የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር) ከሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሰጥ የሰነበተውን የ10ኛና የ12ኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ፣ በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ሲጎበኙ ከተናገሩት የተወሰደ፡፡ የአማራ መገናኛ ብዙኅን ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር እንዲችሉና አገሪቱ ያለችበትን ደረጃ ለማወቅ፣ የፈተና ሥርዓቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሰጥ በአዲሱ የትምህርትና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ይካተታል ብለዋል፡፡ እየተሠራ ባለው ጥናት መሠረት የስድስተኛ ክፍል ፈተና በክልል ደረጃ፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ደግሞ በአገር አቀፍ መመዘኛ ተዘጋጅተው እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑን ሚኒስትሩ መግለጻቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም የአሥረኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና እንደማይቀጥልና የ12ኛ ክፍል ፈተና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብቻ ሳይሆን የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ስለሚሆን፣ እንዴት መሰጠት እንዳለበት እየተጠና መሆኑን ሚኒስትሩ ማስታወቃቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡