በኑክሌር ውዝግብ እንካ ሰላምታ ሲለዋወጡ የከረሙት ኢራንና አሜሪካ፣ ባለፈው ሳምንት በኦማን ባህረ ሰላጤ በሚጓዙ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሳቢያ፣ ሰላጤውን የጦርነት ድባብ ጭነውበታል፡፡
ኢራን አቋርጣ የነበረውን ኑክሌር የማበልፀግ ፕሮጀክት እንደምትቀጥል ካሳወቀችበት ካለፈው ወር ጀምሮ፣ በባህረ ሰላጤው ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን? የሚል ሥጋት ሰፍኗል፡፡ ሰሞኑን አሜሪካ ወደ ባህረ ሰላጤው 1,000 ወታደሮች መላኳ ደግሞ ቀጣናውን ጦርነት ዋዜማ ውስጥ የሚገኝ አስመስሎታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሁለት ነዳጅ የጫኑ መርከቦች ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ፣ አሜሪካ ኢራን በጥቃቱ ለመሳተፏ መረጃ እንዳላት በመግለጽ ወታደሮቿን ወደ ባህረ ሰላጤው መላኳን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኢራን በጥቃቱ መሳተፏን ለማረጋገጥ በርካታ መረጃዎች የሚቀሩ ቢሆንም፣ መጀመርያ በተገኘው መረጃ ኢራንን የጥቃቱ ተሳታፊ ያደረገችው አሜሪካ፣ ከዚህ ቀደም ከላከችው 1,500 ወታደሮች በተጨማሪ 1,000 ወታደሮቿን መላኳ በቀጣይ ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል አመላክቷል፡፡
በኦማን ባህረ ሰላጤ በነበሩ ሁለት ነዳጅ የጫኑ መርከቦች ላይ ከደረሱት ሁለት ተከታታይ ጥቃቶች ጀርባ ኢራን አለች ቢባልም፣ ኢራን አስተባብላለች፡፡
ከሳዑዲ ዓረቢያና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ በመነሳት ወደ ሲንጋፖርና ታይዋን በማቅናት ላይ በነበሩት የጃፓንና ኖርዌይ ነጃጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ኢራን ለምን ጥቃት ልታደርስ ትችላለች? የሚል ጥያቄ መነሳቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ፓትሪክ ሸናሃን አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የላከችው ኢራን የምታሳየውን ያልተገባ ባህሪ ለመቀልበስ ነው ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2015 ኢራንና አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ኃያላን አገሮች መካከል የተገባውን የኑክሌር ስምምነት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካፈረሱና፣ በኢራን ላይ ጠንካራ የተባለ ማዕቀብ ከጣሉ በኋላ፣ በኢራንና አሜሪካ መካከል የቃላት ጦርነቱ ነግሶ ከርሟል፡፡ ኢራንም የ2015ቱን የኑክሌር ስምምነት በመተው በስምምነቱ ከተፈቀደላት መጠን በላይ ኑክሌር ልታበለጽግ መሆኑን አሳውቃለች፡፡
በኢራንና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ጦርነት እንዳያመራ የምትወተውተው ቻይና፣ ኢራን በ2015 የተደረሰውን የኑክሌር ስምምነት እንዳትጥስ ብትጠይቅም፣ ኢራን ስምምነቱን ገሸሽ አድርጋ የኑክሌር ፕሮግራሟን ዳግም እንደምታስቀጥል፣ ውጤቱም በሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደሚታይ አሳውቃለች፡፡
ከወር በፊትም ቢሆን፣ የኢራን ፋርስና ታስኒም ዜና ኤጀንሲዎች ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን በአራት እጥፍ እንደምታሳድግ የኢራን ኑክሌር ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ከማልቫንዲን ጠቅሰው መዘገባቸው ይታወሳል፡፡
ሚስተር ከማልቫንዲ እንደሚሉት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቶሚክ ተቆጣጣሪ እንዲሁም ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢራን ስለጀመረችው እንቅስቃሴ ያውቃሉ፡፡
በኢራንና አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች አገሮች መካከል ተደርሶ ከነበረው ስምምነት አሜሪካ ራሷን ማግለሏና ለኢራን ተሰጥቶ የነበረው የማዕቀብ እፎይታ መሰረዙ ኢራን የኑክሌር ማበልፀግ ፕሮጀክቷን እንድትቀጥል አንዱ ምክንያት ነው፡፡
በስምምነቱ መሠረት የኢራን ዝቅተኛ የዩራኒየም ማበልፀግ ክምችት ከ300 ኪሎ ግራም እንዳይበልጥ የሚያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ ከ300 ኪሎ ግራም በላይ የዩራኒየም ክምችት ለማኖር እንደሚያመርቱ ሚስተር ከማልቫንዲ አስታውቀዋል፡፡
ኢራን ኃይል ለማመንጨት 3.67 በመቶ ዩራኒየም ማበልፀግ የተፈቀደላት ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2015 የተደረሰውን ስምምነት ቀስ በቀስ እያፈረሰች እንደምትመጣ አስታውቃለች፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን የስምምነቱ አጋር የሆኑት እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመንና ሩሲያ አሜሪካ የጣለችውን ዕገዳ እንድታነሳ ማድረግ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡
የኢራን አካሄድ ጥቅሜን ይጎዳል ያለችው አሜሪካ፣ ኢራንን ለመጠርነፍ ወታደሮቿን ወደመካከለኛው ምሥራቅ መላክ ከጀመረች ሰንብታለች፡፡ ሚስተር ሻናሃን እንደሚሉት፣ የአሜሪካ ወታደሮች ወደመካከለኛው ምሥራቅ መላክ ከኢራን ጦርነት ለመግጠም ሳይሆን፣ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ነው፡፡
‹‹አሜሪካ ከኢራን ጋር ግጭት መፍጠር አትፈልግም፡፡ ሆኖም ወታደር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተላከው በሥፍራው የሚገኙ ወታደሮችና በአካባቢው ሰላም ለማስፈን የተሰማሩ ኃይሎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ለመጠበቅና የእጅ አዙር ጦርነት ማድረግ የሚፈልጉትን ለማስጠንቀቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በአካባቢው የተሰማራው ወታደር የኢራንን አካሄድ በየጊዜው ይቆጣጠራል ያሉት ምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ተጨማሪ የተላኩት 1,000 ወታደሮች የትኛው ሥፍራ እንደሚመደቡ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡