Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ለጋሽ አገሮች የሚሳተፉበት የዓለም ልማት ማኅበር የፖሊሲ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ዕርዳታ ለኢትዮጵያ ተፈቅዷል

በኢትዮጵያ ሲካሄድ የመጀመሪያው በሆነውና ለማኅበሩ የፋይናንስ ድጋፍ የሚሰጡ ለጋሽ አገሮች በየሦስት ዓመቱ የሚሳተፉበት የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር 19ኛው ጉባዔ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ መካሄድ ሲጀምር፣ ከ30 በላይ የዓለም ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ220 ለጋሽ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮችም በጉባዔው በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር አማካይነት ዓመታዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና ለወደፊቱ በሚያስፈልጉ የልማት ድጋፎች ላይ የሚመክረው ይህ ጉባዔ፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ከማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚያደርገው ቆይታው እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2023 ላለው ጊዜ የሚያስፈልገውን የሀብት መጠንና የሚከናወኑ ሥራዎችን ከወዲሁ በመገምገም፣ የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚያመላክት ይጠበቃል፡፡

በተለይ በማኅበሩ በኩል ድጋፍ የሚደረግላቸው አገሮች ላይ እያደገ የመጣውን የዕዳ ጫናን በተመለከተ የሚደረገው ውይይት፣ ከበርካታ የጉባዔው አጀንዳዎች መካከል በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ 

የጉባዔው ታዳሚዎች ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ገንዘብ ምንጭነትና በዓለም ባንክ በኩል በኢትዮጵያ መንግሥት ሲከናወኑ የቆዩ ፕሮጀክቶችን እንደጎበኙ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡ የልማት ማኅበሩ በገንዘብ ድጋፍ ካደረገላቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሥራ ፈጣሪ ሴቶች ልማት ፕሮግራም፣ ውጤታማ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ ተወዳዳሪነትና የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የግጭት አወጋገድ ሥርዓትና መሰል ፕሮጀክቶች አፈጻጸሞች ጉብኝት እንደተደረገባቸው የሚኒስቴሩ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ስለጉባዔው በሰጡት ቅድመ ማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡ 

በዘንድሮው በጀት ዓመት በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ድጋፍ አማካይነት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ በጠቅላላው ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ዕርዳታ እንደሚፈቅድ ይጠበቃል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊትም የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ለመስጠት ከመንግሥት ጋር መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በጥቅሉ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ስምምነት መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ለሳኒቴሽን ሥራዎች የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከሳምንት በፊት መፍቀዱ አይዘነጋም፡፡

የዓለም ልማት ማኅበር እ.ኤ.አ. በ1960 ከተመሠረተ ጀምሮ ለ112 የዓለም ደሃ አገሮች ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ አቅርቧል፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ከ20 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ከማኅበሩ አግኝታለች፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህም 19 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለዓለም ደሃ አገሮች ያቀረበ ሲሆን፣ ለአፍሪካ አገሮችም የ19 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ድጋፍ እንዳቀረበ የተቋሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች