Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ጉሬዛ

ቀን:

ጉሬዛ (Abyssinian Black and White Colobus- Colobus Guereza) ከአፍሪካ ጉሬዛ አስተኔዎች ሁሉ ተለቅ ያሉ፣ ሴቶቹ በአማካይ 9.2 ኪግ ሲመዝኑ፣ ወንዶቹ ደግሞ 13.5 ኪግ የሚመዝኑ፣ ዛፍ ላይ የሚኖሩ እንስሶች ናቸው፡፡ ዋነኛ ምግቡ ቅጠላ ቅጠሎችና፣ በተጨማሪም ፍራፍሬዎች ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚበሉት ቅጠል ሲሆን፣ አንዳንዴ ያልበሰሉ ፍሬዎችና እንቡጦች ሲያገኙም ይበላሉ፡፡

በግንባሩ፣ በጉንጮቹና በአገጩ ላይ ነጭ ፀጉር አለው፡፡ በጅራቱ ጫፍና በጎኑ ነጭ አለው፡፡ በተረፈ ፀጉሩ ጥቁር ነው፡፡ አዲስ የተወለዱት፣ እንደ ትልልቆቹ ፊታቸው ጥቁር ሳይሆን ቀይ ነው፡፡ ፀጉራቸውም በሙሉ ነጭ ነው፡፡

የመኖርያ ክልላቸው ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅጠል የትም እንደልብ ስለሚገኝና የተወሰኑ ዛፎችን ቅጠል ስለሚበሉ ነው፡፡ የምግብ መፍጫ ያካላቸው ክፍል የዳበረ ነው፡፡ በመሆኑም ቅጠል ብቻ ተመግበው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ ዓይነት ሥፍራዎችም ለመኖር ይችላሉ፡፡ በአገራችን ብዙ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ በአብዛኛው ቦታዎች እንደ ጻድቃን ይቆጠራሉ፡፡ ምክንያቱም  ዛፍ ላይ ቅጠላቸውን እየበሉ ነው የሚኖሩት፡፡ እናም፣ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ የተከዙ መስለው ብዙ ሳይንቀሳቀሱ ስለሚታዩና፣ የባሕታዊን የመሰለ እይታ ስላላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ኢሉባቡር ውስጥ ሰብል ከሚያጠፉ የጦጣ ዘሮች ውስጥ ጉሬዛዎችም የሚጠቃለሉ ሆነዋል፤ እዚያ ጻድቃን የሚላቸው የለም፡፡

ማኅበራዊ አደረጃጀታቸው ክልልተኛና በአንድ ወንድ የሚመሩ ቡድኖች ናቸው፡፡ ክልላቸው ተደራራቢ አይደለም፡፡ አንድ ዓይነተኛ የጉሬዛ ቡድን ከ6 እስከ 10 አባላት ይኖሩታል፡፡ ይህ ልጆቻቸውንም ጨምሮ ነው፡፡ አንዳንዴ ብቸኛ ወንዶች ይገኛሉ፡፡ አንዳንዴም በአንድ ቡድን ከአንድ በላይ ወንዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

በጠባብ ክልል መኖራቸው ከላይ ተገልጿል፡፡ ድንበራቸው ግልጽና በቅርብ የሚቆጣጠሩት ነው፡፡ በግምት ወደ 5 ሔክታር ግድም ይሆናል፡፡ በአንድ ካሬ ኪሜ ከ200 እስከ 500 ጉዞዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የጉሬዛዎች ቡድን፣ ከአካላዊም ሆነ ከማኅበራዊ አቅጣጫ፣ የተቀራረቡ ናቸው፡፡

ጉሬዛዎች ብዙም ሳይንቀሳቀሱ የሚበቃቸውን ያህል ቅጠላቸውን ስለሚበሉ፣ የቡድናቸው አባላት ተሰባስበው ይኖራሉ፡፡ በመኻከላቸው እጅግም ፀብ የለም፡፡ በተቃራኒው፣ ብዙ ጊዜ እርስ በርስ ስለሚቀማመሉ፣ ያለው ወዳጅነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ልጆች ሲወለዱ፣ ገና ፊታቸው ሳይጠቁርና ፀጉራቸው ነጭ እያለ፣ ከእናትየዋ ሌላ ሌሎቹም የቡድን አባላት፣ በተለይ ሴቶቹ ይይዟቸዋል፡፡ ለሕፃኖቹ የሚሰጠው ፍቅር፣ ፊታቸው ሲጠቁር፣ ዕድሜአቸው ወደ አራት ወር ግድም ሲሆን ያበቃል፡፡

ጉሬዛዎች በየዕለቱ ከ2 እስከ 3 ኪ.ግ የሚመዝን ቅጠላ ቅጠልና ሌሎች የዕፅዋት ክፍሎችን ይመገባሉ፡፡ የክብደታቸውን ሩብ (1/4) ወይም (1/3) ያህል መሆኑ ነው፡፡ መመገብ የጊዜአቸውን 30% ይወስዳል፡፡ ከተራዋ ጦጣ ጋር ሲነፃፀር፣ ጦጣ ለምግብ የምታጠፋው ጊዜ 47% ነው፡፡ ጉሬዛዎች ሲመገቡ 99% አንድ ቦታ ተቀምጠው ነው፡፡

ጉሬዛዎች ካላቸው የርስ በርስ መግባቢያ መንገድ አንዱ ድምፅ ነው፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚውሉ 5 ዓይነት ድምፆች አላቸው፡፡ በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች እንደሚታወቀው፣ በጠዋት የሚያሰሙት ከፍተኛ ድምፅ በማኅበር ከመሆኑ ጋር ተደምሮ እንግዳ ስሜት ይፈጥራል፡፡ አልፎ አልፎ ዋነኞቹ ወንዶች ከጎረቤት ወንዶች ጋር ግጭቶች ያደርጋሉ፡፡

የተለየ የመውለጃ ወቅት የላቸውም፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎቹ በክረምት ወራት ይወልዳሉ፡፡ የእርግዝና ርዝመት 6 ወር ሲሆን፣ አንዲት ሴት በየ20 ወራት (በአማካይ) ትወልዳለች፡፡ ለአካለ መጠን ለመድረስ ከ4 እስከ 6 ዓመቶች ይፈጅባቸዋል፡፡

ነጭ ሆነው የሚወለዱት ሕፃናት፣ ከ14 እስከ 17 ሳምንት በሆነ ጊዜ የትልልቆቹ ቀለም ይኖራቸዋል፡፡ ጉሬዛዎች ልጆቻቸውን ሆዳቸው ላይ ለጥፈው ነው የሚጓዙት፡፡ በ5 ሳምንት ዕድሜአቸው በግላቸው መሔድ ቢጀምሩም፣ 8 ወር እስኪሞላቸው እናታቸው ላይ መለጠፋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ዕድሜአቸው ከ23 እስከ 25 ሳምንት ሲሞላ፣ እናቶች ይተውአቸዋል፡፡ 50 ሳምንት ሲሞላቸው ሙሉ ለሙሉ በግላቸው ቢሆኑም፣ በመኝታ ጊዜ ከእናታቸው ጉያ አይርቁም፡፡

  • ሰሎሞን ይርጋ (ዶር.) “አጥቢዎች” (2000) 
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...