[ክቡር ሚኒስትሩ መኪናቸው ውስጥ ገብተው ወደ ቢሮ ሊሄዱ ነው]
- ወደ ቢሮ እንሂድ፡፡
- እ…
- ወደ ቢሮ ውሰደኝ፡፡
- እ…
- ምን ሆነሃል?
- እ…
- ተኝተሃል እንዴ?
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ማታ የት ነው የነበርከው?
- ቤቴ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ መኪና ውስጥ ለምን ትተኛለህ?
- እርቦኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር?
- ምን እያልክ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ቤት መብራት ብቻ ሳይሆን ምግብም በፈረቃ ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ይኸው ቁርስ ከበላሁ ሦስተኛ ቀኔ ነው፡፡
- አሁን ፆም አለ እንዴ?
- ፆሙ ከገባ እኮ ቆየ፡፡
- የምን ፆም ነው፡፡
- መንግሥት ያዘዘው ነዋ፡፡
- አንተ መንግሥትና ሃይማኖት እንደሚለያዩ አታውቅም እንዴ?
- ወረቀት ላይ ነዋ የሚለያዩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አልገባኝም፡፡
- አሁን እኮ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነዋል፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር የአገራችን ፖለቲካ እያስጠላ መጥቷል፡፡
- እንዴት?
- ሁሉም ቦታ የፖለቲከኛ መድረክ ሆኗል፡፡
- እ…
- የፖለቲካ መሪዎቻችን የቤተ ክርስቲያን ቆብና ካባ ለብሰው ጳጳስ መምሰላቸው ሲያስገርመን ነበር፡፡
- ምን አልከኝ?
- እሱ አልበቃ ብሏቸው መስጊድም ገብተው ኢማም መሆን ሲያምራቸው ተመልክተናል፡፡
- ያው መቻቻልን ለማስተማር እኮ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው አላሉኝም?
- እሱማ ትክክል ነህ፡፡
- ስለዚህ መንግሥት ድንበር ዘሎ እየገባ ነው፡፡
- የት ነው የገባው?
- ፈንጂ ወረዳ፡፡
- ፖለቲከኛ ሆነሃል ልበል?
- ስነግርዎት አሁን ፖለቲካ ያልገባበት የት አለ ብለው ነው?
- እ…
- ይኸው ብሎ ብሎ ስፖርታችንም ፖለቲካ ሆኗል አይደል እንዴ?
- ምን ታደርገዋልህ?
- ክቡር ሚኒስትር ይታሰብበት፡፡
- ለመሆኑ መንግሥት የምን ፆም ነው ያወጀው?
- የኑሮ ውድነት የሚባል ነዋ፡፡
- እ…
- ይኸው ቁርስ ዛሬ ከበላሁ በሦስተኛው ቀን ነው የሚደርሰኝ፡፡
- ለምን?
- በመሀል ባሉት ቀናት ሚስቴና ልጄ ናቸዋ የሚበሉት፡፡
- ወይ ጉድ፡፡
- ስለዚህ ዕድሜ ለመንግሥት ኑሯችንንም በፈረቃ አድርጎልናል፡፡
- ቀልደኛ ነህ እባክህ?
- ለነገሩ እርስዎ ምንም አይገባዎትም፡፡
- ምኑ ነው የማይገባኝ?
- የሕዝቡ ችግር ነዋ፡፡
- እ…
- ክቡር ሚኒስትር ችግሩ እንዲገባችሁ አንዳንዴ ምን እንደምመኝ ያውቃሉ?
- ምንድነው የምትመኘው?
- ከሕዝቡ ጋር…
- እ…
- ቤት እንድትቀያየሩ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- የት ነው የጠፋኸው?
- መቼ ፈልገውኝ ያውቃሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ሪፖርት ካቀረብክልኝ ስንት ጊዜህ ነው?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይተው፡፡
- እንዴት?
- ሪፖርት መቼ ተቋርጦብዎት ያውቃል?
- የት አለና?
- ይኸው ፊትዎ የተከመረው የሪፖርት መዓት ምንድነው?
- እንዴት አላየሁትም ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትር መቼ ቢሮ ይውሉና፡፡
- እ…
- ከባለሀብትና ከደላላ ጋር አይደል እንዴ የሚውሉት?
- ምን አልከኝ?
- ለማንኛውም ምን ፈልገው ነው?
- አገሪቱ እንዴት ነች?
- አገሪቱማ ታማለች፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ነው፡፡
- እኮ ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር የኑሮ ውድነቱ ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል፡፡
- እኛ እኮ ፖለቲካው ላይ ስናተኩር ኢኮኖሚው ከእጃችን እያፈተለከ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በኋላ ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
- እንዴት?
- ፖለቲካው ያለ ኢኮኖሚው እንዲሁ ድካም ነዋ፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- መንግሥት ገበያውን ማረጋጋት አለበት፡፡
- እኮ በምን?
- ክቡር ሚኒስትር የዋጋ ንረቱ እኮ ሰው ሠራሽ ነው፡፡
- ሰው ሠራሽ ስትል?
- በቃ ስግብግብ ነጋዴዎች ያላግባብ ለመክበር ብለው ሕዝቡ ላይ ዋጋ እየጨመሩበት ነው፡፡
- ታዲያ ነፃ ገበያ ብለን ምን ይደረግ?
- ክቡር ሚኒስትር ነፃ ገበያም ቢሆን ሕገወጥ ድርጊቶችን መንግሥት ሊያርም ይገባል፡፡
- እሱስ ልክ ነህ፡፡
- የዋጋ ንረቱ የተከሰተው ነጋዴዎች ያላግባብ ዕቃ እየደበቁ ስለሆነ ነው፡፡
- የት ነው የሚደብቁት?
- መጋዘናቸው ውስጥ ነዋ፡፡
- እነዚህ ላይማ ዕርምጃ መውሰድ ነዋ፡፡
- ምን ዓይነት ዕርምጃ?
- ማሸግ ነዋ፡፡
- ምን ብለን?
- የለውጡ አደናቃፊዎች!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ነጋዴ ጋ ደወሉ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰላም ይንሳህ፡፡
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አገር ተበጥብጦ አንተ በሰላም መኖር የምትችል ይመስልሃል?
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አገር ለምን ትበጠብጣለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ተሳስተው ደውለው ነው?
- አልተሳሳትኩም፡፡
- ምናልባት አክቲቪስት ጋ የደወሉ መስሎዎት ከሆነ ብዬ ነው?
- ከእናንተማ አክቲቪስቶቹ ይሻላሉ፡፡
- እንዴት?
- እነሱ ቢያንስ ሕዝቡን የሚበጠብጡት በወሬ ነው፡፡
- እኛስ?
- እናንተማ በሆዱ ነው የመጣችሁበት፡፡
- እ…
- ስማ የምታደርጉትን ሁሉንም ነገር እናውቃለን፡፡
- ተረጋጉ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ አገር እየበጠበጣችሁ እንዴት እንረጋጋ?
- ምን አድርገን ነው የበጠበጥነው?
- ይኸው አላግባብ ዋጋ ሕዝቡ ላይ እየጨመራችሁ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ የነፃ ገበያ መርህ እኮ ነው የምትከተለው፡፡
- ቢሆንስ ታዲያ?
- ስለዚህ ሕዝቡ ከፈለገ ይገዛል ካልፈለገ ይተዋላ፡፡
- እንደዚህ ዓይነት ቀልድ ለማንም አያዋጣም፡፡
- ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ያደረሳችሁ የእኛ ሥርዓት መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
- እሱ እንኳን እዚህ የደረስነው በቀድሞው ሥርዓት ነው፡፡
- አሃ አሁን ይኼ በቀል መሆኑ ነው?
- የምን በቀል?
- የለውጡ አደናቃፊ መሆንህን በሚገባ አውቃለሁ፡፡
- ምንድነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
- ምንም ብትመኘው ወደ ቀድሞው ሥርዓት አንመለስም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ያልገባዎት ነገር ስላለ እኮ ነው፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- አሁን ዶላር ማግኘት ተስኖኝ ከብላክ ማርኬት ነው የምገዛው፡፡
- ምን ይጠበስ ታዲያ?
- ስለዚህ ዋጋ የጨመርኩት ስለማያዋጣኝ ነዋ፡፡
- ስማ ዋጋማ የጨመርከው ስለማያዋጣህ ሳይሆን ሆዳም ስለሆንክ ነው፡፡
- አይሳደቡ እንጂ፡፡
- የሕዝቡን ሰላም በሲስተም እየበጠበጡ በሰላም መኖር አይቻልም፡፡
- ምን ላድርግ እኔ?
- ምን እንደምተደርግ ታውቃለህ?
- ንገሩኝ?
- የዕቃዎችህን ዋጋ ቀንስ፡፡
- እሱማ አይሆንም፡፡
- እንግዲያው ምን እንደማደርግ ታውቃለህ?
- ምን ያደርጋሉ?
- ትወረሳለህ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ሕዝቡ ተማሯል አሉ እባክሽ?
- በምን?
- በኑሮ ውድነቱ ነዋ፡፡
- እሱንማ አታንሳው፡፡
- እንዴት?
- የሚበላው ያጣው ስፍር ቁጥር የለውም ስልህ?
- በጣም አሳሳቢ ነው፡፡
- የሚበላው ያጣ ሕዝብ ደግሞ መሪውን ይበላል ተብሏል፡፡
- እ…
- ምን እ… ትላለህ አንድ ቀን ልትበላ ትችላለህ፡፡
- ማን ነው የሚበላኝ?
- ሕዝቡ፡፡
- ነጋዴዎች ሆን ብለው ነው አሉ፡፡
- ምን የሚያደርጉት?
- ሕዝቡ ላይ ዋጋ የሚጨምሩት፡፡
- እሱማ ግልጽ ነው፡፡
- እንደዚያ ከሆነ ደግሞ እንዳልሽው ለእኛም አደጋ አለው፡፡
- በሚገባ እንጂ፡፡
- ስለዚህ አፋጣኝ የሆነ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- በቃ በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡
- ምን ዓይነት ዕርምጃ?
- መውረስ ነዋ፡፡
- ከዚያስ?
- ከዚያማ እኛው እናከፋፍለዋለን፡፡
- ምኑን?
- ዕቃውን ነዋ፡፡
- እንዴት አድርገን?
- ራሳችን እንሆናለና፡፡
- ምን?
- ነጋዴ!