Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበፖለቲካ ጫና አቅሙ የተፈነተው እግር ኳስ ፌዴሬሽን

በፖለቲካ ጫና አቅሙ የተፈነተው እግር ኳስ ፌዴሬሽን

ቀን:

እግር ኳስ ዓለም አቀፋዊ የስሜት ቋንቋ ለመሆን የበቃ ስፖርት ነው፡፡ የእግር ኳስ ስፖርት በኢትዮጵያ አትታደል ቢለው ትርጉም የለሽ በሚመስል ሄድ መለስ ውስጥ ቢገኝም፣ በሌሎች አገሮች ውስጥ ትልቅ ኢንዱስትሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለክለቦችና ለአገሮች ብሎም ለበርካታ የዓለም ሕዝቦች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለኝታነቱ እያየለ፣ መግነ ጢሳዊነቱ እየጎላ የመጣ ፈርጣማ የስፖርት ዘርፍ እግር ኳስ ነው፡፡

የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ሚናውን ያህል ፖለቲካዊ አንደምታውና ጫናውም የጎላ ነው፡፡ ስፖርቱን ተገን አድርገው የሚቀነቀኑ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ከዓመታት ቀድሞ ዕልባት ቢበጅላቸውም፣ ስፖርቱ ከሚመራበት ወዳጅነትና ወንድማማችነት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊነት ባፈነገጠ መንገድ በታዳጊ አገሮች አልፎ አልፎ የሚታየው ድርጊት፣ የእግር ኳስ ሜዳን የጦር ቀጣና እስኪመስል ድረስ ውክቢዎች ተበራክተዋል፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ለዚህ ዓይነቶቹ ችግሮች የሚመራባቸው መርሆዎችና መፍትሔዎች ቢኖሩም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ውስጥ ግን የክለቦች ውድድርን ከፖለቲካ ጫናና ትኩሳት ነፃ አላደረጋቸውም፡፡

በሜዳው የምትንከባለለው ኳሷ ያችው፣ የበነረችው ክቧ ሁሉም የስፖርቱ ተዋንያን በጥበብና በችሎታ የሚቀባበሏትና ከፍጥረቷ ጀምሮ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በዘለቀው ታሪኳ ቅርጿን እንደያዘች የነበረችና የኖረች ነች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጫወቻ ሜዳዎች ስትመጣ ግን የኳሷ ምንነትና ስፖርታዊነቷ፣ ስሜት ፈንቃይነቷ በፖለቲካዊ ጩኸቶችና ድራማዎች ያውም ደግሞ መንደር አደግ አጀንዳ በሚቀነቀንባቸው ሜዳዎች የኳሷ ህልውና አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ የስፖርቱ ተመልካችና አድናቂ ከኳስ ጥበብ ወደ መንደር ጠበብ ክንውኖች የተለወጡ የስፖርት ውሎዎችን ለመመልከት የተገደደበት ወቅት ሆኗል፡፡ 

የእግር ኳስ ሜዳዎች የስፖርት ማዘውተሪያነታቸው እየቀረ፣ የፖለቲካ መናኸሪያ እየሆኑ፣ እግር ኳስን በአፍንጫዬ ይውጣ የሚል ተመልካች እንዲበራከት እያስገደዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየተባባሰ ለመጣው ለዚህ ችግር፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አጀንዳዎች ፈር ለቀው በየሜዳው መቀንቀን ሲጅምሩ ቀድሞ ለመቆጣጠርና ለመከላከል ብሎም ለማስቀረት የሚያስችል የተደራጀ፣ የካበተ ሥርዓት ባለመኖሩ ሜዳዎች የእግር ኳስ ጥበብ መፈተሻና መወዳደሪያነታቸው እየቀነሰ በአንፃሩ የፖለቲካ መናቆሪያነትና መቆመሪያነት እየሆኑ፣ መንገዱም ክፍት ሆኖላቸዋል በማለት ትችቶችን የሚያቀርቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይደመጣሉ፡፡

ለወትሮው የእግር ኳስ ስፖርት መነታረኪያው የውጤት፣ የችሎታ፣ የክህሎትና የመሳሰለው ጉዳይ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሜዳዎች በአብዛኛው የፖለቲካ ማቀንቀኛ ማሳ እየሆኑ በመምጣታቸው፣ እንደ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ያሉ አንጋፋና የስፖርቱ ባለሙያዎች በአደባባይ፣ ‹‹ስፖርት የለም፡፡ የስፖርቱ ሜዳ የፖለቲካ መነገጃ ሆኗል፤›› እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡

እንደ ገነነ (ሊብሮ) ሁሉ ሌሎች የስፖርቱ ሙያተኞችም፣ ‹‹እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን ከሚያስተዳድረው አካል ምርጫና ለምርጫ ይመጥናሉ ተብለው ከየክልሉ በውክልና የሚላኩ ግለሰቦች የአቅም ጉዳይ መታየት ይኖርበታል፡፡ የክልል ውክልናው ሳይነካ፣ በውክልና የሚላኩ ዕጩዎች ግን ቢያንስ የዓለም እግር ኳስ የሚመራበትን አካሄድ በቅጡ መረዳት የሚችሉ፣ አቅምና ዕውቀት እንዲሁም የአመራር ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ተቃራኒው ነው፤›› በማለት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ አደረጃጀት ጀምሮ የክልል ውክልናን የተላበሰው የምርጫ አካሄድ እስካልተፈተሸ ድረስ ችግሩ ወደፊትም እንደሚከሰት ቅርበቱ ያላቸው ኃላፊዎች ይናራሉ፡፡

ስፖርት ማዘውተሪያዎች ቀደም ሲል ከነበራቸው በተለየ መልኩ አሁን ላይ ሲቀነቀንባቸው የሚደመጡ ጥራጥሬ ፖለቲካዎችና ‹‹ቁረጠው ፍለጠው›› የሚሉ መፈክሮች መናኸሪያ እየሆኑ መምጣታቸው፣ ብሔራዊ ፌደሬሽኑ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነትና የሚወስናቸውን ውሳኔዎች ወደ ሚመለከታቸው አካላት አውርዶ በማስፈጸም ረገድ፣ እንዲህ ያሉት ተጽዕኖዎች እያሽመደመዱት መምጣታቸውን በማውሳት ተቋሙን የሚተቹ አሉ፡፡ ለዚህ ማሳያው ከሰሞኑ በቀናት ልዩነት ሲተላለፉ የነበሩ አጨቃጫቂ ውሳኔዎቹን ተከትሎ በፌዴሬሽኑና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡናና በመቀሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠሩት መካረሮች በአስረጅነት ይቀርባሉ፡፡

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከብዙ ንትርክ በኋላ ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ በሰላም የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በውጤቱም ያለምንም ግብ ተለያይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...