Thursday, February 2, 2023

ኢትዮጵያ ድሮና ዘንድሮ በቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮች ዕይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ምሥራቅ አፍሪካን በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን በሚመለከቱ የተለያዩ ውይይቶች ላይ፣ በኢትዮጵያ እየተደረገ ስላለው ለውጥ በአንድም በሌላም መንገድ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ አልፎ ተርፎም ኢትዮጵያንና እየተካሄደ ባለው ለውጥ ላይ ብቻ ያተኮሩ ውይይቶች፣ በተለያዩ ሥፍራዎችና ጊዜዎች ሲደረጉ ተስተውሏል፡፡ እነዚህ ውይይቶችም ከአዲስ አበባ እስከ ዋሽንግተን ዲሲ የዘለቁ ሆነዋል፡፡

ከእነዚህና መሰል ውይይቶች አንዱ የሆነውና ሰሞኑን በአሜሪካ የሰላም ተቋም የተደረገው የሁለት ሰዓታት ውይይት፣ በዓይነቱ ለየት ያለና አራት የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮችን በአንድ ላይ ያገናኘ ነበር፡፡ ከኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን መጀመርያ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጦርነት አንስቶ፣ እስከ ዘመነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድረስ በመዝለቅና የወደፊቱን በመገመት የተተነተነበት ውይይት ተደርጓል፡፡ በአሜሪካ የሰላም ተቋም ባለሙያና የበርካታ መጻሕፍት ደራሲ ዓሊ ሸርጂ አወያይነት በተወያይነት የተቀመጡት አምባሳደሮች ዴቪድ ሺን (እ.ኤ.አ. ከጁላይ 1996 እስከ ኦገስት 1999 በኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ)፣ አምባሳደር ኦሬሊያ ብራዚል (እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 2002 እስከ ሴፕቴምበር 2005 በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ)፣ አምባሳደር ማርክ ባስ (በኢትዮጵያ ከደርግ መውደቅ በኋላ የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ የነበሩ) እና ዶናልድ ቡዝ (በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ) ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን የብሔር ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫና እያደገ የመጣውን የወጣቶች ቁጥርንና የሥራ ፈጠራ ፈተናዎችን በተመለከተ ሰፋፊ ምልከታዎችን አካፍለዋል፡፡

በማስቀደም ኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ከመመደባቸው አስቀድሞ ቢያውቁት መልካም ነበር ስለሚሉት ጉዳይ የተጠየቁት አምባሳደር ቡዝ፣ በኢትዮጵያ ያለውንና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለየት ያለውን የብሔር ማንነት ጥልቀት ቢረዱ ይመኙ እንደነበር በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ክልሎች እንደ አንድ አገር እንዲሆኑና በዚህም ሳቢያ በተፈጠረ መከፋፈል አንዱ ሲያገኝ ሌላው ያጣል የሚል የዜሮ ድምር ፖለቲካን እንደፈጠረ አውስተዋል፡፡

አምባሳደር ብራዚል በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸውን የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት አውቀው ቢሆን እንደሚመኙ የገለጹ ሲሆን፣ አምባሳደር ሺን በበኩላቸው አንዱ በሰጥቶ መቀበል እምነት ይቅርብኝ የሚለው ጉዳይ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ እምብዛም እንደማይታይ በማውሳት፣ ይኼንን ከመቀበል በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም በማለትም ገልጸውታል፡፡

እሳቸው አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ከወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳልነበራቸው ያስታወቁት አምባሳደር ቡዝ፣ ሆኖም አቶ መለስ በመንግሥት ውስጥ ካሉ ኃላፊዎች ሁሉ በቀጥታ ሄደው ጥያቄ በማቅረብ ይሆናል ወይም አይሆንም የሚል ቀጥተኛ ምላሽ መስጠት የሚችሉ፣ ከመልሶቹ በኋላም  የተባሉት ጉዳዮች ይሆናሉ ወይስ አይሆኑም ተብለው የማይጠረጠሩ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱም በተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች አዎን ወይም አይሆንም የሚሉ ምላሾች ቢሰጡም፣ ተወያይተን እንመለሳለን ከተባለም አሉታዊ ምላሽ አድርጎ መውሰድ እንደሚያስፈልግ መገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአቶ መለስ በኋላ በዚህ ሁኔታ ላይ የነበረ መሪ በኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም [ደሳለኝ] በእርግጠኝነት እንደዚያ አልነበሩም፡፡ በብዛት በሌሎቹ የኢሕአዴግ አባላት የምሕረት ጥላ ሥር ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም ቢሆኑ እዚያ ደረጃ ደርሰዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ የላቀ ክብር ቢኖራቸውም፣ እንደ አቶ መለስ ያለ ሁኔታ ላይ ግን አይደሉም፤›› በማለትም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የውሳኔ አሳማኝ ሒደትና መጓተትን በተመለከተ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ጃፓናውያንን ይመስሉኛል፤›› በማለት የጃፓን ቆይታቸውንም አጣቅሰው የተናገሩት አምባሳደር ብራዚል፣ ውሳኔዎች የጋራ መግባባትን በመለየታቸውና ሰፊ ውይይት ስለሚደረግባቸው በእጅጉ ይዘገያሉ ብለዋል፡፡ ውሳኔ ከተላለፈ ወዲያ ግን ተግባራት ይፈጥኑ ነበር በማለት ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ሒደት ምቾት እንጂ ሌላ አሉታዊ ስሜት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በ1997 ግንቦት ወር የተደረገው ምርጫ ኢሕአዴግን እንዳስደነገጠውና መንግሥት ከደርግ መውደቅ በኋላ ሊያሳካ እየሠራ ያለውን ጉዳይ ሕዝቡ በመረዳቱ የሰጠውን ድምፅ ተከትሎ፣ ሁሉንም ምኅዳሮች የማጥበብ ዝንባሌ እንዲያሳይ አድርጓል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የውጭ ዜጎችን በጥርጣሬ ያያሉ በማለት አቶ መለስን የገለጹት አምባሳደር ቡዝ በበኩላቸው፣ መለስ ቀጥታ ተናጋሪና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማተኮር የሚያዘወትሩ እንደሆኑም ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በብዛት እሳቸው የሚወዱትን ዓይነት ለውጥ እስረኞችን በመፍታት፣ ከኤርትራ ጋር ዕርቅ በማውረድና የሚዲያ ነፃነትን ለማምጣት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመጥቀስ፣ ምንም እንኳን ይኼንን በማየት፣ ‹‹ለመደገፍ ብንቀርብም ከውጭ የሚቀበሉት ምክር መጠን ውስን በመሆኑ መጠነኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡፡ ‹‹ይሰማሉ ግን በእርግጠኝነት በራሳቸው መንገድ ነው የሚሠሩት፤›› ሲሉም በችግሮች ላይ መስማማት ላይ መድረስ ቢቻልም እንኳ፣ መፍትሔ ላይ ግን የራሳቸውን መንገድ ይከተላሉ ሲሉ የኢትዮጵያን መንግሥት ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) በሚካሄድበት ጊዜ በአምባሳደርነት እንዳገለገሉና በወቅቱ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እንደነበር የጠቆሙት አምባሳደር ባስ በበኩላቸው፣ ምርጫ ሒደት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው እንዲሠሩት ሊተውላቸው እንደሚገባና ቀጣዩን ምርጫ በባለቤትነት ሊያካሂዱት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ምርጫውም ነፃና ገለልተኛ፣ እንዲሁም ተዓማኒ እንዲሆን ማበረታታት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

‹‹በሒደቱ ላይ ነው መሥራት ያለብን፡፡ እኛ ሄደን ይኼንን ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ አድርጉ ብንል ቅር ይሰኛሉ፡፡ ይኼ እምብዛም የሚጠቅም አይሆንም፤›› በማለትም ያሳስባሉ፡፡

እንኳን ‹‹ከሁለት ሺሕ በላይ ዓመታት ታሪክ ውስጥ አንድ ምርጫ ያልተደረገባት ኢትዮጵያ ትቅርና የትም ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ቀላል አይደለም፡፡ እኔ እስከሚገባኝ በአሜሪካ እንኳን ነፃና ገለልተኛ ምርጫ የለንም፤›› ሲሉም ያበክራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እሳቸው ሊበራል ዴሞክራሲ ብለው በሚፈርጁት መንገድ መልካም ግስጋሴ እያደረጉ እንዳሉ አውስተው ሲያደንቁ አምባሳደር ሺን፣ የአገሪቱን ተደራራቢ ችግሮችን ለመወጣት ግን ከባድ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ ይኼም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወቅቱ ፈተና እንደሆነ የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ የምርጫ ጣቢያ ለማደራጀት የሚያግዘው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን ማድረግ ባልተቻለበት ሁኔታ፣ ቀጣዩን ምርጫ ማድረግ ይቻላል ብለው እንደማያምኑና አሳማኝ ምክንያትም እንደማይሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ በርካታ ነገሮች መቀየራቸውን የጠቆሙት ደግሞ አምባሳደር ብራዚል ሲሆኑ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ምን ያህል ዕድገት እንዳሳየ መገመት ግን አዳጋች እንዳሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ሆኖም ለእንዲህ ዓይነቱ ምርጫና የጊዜ መለዋወጥ ብሎም አካታችነት ዕድገት ማሳየት ቀላል እንደማይሆን የአሜሪካን የ240 ዓመታት ታሪክ፣ የሴቶችና የጥቁሮችን መብት በተመለከተ ያሉ ችግሮችን አንስተው አብነት ያደርጋሉ፡፡ አሜሪካ የሴቶችን መብት ለማስከበር ከ100 ዓመታት በላይ እንደፈጀባትና የጥቁሮችን መብት በሙሉ ደረጃ ለማክበር አሁንም ድረስ እንዳልቻለች በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ችግኞችን ውኃ በማጠጣት ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንድታሳድግ እንደሚፈልጉ በመናገር፣ ከውጭ ሊጫንባቸው አይገባም ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡

ከአሁን ቀደም በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ተመሳሳይ ድንገቴ ክስተት እንዳይገጥም ለሁሉም ጉዳይ ኢሕአዴግን በእጀጉ ተጠቅመዋል በማለት፣ ሥልጣን ላይ መቆያ ዋነኛ መሣሪያ በእጃቸው ሳለ ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የሆኑ የቀበሌ ወይም የወረዳ መሪዎች የትኞቹ ይሆኑ በማለትም ቡዝ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ሆኖም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢሕአዴግን እንዲዳከም በማድረጋቸውና ሊመኩበት የሚችሉት መንግሥታዊ መሠረት የሌላቸው በመሆኑ በሁለት ውጥረቶች መካከል እንደሚገኙ በመጠቆም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲውን እንደ ሥልጣን መሣሪያም እየተጠቀሙበት አይደለም ይላሉ፡፡

ከምርጫ 97 በተለየ አሁን ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ ሰፊ ተጠቃሚነት፣ የተሻለ የተማረ ሰው ብሎም የሕዝብ ብዛት ቀጣዩን ምርጫ የተለየ መልክ ሊሰጡ የሚችሉ ለውጦች መሆናቸውን አምባሳደር ብራዚል አክለዋል፡፡

ይኼንን በማጠናከርም፣ ‹‹እኔ በነበርኩባቸው ጊዜያት የገጠሩ አካባቢ ከከተማው ጋር አነስተኛ ግንኙነት የነበረው በመሆኑ፣ የአካባቢ ባለሥልጣናት ጠንካራ ኃይል እንዲኖራቸው አግዟል፡፡ ይኼ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ መምጣትና የተማረ ሰው በመበራከቱ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን እኔ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ በእጅጉ የተለየች ናት፤›› ሲሉ አምባሳደር ባስ ያስገነዝባሉ፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉትና ወደ ምዕራቡ የሊበራል ዴሞክራሲ የሚያዘነብሉ ለውጦችን ተከትሎ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጡ፣ በተለይ እየተካረረ የመጣውን የብሔር ፖለቲካ በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝሙን ስታዋቅር አነስተኛ ጉዳት ሊያስከትል የሚችለው የብሔር መዋቅር መከተሏን በመጠቆም፣ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ሊመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ይኼንን መፍታት ካልተቻለ ምርጫ ማካሄድን አዳጋች እንደሚያደርግ፣ የፀጥታ ሁኔታዎችን እያባባሰ እንደሚሄድና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ከባድ እንደሚያደርግ ያሳስባሉ፡፡

አምባሳደር ባስ በበኩላቸው በወቅቱ አነስተኛ ጉዳት በነበረው ምርጫ ፌዴራሊዝሙን ከማዋቀር ውጪ አማራጭ እንዳልነበር በመጠቆም፣ ከ30 ዓመታት በኋላ ግን ይኼ ያስፈልጋል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካን በተመለከተ እየታየ ያለው ችግር የሥልጣን ክፍፍልን በማምጣት ማከም እንደሚቻል የጠቆሙት ደግሞ አምባሳደር ቡዝ ሲሆኑ፣ የብሔር ማንነት ባመጣቸው ችግሮች በተለይ በአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የተወሰኑ ክፍሎቻቸውን መቆጣጠርና መግዛት እየቻሉ አይደለም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. ከተደረገው ምርጫ በኋላ ኢሕአዴግም ሙሉ ትኩረቱን ወደ ኢኮኖሚው በማዞር በልማታዊ መንግሥትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እየተመራ ሁለት ተከታታይ የዕድገት ዕቅዶችን በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱን የጠቆሙትን የአምባሳደር ቡዝን ንግግር በመከተል ሐሳባቸውን የሰነዘሩት አምባሳደር ሺን፣ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአውቶ ፓይለት (ደመነፍስ) ሲሄድ ነበር በማለት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ግን ኢኮኖሚው ወዴት መሄድ እንዳለበት ያውቃሉ ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡ የዓብይ ጥረት ሊሠራ ይችላል በማለትም፣ በእርግጠኝነት ይሠራል ማለት ግን አይደለም ሲሉ ያስረግጣሉ፡፡

ለኢኮኖሚው ተጨማሪ ፈተና እየሆነ የመጣው የወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ቁጥር መጨመር አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት አምባሳደር ብራዚል በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ወሳኝ ትኩረት ያሻዋል ይላሉ፡፡ መንግሥት ለኢኮኖሚው መነቃቃት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወርና ገበያውን ለመክፈት ቢያውጅም፣ በእሳቸው የሕይወት ዘመን መንግሥት ከኢኮኖሚው ወጥቶ አያለሁ እንደማይሉም አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ባስ ለግብርናው ትኩረት መስጠት ሊዘነጋ አይገባም የሚል መልዕክት ቢይዙም፣ አምባሳደር ቡዝ በበኩላቸው ገበያውን ከአንድና ከተወሰኑ ተቋማት ጥገኝነት ማላቀቅ ትልቅ ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡

አራቱም አምባሳደሮች የአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያደረገውን የሰላም ስምምነትና ዕርቅ ለማውረድ የሄደበትን ጥረት ያደነቁ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግን ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉና ምን እንደሚያስቡ ከባድ እንደሆነ አምባሳደር ቡዝ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለኤርትራ የዕርቅና የውይይት ጥሪ ማቅረባቸው በወቅቱ የተሳሳተ አረዳድን ፈጥሮ ነበር ያሉት አምባሳደር ቡዝ በበኩላቸው፣ ሆኖም የወቅቱ ጥሪ ከንግግር ያላለፈና በፖሊሲ ያልተደገፈ፣ እንዲሁም ካልተወያየን ቀድመው የተቀመጡ የድንበር ማካለልና የአልጀርስ ስምምነትን አንቀበልም የሚል መልዕክት ነበረው ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የትግራይ ባለሥልጣናትን ወደ ጥግ ገፍተዋል በሚል እምነት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለዕርቅ ፈቃደኛ መሆናቸውን በመጠቆም፣ ከዚህ ዕርቅ ግን ኢትዮጵያ ምን አተረፈች ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተታለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኪሒደቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝተውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ምናልባትም ወደብ ታስብ ይሆናል፤›› በማለት ተንትነው፣ ‹‹መልካም ሒደት ነው፣ ነገር ግን የኢትዮጵያና የኤርትራን ችግር አልፈታም፤›› በማለት ያስገነዝባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -