል፡፡
የኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ የሆነው ኬንጄን 12 የጂኦተርማል ጉድጓዶች የሚቆፍር ሲሆን፣ የመጀመርያዎቹ ሦስቱ የፍለጋ ጉድጓዶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ የቁፋሮ ሥራው አጠቃላይ ወጪ 60 ሚሊዮን ዶላር ሲገመት፣ ቱሉ ሞዬና ኬንጄን የሥራ ውሉን በመጪው ሳምንት እንደሚፈራረሙ ታውቋል፡፡
ኬንጄን የመቆፈሪያ መሣሪያዎቹንና አስፈላጊ ባለሙያዎቹን ወደ ኢትዮጵያ በማጓጓዝ፣ በመስከረም 2012 ዓ.ም. የመጀመርያውን የፍለጋ ጉድጓድ ቁፋሮ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የሚቆፈሩት የመጀመርያ ሦስት የፍለጋ ጉድጓጎች የዕምቅ እንፋሎት ኃይሉ መጠን፣ የሙቀትና ግፊት መጠን፣ እንዲሁም የእንፋሎቱን ጥራት ለማጥናትና ለማወቅ እንደሚያስችል ቦይድ ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱን ጉድጓድ ለመቆፈር ሁለት ወራት ተኩል ያህል የሚፈጅ በመሆኑ፣ የሦስቱ ጉድጓዶች ቁፋሮ በስምንት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
የሦስቱ ጉድጓዶች ቁፋሮ ከተጠናቀቀ በኋላ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ንድፍ ሥራ እንደሚካሄድ፣ ግንባታውን የሚያከናውነው ኮንትራክተር በጨረታ እንደሚቀጠር ቦይድ ገልጸዋል፡፡
የቱሉ ሞዬ የጂኦተርማል ልማት የመጨረሻ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2018 መጀመርያ ተፈርሞ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ይገባል የሚል ዕቅድ የነበረው ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ሒደቱ ሊዘገይ እንደቻለ ቦይድ ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ትግበራ ይገባል የሚል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ 24 ሰዓት፣ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ዘነበ አልዘነበ፣ ድርቅ ኖረ አልኖረ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ መሆኑን ቦይድ ገልጸዋል፡፡
‹‹የውኃ ኃይል ማመንጫ ታዳሽ የኃይል ምንጭ በመሆኑ ጥሩ ነው፡፡ የዝናብ እጥረት ካለ ግን የሚፈለገውን ኃይል አያመነጭም፡፡ 100 ሜጋ ዋት የውኃ ኃይል ማመንጫ ካለህ ዓመቱን ሙሉ በአማካይ የሚያመነጨው 30 ሜጋ ዋት ነው፡፡ ጂኦተርማል ግን 100 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ካለህ ዓመቱን ሙሉ 100 ሜጋ ዋት ያመነጫል፤›› ያሉት ቦይድ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የነደፈችውን ዕቅድ ለማሳካት የጂኦተርማል ፕሮጀክቱ ሊያግዝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል፤›› ያሉት ቦይድ፣ ቱሉ ሞዬና ኮርቤቲ ጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ፣ ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኒውዚላንድ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ በጂኦተርማል ሀብታቸው የሚታወቁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከጂኦተርማል ሀብቷ 10,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ይገመታል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ዕምቅ የእንፋሎት ኃይል ጥራት ከተጠቀሱት አገሮች የበለጠ ነው፤›› ያሉት ቦይድ፣ ጎረቤት ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2000 የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት የነበረባት ቢሆንም ከጂኦተርማል ሀብት 700 ሜጋ ዋት በማመንጨት ችግሩን መቅረፍ እንደቻለች ገልጸዋል፡፡
የቱሉ ሞዬና ኮርቤቴ ጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ጠንሳሽ የሆኑት አቶ ነጂብ አባቢያ፣ ‹‹በኢትዮጵያ መንግሥት ስለምንተማመን ቀድመን ብዙ ሚሊዮን ዶላር አውጥተን በርካታ ሥራዎች አከናውነናል፡፡ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡ ስምምነቶቹን በአፋጣኝ አፅድቆ ወደ ትግበራ በሙሉ ልብ መግባት አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማትን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ የቱሉ ሞዬና የኮርቤቲ ጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ትልቅ ዕገዛ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡