Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

መረጃን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የማድረግ ጉዞ

ጋዜጠኛ ገድለሚካኤል አበበ የብሥራት ፕሮሞሽን ፒኤልሲ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ዓይነ ስውር ናቸው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በምዕራብ ሸዋ ባኮ ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አዲስ አበባ ከተማ ከተከታተሉ በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ በብሥራት ፕሮሞሽን ፒኤልሲና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓይን ብርሃንዎን ያጡት መቼ ነው?

አቶ ገድለሚካኤል፡- ዓይነ ስውር ሆኜ ነው የተወለድኩት፡፡ የዓይን ስፔሻሊስት ዶክተር ጳውሎስ ቀንአ አንዳንዴ በተፈጥሮ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሊመጣ እንደሚችል ለአባቴ እንደነገሩአቸው ተገልጾልኛል፡፡ የተወለድኩትም በወላጆቼ ዘንድ ወንድ ልጅ በጣም ይፈለግ በነበረበት ወቅት ስለሆነ ከፍ ያለ እንክብካቤ ይደረግልኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎ ጋዜጠኛ ናቸው ይባላል?

አቶ ገድለሚካኤል፡- አዎ ጋዜጠኛ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አየሠራች ትገኛለች፡፡ ከዚህም ሌላ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥም የምልክት ቋንቋ ታስተረጉማለች፡፡ ይህም ሆኖ ግን አካል ጉዳተኛ አይደለችም፡፡ በጆርናሊዝም ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን በምልክት ቋንቋ ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪ አግኝታለች፡፡ አሁን ባቋቋምኩት ኩባንያ ውስጥ የትርጉም ሥራ አገልግሎትን እየመራች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎ በሥራ ምን ያህል ከጎንዎ ይቆማሉ?

አቶ ገድለሚካኤል፡- በጣም ትረዳኛለች፡፡ ከተጋባን ሰባት ዓመት ሆኖናል፡፡ እንደ ወንድምና እህት፣ እንደ ባልና እንደ ሚስት ተከባብረን፣ ተጋግዘን፣ ተሳስበንና ተዋደን ነው የምንኖረው፡፡ እጅግ በፍቅር ነው እየኖርን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተማሪ ሆነው ፍላጎትዎ ምን ነበር?

አቶ ገድለሚካኤል፡- ተማሪ እያለሁ ፍላጎቴ ሙዚቃ መሥራት ነበር፡፡ በፍላጎቴም መሠረት ድምጻዊና መድረክ አስተዋዋቂ ነበርኩ፡፡ በዚህም የተለያዩ ቦታዎች ለጥቂት ዓመታት ሠርቼያለሁ፡፡ በተለይ አልበም ለመሥራት ያልሞከርኩት ጥረት የለም፡፡ አሁን ወዳለሁበት ሥራ የገፋፉኝም ከፍ ብሎ በዝርዝር የገለጽኳቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው ለማለት ይቸላል፡፡ እንዳው በአጠቃላይ አሁን ላለሁበት ደረጃ ብዙ ጊዜ እየተነሳሁ ወድቄያለሁ፡፡ ብዙ ለፍቻለሁ፡፡ በርካታ ጥረቶችንም አድርጌያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የነበረብዎትን ውጣ ውረድ ቢያብራሩልን፡፡

አቶ ገድለሚካኤል፡- ከድምፃዊነት ባሻገር ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት እያደረብኝ መጣ፡፡ በዛን ጊዜ አንድ ለናቱ የነበረው የኢትዮጵያ ሬድዮ ጣቢያ ነበር፡፡ የልጆች ፕሮግራም ለመሥራት ወደ ጣቢያው ጎራ አልኩ፡፡ ስም መጥቀሱ ባያስፈልገኝም በወቅቱ የነበረች አንዲት ኃላፊ ዓይነ ስውር ይህን መሥራት አይችልም፡፡ አርፈህ ትምህርትህን ብቻ ተማር፡፡ በተረፈ ሙዚቃ ለመሥራት ወደ ክለብ ስትሄድ በኋላ አንተን ማን ይመልስሃል አለችኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አነጋገር ተስፋ አስቆረጥዎት ወይስ ፍላጎትዎን ለማሳካት እንቅስቃሴዎን ቀጠሉ?

አቶ ገድለሚካኤል፡- በአንድ አጋጣሚ ሬዲዮ ፋና የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለመሥራት ፕሮፖዛል እንዲገባ ጠየቀ፡፡ በዚህም ምክንያት እኔ መጀመርያ ፈቃድ አውጥቼ መሥራት አለብኝ ብዬ ወስንኩ፡፡ ፈቃዴንም አወጣሁ፡፡ ሬድዮ ፋናም ‹‹አንድ ድምጽ›› የሚባል ሳምንታዊ ፕሮግራም እንድሠራ ፈቀደልኝ፡፡ ይህንንም ሥራዬን የተቀላጠፈና ሕጋዊ ለማድረግም እንዲያስችለኝ ‹‹ብሥራት ፕሮሞሽን›› የሚባል ተቋም አቋቋምኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ሳምንታዊው ፕሮግራም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ብቻ ያተኮረ ነበር?

አቶ ገድለሚካኤል፡- አዎ! የአካል ጉዳተኞችን መገለል ለመቀነስና ሌሎችም ማኅበረሰቦች በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ለማቃናት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት ፕሮግራም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ያተኮረ የፕሮሞሽን ሥራ በሬዲዮ በመሥራት ረገድ እኛ የመጀመርያዎቹ ነን ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የሬዲዮ ፕሮግራም ስትሠሩ በሒደት ያጋጠማችሁ ችግር ወይም የተገነዘባችሁት ክስተት ይኖር ይሆን?

አቶ ገድለሚካኤል፡- የሬዲዮ ፕሮግራም ስንሠራ የተለያዩ ችግሮችን አስተዋልን፡፡ አንደኛው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ፕሮግራም ለመሥራት ስፖንሰርሺፕ ማግኘቱ አዳጋች ሆኖ መገኘቱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ችግር ደግሞ አንዳንድ ሰዎችና ራሳችን ጭምር አካል ጉዳተኞች የሚገለገሉባቸውን ልዩ ልዩ ዓይነት መሣሪያዎች ከየት ማግኘት እንዳለባቸው አለማወቃቸውን ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመወጣት አንድ ሌላ መንገድ መፍጠር ነበረብን፡፡ ይኼውም የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ልዩ ዓይነት ማቴሪያሎችን አስመጥቶ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ አቅምን ባገናዘበና በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥን እንደ አማራጭ ወሰድን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ብሥራት ፕሮሞሽን ሌላ እህት ኩባንያ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የማቋቋሙ ጉዳይ ዕውን ሆነ፡፡ እህት ኩባንያውም ብሥራት ፕሮሞሽን ፒኤልሲ ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሥራት ፕሮሞሽን ፒኤልሲ ከተቋቋመ ስንት ዓመት ይሆነዋል? ስንት የሥራ ዘርፎች አሉት?

አቶ ገድለሚካኤል፡- ብሥራት ፕሮሞሽን ፒኤልሲ ከተቋቋመ 12 ዓመት ሆኖታል፡፡ በአምስት ዋና ዋና ዘርፎች ዙሪያ የተደራጀ ነው፡፡ ከሥራ ዘርፎቹም መካከል አንደኛው ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት የሚውሉ ማቴሪያሎችን ከውጭ ማስመጣት፣ ለተለያዩ ተቋማት የምልክት ቋንቋ ትርጉም መሥራት፣ በማኅበራዊና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ፕሮሞሽን፣ ሥልጠናና የማማከር አገልግሎት መስጠት፣ የህትመት ሥራ ማከናወን፡፡ ይህም ማለት ለተለያዩ ኩባንያዎች ዲዛይኖች፣ የተለያዩ ቲሸርቶች፣ መጽሔቶች፣ ብሮሸሮች መሥራት ናቸው፡፡ የፕሮሞሽኑን ሥራ የሚሠራው በአዲስ አበባ በብሥራት ኤፍኤም ሬዲዮ 101.1፣ ሁልጊዜ ሐሙስ ከምሽቱ ሁለት እስከ ሦስት ሰዓት እንዲሁም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሬዲዮና ቴሌቪዥን 100.9 ኤፍኤም ቅዳሜ ከቀኑ ስምንት እስከ ዘጠኝ ነው፡፡ በእያንዳንዱም ዘርፍ ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ሠራተኞች በቋሚነትና በጊዜያዊነት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገር የምታስመጧቸው ማቴሪያሎችን ዝርዝር ሊገልጹልን ይችላሉ?

አቶ ገድለሚካኤል፡- ለዓይነ ስውራን የብሬል መጻፊያ መሣሪያዎች፣ የብሬል ወረቀት፣ ዝቅተኛ የማየት ችግር ላለባቸው ወገኖች ደግሞ አጉልቶ ማሳየት የሚችል መሣሪያ (ማግኒፋየር)፣ ለእግር ጉዳተኞች የሚውሉ የተለያየ መጠንና ደረጃ ያላቸውን ክራንችና ዊልቸር፣ የመስማት መሣሪያ፣ የምልክት ቋንቋና የብሬል መማሪያ መጻሕፍት፣ በአጠቃላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግሉ ሌሎችም የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችን ሁሉ እያስመጣን አቅምን ባገናዘበና ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ለተጠቃሚዎች እንሸጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሬዲዮ ለምታስተላልፉት ፕሮግራም ከአካል ጉዳተኞችም ሆነ ከሌላው ማኅበረሰብ የምታገኙት ግብረ መልስ ምን ይመስላል?

አቶ ገድለሚካኤል፡- የእኛ ድርጅት በአካል ጉዳተኝነትና ጉዳተኞች ላይ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮና ብርሃን ለሕፃናት ከተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ ጉዳዮችንና ለችግር የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሉባቸው ቦታዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶች እንሠራለን፡፡ ለዚህም የሚውል አንድ ትልቅ ስቱዲዮ አቋቁመናል፡፡ ለሚዲያ ባለሙያዎችም ሐዋሳና አዲስ አበባ ውስጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥተናል፣ ወደፊትም እንሰጣለን፡፡ የኦዲዮና የኦዲቪዡዋል ዶክመንተሪ ፕሮግራሞችን እየሠራን ለተቋማት እናቀርባለን፡፡ ይህንንም ሥራ የሚከታተል የኦዲቪዡዋል ዲፓርትመንት አለን፡፡ በተረፈ ግብረ መልስ በተለያየ መልኩ ይገለጻል፡፡ እኛ በሬዲዮ ፋና ፕሮግራም መሥራት ከጀመርን በኋላ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚሠሩ ሌሎች አራት ድርጅቶች ተፈጠሩ፡፡ የድርጅቶቹ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ ወደ ስድስት ከፍ ብሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው የምናገኘው ግብረ መልስ ውጤታማ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ግንባር ቀደም መሆናችንንም የሚያመለክት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሬዲዮ ፕሮግራም ከመሥራታችሁ በፊት ይህ ዓይነቱን ሥራ የሚያከናውን ሌላ አካል አልነበረም ማለት ይቻላል? ከሬዲዮ ፋና እንዴት ለቀቃችሁ?

አቶ ገድለሚካኤል፡- ከእኛ በፊት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ብቻ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በየአሥራ አምስት ቀን ለ15 ደቂቃ ያህል ገንዘብ እየከፈለ በአካል ጉዳተኞችና ጉዳቶች ዙሪያ የፕሮሞሽን ሥራ ያከናውን ነበር፡፡ በተረፈ የእኛ ድርጅት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለመሥራት ለሦስት ዓመት ያህል ለፍተን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ከሬዲዮ ፋና የወጣነውም የምታስመጡት የገበያ ደረጃ በቂ አይደለም ተብለን ነው፡፡ ሬዲዮ ጣቢያዎች ገቢ ካላስገኘላቸው የመቀበል ፍላጎት የላቸውም፡፡ እኛ ግን የራሳችንን ድርጅት አቋቁመን በርትተን በመሥራታችን የተነሳ ፕሮግራማችንን የወደዱ ስፖንሰሮች በብዛት ወደ እኛ እየመጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአካል ጉዳተኛና ጉዳተኝነት ዙሪያ ያተኮሩ ብዙዎች ፕሮግራሞች በአካል ጉዳተኞች ብቻ ሲሠሩ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ ገድለሚካኤል፡- እንዲህ ዓይነቱ ፕሮግራም አካል ጉዳተኞች ብቻ መሥራት አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ ቢቻል አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ፕሮግራም ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ ይህን ፕሮግራም ለመሥራት ዕውቀት፣ ብቃት፣ ማንበብና መረዳት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን የሚያሟሉ አካል ጉዳት የሌለባቸው ወገኖች ሊሠሩበት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ ሚዲያዎች በአካል ጉዳተኞችና ለተለያዩ ችግሮች በተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሽፋን እንዲሰጡ የብሮድካስት ፖሊሲ ያስገድዳል፡፡ ምን ያህል ተግባራዊ እየሆነ ነው የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁን ቢገልጹልን፡፡

አቶ ገድለሚካኤል፡- ፊት ለፊታችን ያለው ምርጫ ላይ ለሁሉም አካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት ጉዳዩ ከሚመለከተው ተቋም ጋር በመገናኘት ለመሥራት የሚያስችል እንቅስቃሴ  ጀምረናል፡፡ እያንዳንዱ አካል ጉዳተኛ መብቱን እንዲጠቀም ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ተሻሽሎ የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅም በመብት ላይ እንድንሠራ ይፈቅድልናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ የተባበራችሁ አካል አለ?

አቶ ገድሚካኤል፡- አዎ! የብሥራት ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መንግሥቱ ላቅ ያለ ዕገዛና ትብብር እንዳደረጉልን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ባቋቋሙት ሬዲዮ ጣቢያ በሳምንት አንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል፣ በዓመት በዓል ሰሞን ደግሞ በሳምንት ለአምስት ሰዓት ያህል ፕሮግራማችንን አየር ላይ እንድናውል ፈቅደውልናል፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹እግር ኳስን በሬዲዮ›› በሚለው ፕሮግራማቸው ዓይነ ስውራን ዓለም አቀፍም ሆነ አገር አቀፍ እግር ኳስ ውድድሮችን በጆሮአቸው በመስማት እንዲዝናኑ የማድረግ ሥራ ማከናወናቸው በአካል ጉዳተኞች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ሊያተርፉ ችለዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...